1እንግዲህ እናንተ ከበደላችሁና ከሓጢአታችሁ የተነሳ የሞታችሁ ነበራችሁ።
2በዚያን ጊዜ የዚህን ዓለም ክፉ መንገድ በመከተል፥ በአየር ላይ ባሉት ኀይላት ላይ ገዥ ለሆነው እንዲሁም በማይታዘዙት ልጆች ላይ ለሚሠራው መንፈስ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር።
3በአንድ ወቅት እኛ ሁላችን ለሥጋችን ክፉ ምኞት እየታዘዝንና ፈቃዱን እየፈጸምን፥ የአእምሮአችንንም ሐሳብ እየተከተልን በእነዚህ በማያምኑት ሰዎች መካከል እንኖር ነበር፤ በተፈጥሮአችንም እንደሌሎቹ የቁጣ ልጆች ነበርን።
4ነገር ግን እግዚአብሔር ምሕረት በማድረግ ባለጠጋ ስለሆነ፥ ከወደደን ከታላቅ ፍቅሩ የተነሳ
5በበደላችን ሙታን በነበርንበት ጊዜ እንኳ ከክርስቶስ ጋር አዲስ ሕይወት ሰጠን፤የዳናችሁትም በጸጋ ነው፤
6ከእርሱም ጋር አስነሳን፤በሰማያዊ ስፍራም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር እንድንቀመጥ አደረገን።
7ይህንንም ያደረገው፥በክርስቶስ ኢየሱስ በቸርነቱ የገለጠውን የጸጋው ባለጠግነት ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ በሚመጣው ዘመን ለእኛ ያሳይ ዘንድ ነው።
8የዳናችሁት በእምነት አማካይነት በጸጋ ነውና ፤ ይህ ከእግዚአብሔር ያገኛችሁት ስጦታ እንጂ ከእናንተ የሆነ ነገር አይደለም።
9ማንም ሰው እንዳይመካ በሥራ የተገኘ ነገር አይደለም
10ምክንያቱም እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት እንድንፈጽመው ያዘጋጀውን መልካም ሥራ ለመሥራት በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።
11ስለዚህ በአንድ ወቅት በአካል ላይ በሰው እጅ የሚከናወነውን መገረዝ ስላገኙ «የተገረዙ» በሚባሉት ዘንድ «ያልተገረዙ» ተብላችሁ የምትጠሩ በትውልድ አሕዛብ የነበራችሁ እንደሆነ አስታውሱ።
12በዚያን ጊዜ ከክርስቶስ ተለይታችሁ፥ የእስራኤል ወገን ከመሆን ርቃችሁ፥ለተስፋውም ኪዳን ባዕድ ሆናችሁ ያለ ተስፋ እና ያለ እግዚአብሔር በዓለም ላይ ትኖሩ እንደነበር ልብ በሉ።
13ነገር ግን አሁን ከእግዚአብሔር ርቃችሁ የነበራችሁት በክርስቶስ ኢየሱስ በመሆን በክርስቶስ ደም አማካይነት ወደ እግዚአብሔር እንድትቀርቡ ተደርጋችኋል።
14አይሁድንና አሕዛብን ሁለቱን አንድ ሕዝብ ያደረገ እርሱ ሰላማችን ነውና ፤ በሥጋውም እርስ በርስ የለያየንን የጥል ግድግዳ አፈረሰ።
15ይኸውም ከሁለቱ ሕዝቦች አንድ አዲስ ሕዝብ በመፍጠር ሰላምን ያደርግ ዘንድ የትእዛዛትንና የሕግ ደንቦችን በሥጋው ሻረ።
16ይህንንም ያደረገው በመስቀሉ አማካይነት በመካከላቸው የነበረውን ጠላትነት ገድሎ ሁለቱን ሕዝቦች አንድ አካል በማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ነው።
17ኢየሱስ መጥቶ ርቀው ለነበሩት እና ቀርበው ለነበሩት ለእነዚያ የምሥራቹን ወንጌል ሰበከ፤ ሰላሙንም አወጀ።
18በኢየሱስ አማካይነት እኛ ሁለታችንም በአንድ መንፈስ ወደ አብ መቅረብ እንችላለንና።
19ስለዚህ እናንተ አሕዛብ ከቅዱሳንና ከእግዚአብሔር ቤተ ሰብ አባላት ጋር የአንድ አገር ዜጎች ናችሁ እንጂ ከእንግዲህ መጻተኞችና እንግዶች አይደላችሁም።
20እነዚህ በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ ነው።
21ቤተ ሰቡ የሆነው ሕንጻ ሁሉ በኢየሱስ ኀይል አንድ ላይ ተገጣጥሞ ለጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ ለመሆን ያድጋል።
22እናንተም እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚኖርበት ሕንጻ እንድትሆኑ አብራችሁ በክርስቶስ እየታነጻችሁ ነው።