1ስለ ጻድቃንና ስለ ጥበበኛ ሰዎች፥ ስለ ሥራቸውም፥ ስለ እነዚህ ሁሉ ለመገንዘብ በልቤ አሰብሁ። ሁሉም በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ናቸው። አንድ ሰው ፍቅር ወይም ጥላቻ ይገጥመው እንደሆነ ማንም አያውቅም።
2ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ አለው። ጻድቃንን እና አመጸኞችን፥ መልካምና ክፉ ሰዎችን፥ ንጹሕ የሆኑትንና ያልሆኑትን፥ መሥዋዕት የሚያቀርበውንና የማያቀርበውን ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ይጠብቃቸዋል። መልካም ሰዎች እንደሚሞቱ ኃጢአተኞችም ደግሞ እንዲሁ ናቸው። የሚምለው ሰው እንደሚሞተው ሁሉ ለመማል የሚፈራው ሰውም ይሞታል።
3ከፀሐይ በታች ለተደረገው ሁሉ ክፉ ዕጣ ፈንታ አለው፥ ለሁሉም አንድ መጨረሻ። የሰዎች ልብ በክፋት የተሞላ ነው፥ በሕይወት እያሉም ዕብደት በልባቸው አለ። ከዚያ በኋላ ወደ ሙታን ይሄዳሉ።
4ከሞተ አንበሳ በሕይወት ያለ ውሻ እንደሚሻል በሕይወት ላለ ሰውም አሁንም ተስፋ አለው።
5ሕያዋን ሰዎች እንደሚሞቱ ያውቃሉ፥ ሙታን ግን ምንም አያውቁም። መታሰቢያቸው ተረስቷልና ምንም ብድራት አይኖራቸውም።
6ፍቅራቸው፥ ጥላቻቸውና ቅናታቸው ከብዙ ጊዜ በፊት ጠፍቷል። ከፀሐይ በታች በተደረገ በማንኛውም ነገር ዳግም ስፍራ አይኖራቸውም።
7መንገድህን ሂድ፥ ምግብህን በደስታ ተመገብ፥ በደስተኛ ልብ ወይንህን ጠጣ፥ መልካሙን ሥራህን እግዚአብሔር ተቀብሎታልና።
8ልብሶችህ ሁልጊዜ ነጭ ይሁኑ፥ ራስህንም በዘይት ተቀባ።
9ከፀሐይ በታች እግዚአብሔር በሰጠህ በከንቱ ዘመንህ፥ ከንቱ በሆነው የሕይወት ዘመንህ ሁሉ ከምትወዳት ሚስትህ ጋር በደስታ ኑር። ከፀሐይ በታች ለሆነው ሥራህ ይህ ብድራት ነው። እጅህ ለመሥራት የሚያገኘውን ሁሉ በሙሉ ኃይልህ ሥራ፥
10በምትሄድበት በመቃብር ስፍራ ሥራ ወይም ገለጻ ወይም እውቀት ወይም ጥበብ በዚያ የለምና።
11ከፀሐይ በታች አንዳንድ የሚያስደስቱ ነገሮችን አየሁ፡ ሩጫ ለፈጣኖች አይሆንም። ውጊያ ለብርቱ ሰዎች አይሆንም። እንጀራ ለጥበበኞች ሰዎች አይሆንም። ሀብት ለአስተዋይ ሰዎች አይሆንም። ሞገስ እውቀት ላላቸው ሰዎች አይሆንም። ከዚህ ይልቅ ጊዜና ዕድል በሁሉ ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል።
12ዓሳ በሚሞትበት መረብ እንደሚጠመድ ወይም ወፎች በወጥመድ እንደሚያዙ ማንም ሰው የሚሞትበትን ጊዜ አያውቅም። የሰው ልጆችም ልክ እንደ እንስሳ ድንገት በሚወድቅባቸው ክፉ ጊዜ ይታሰራሉ።
13ደግሞም ከፀሐይ በታች ያስገረመኝን ጥበብ አየሁ።
14ጥቂት ሰዎች ብቻ የሚኖሩባት አንዲት ከተማ ነበረች፥ አንድ ታላቅ ንጉሥ መጣባት፥ ከበባት፥ በዙሪያዋም ታላቅ ምሽግ ገነባባት።
15በከተማው ውስጥ አንድ ድሃ ጠቢብ ሰው ተገኘ፥ በጥበቡም ከተማይቱን አዳነ። በኋላ ላይ ያንን ድሃ ሰው ማንም አላሰበውም።
16እኔም፥ "ጥበብ ከኃይል ይሻላል፥ ነገር ግን የድሃው ጥበብ ተንቋል፥ ቃሎቹም አልተሰሙም" ብዬ ደመደምኩ።
17በሞኞች መካከል ከሚጮህ ማንኛውም ገዥ ይልቅ በዝግታ የሚነገሩ የጥበበኞች ሰዎች ቃል ይደመጣል።
18ከጦር መሣሪያዎች ጥበብ ትሻላለች፥ ነገር ግን አንድ ኃጢአተኛ ብዙ መልካም ነገሮችን ሊያበላሽ ይችላል።