1የሞቱ ዝንቦች ሽቶን ያገሙታል፥ ትንሽ ሞኝነትም ጥበብና ክብርን ሊጎዳ ይችላል።
2የጠቢብ ልብ ወደ ቀኝ ያዘነብላል፥ የሞኝ ልብ ግን ወደ ግራው።
3ሞኝ መንገድ ላይ በሚሄድበት ጊዜ ማስተዋሉ ያነሰ ነው፥ ሞኝነቱን ለሁሉ ያሳውቃል።
4አለቃ በቁጣ ቢነሣብህ ሥራህን አትልቀቅ። ትዕግስት ታላቁን ቁጣ ጸጥ ማድረግ ይችላል።
5ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ አለ፥ ያም ከገዝ የሚመጣ ስህተት ነው፡
6ውጤታማ ሰዎች ዝቅተኛ የሥራ መደብ ሲሰጣቸው ሞኞች የመሪነት ሥራ ተሰጣቸው።
7ባሪያዎች በፈረስ ተቀምጠው፥ ስኬታማ ሰዎች አንደ ባሪያ በእግራቸው ሲሄዱ አየሁ።
8ጉድጓድ የሚቆፍር በዚያ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል፥ ካብ የሚያፈርሰውንም እባብ ሊነድፈው ይችላል።
9ድንጋዮችን የሚፈነቅል በእነርሱ ሊጎዳ ይችላል፥ ግንድ የሚጠርብም አደጋ ይደርስበታል።
10የብረቱ መቁረጫ ጫፉ ቢደንዝና ሰው ባይስለው ብዙ ኃይል ሊያወጣበት የግድ ነው፥ ጥበብ ግን ውጤታማ የሚሆንበትን መንገድ ያዘጋጅለታል።
11ድግምቱ ከመደገሙ በፊት እባብ ቢነድፍ ደጋሚው ምንም አይጠቀምም።
12ከጠቢብ ሰው አፍ የሚወጣ ቃል ሞገስ አለው፥ የሞኝ ከንፈር ግን ራሱን ያጠፋዋል።
13ከሞኝ አፍ ቃል መውጣት ሲጀምር ሞኝነት አብሮ ይወጣል፥ በመጨረሻም ከአፉ ክፉ ዕብደት ይወጣል።
14ሞኝ ቃሉን ያበዛል፥ የሚመጣው ምን እንደሆነ ግን ማንም አያውቅም። ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ማን ያውቃል?
15ወደ ከተማ የሚወስደውን መንገድ እንኳን እስከማያውቁ ድረስ ሞኞችን ሥራቸው ያደክማቸዋል።
16ንጉሣችሁ ወጣት ከሆነና መሪዎቻችሁም ግብዣቸውን በማለዳ የሚጀምሩ ከሆኑ በዚያች ምድር መከራ ይሆናል።
17ነገር ግን ንጉሣችሁ ከተከበረው ቤተሰብ የተወለደ፥ መሪዎቻችሁ ለመስከር ሳይሆን ለመበርታት በተገቢው ጊዜ ሲመገቡ ምድሪቱ ደስ ይላታል።
18በስንፍና ምክንያት ጣሪያ ይዘብጣል፥ በእጅ ሥራ መፍታትም ቤት ያንጠባጥባል።
19ሰዎች ምግብን ለሣቅ ያዘጋጃሉ፥ ወይን ሕይወትን ደስ ያሰኛል፥ ገንዘብም ፍላጎትን ሁሉ ያሟላል።
20በልብህም ቢሆን ንጉሡን አትርገመው፥ በመኝታህም ላይ ባለጸጎችን አትርገም። በሰማይ የሚበር ወፍ ቃልህን ይወስድ ይሆናልና ክንፍ ያለውም ሁሉ ጉዳዩን ሊያሰራጨው ይችላል።