1ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም ለሰዎች ከባድ ነው።
2ለራሱ የሚመኘውን አንዳች ላያጣ እግዚአብሔር ሀብትን፥ ባለጠግነትንና ክብርን ይሰጠዋል፥ የሚደሰትበትን ችሎታ ግን አይሰጠውም። ይልቁንም እነዚህን ነገሮች ሌላው ሰው ይጠቀምባቸዋል። ይህ እንፋሎት፥ ክፉ ስቃይም ነው።
3ሰው አንድ መቶ ልጆች ቢወልድና ብዙ ዘመን ቢኖር፥ የዕድሜው ዘመን ቢረዝም፥፥ ልቡ ግን በመልካም ነገር ባይረካ፥ በክብርም ባይቀበር፥ ከዚህ ሰው ይልቅ ሞቶ የተወለደ ሕጻን ይሻላል አልሁ።
4እንዲህ ያለው ሕጻን እንኳን በከንቱ ይወለዳል በጨለማም ይሄዳል፥ ስሙም አይታሰብም።
5ይህ ሕጸን ፀሐይን ባያይ ወይም ምንም ባያውቅ፥ ያኛው ባይኖረውም ለዚህኛው ዕረፍት አለው።
6ሰው ሁለት ሺህ ዓመት ያህል እንኳን ቢኖር በመልካም ነገሮች ግን መደሰትን ባያውቅ፥ እንደ ሌላው ሁሉ ወደዚያው ስፍራ ይሄዳል።
7የሰው ሁሉ ሥራ አፉን ለመሙላት ነው፥ ፍላጎቱ ግን አይሞላም።
8በርግጥ ከሞኙ ይልቅ የጠቢብ ሰው ብልጫው ምንድነው? ድሃ በሌሎች ሰዎች ፊት እንዴት መመላለስ እንዳለበት ቢያውቅ ምን ብልጫ አለው?
9በምኞት ከመቅበዝበዝ በዓይን አይቶ መርካት ይሻላል፥ ይህም ደግሞ እንፋሎትና ንፋስን ለማገድ መሞከር ነው።
10ለነበረው ሁሉ ቀደም ሲል ስያሜ ተሰጥቶታል፥ ሰው ምን እንደሚመስልም አስቀድሞ ታውቋል። ስለዚህ በሁሉ ላይ ብርቱ ፈራጅ ከሆነው ጋር መከራከር አይረባም።
11የሚነገር ቃል ሲበዛ ከንቱነትም ይበዛል፥ ታዲያ ይህ ለሰው ምን ይጠቅመዋል?
12እንደ ጥላ በሚያልፍበት ከንቱና የተቆጠረ የሕይወት ዘመኑ ለሰው በሕይወቱ መልካም የሆነውን የሚያውቅ ማን ነው? እርሱ ካለፈ በኋላ ከፀሐይ በታች ምን ሊሆን እንዳለ ማን ሊነግረው ይችላል?