1ወደ እግዚአብሔር ቤት በምትሄድበት ጊዜ ጠባይህን ተቆጣጠር። ለመስማት ወደዚያ ሂድ። ሞኞች ክፉ መሥራታቸውን ሳያውቁ ከሚያቀርቡት መሥዋዕት ይልቅ መስማት ይበልጣል።
2ለመናገር እጅግ አትፍጠን፥ በእግዚአብሔር ፊት የትኛውንም ጉዳይ ለማቅረብ ልብህ እጅግ አይፍጠን። እግዚአብሔር በሰማይ ነው፥ አንተ ግን በምድር፤ ስለዚህ ቃልህ ጥቂት ይሁን።
3የምትሠራው ከበዛና ሃሳብ ከሆነብህ፥ ክፉ ህልም ሊገጥምህ ይችላል። ቃልህ ብዙ ሲሆን ብዙ የሞኝነት ነገርም ትናገራለህ።
4ለእግዚአብሔር በምትሳልበት ጊዜ ከመፈጸም አትዘግይ፥ እግዚአብሔር በሞኞች ደስ አይለውምና።
5የተሳልከውን ፈጽመው። የተሳሉትን ካለመፈጸም ያለመሳል ይሻላል።
6አንደበትህ ሰውነትህን ለኃጢአት እንዲያነሣሣው አትፍቀድለት። ለካህኑ መልዕክተኛ፥ "ያ ስዕለት ስሕተት ነበረ" አትበል። በሐሰት በመሳል እግዚአብሔርን ለምን ታስቆጣዋለህ፥ የእጅህንስ ሥራ እንዲያጠፋ እግዚአብሔርን ለምን ታነሣሣዋለህ?
7በብዙ ሕልም ውስጥ፥ በብዙም ቃል ውስጥ እንፋሎት የሆነ ከንቱነት አለ። ስለዚህ እግዚአብሔርን ፍራ።
8በግዛትህ ውስጥ ድሃው ሲበደል፥ ፍትህንና መብቱን ሲነጠቅ በምታይበት ጊዜ፥ ማንም አላወቀም ብለህ አትደነቅ፥ ምክንያቱም ከሥራቸው ያሉትን የሚቆጣጠሩ አለቆች አሉ፥ በእነርሱም ላይ እንኳን የበላይ አለቆች አሉ።
9በአጠቃላይ የምድሪቱ ምርት ለሁሉም ነው፥ ንጉሡ ራሱም ምርቱን ከእርሻ ይወስዳል።
10ማንም ብርን የሚወድ በብር አይረካም፥ ማንም ብልጽግናን የሚወድ ሁልጊዜ ተጨማሪውን ይፈልጋል። ይህም ደግሞ እንፋሎት ነው።
11ሀብት ሲበዛ በእርሱ የሚጠቀሙ ደግሞ ይበዛሉ። ባለቤቱ በዓይኖቹ ከማየቱ በስተቀር ሀብቱ ምን ይጠቅመዋል?
12ብዙም ሆነ ጥቂት ቢበላ፥ የሚሠራ ሰው እንቅልፉ ጣፋጭ ናት፥ የባለጸጋው ሀብት ግን እንቅልፉን ይነሳዋል።
13ከፀሐይ በታች ያየሁት እጅግ የከፋ ነገር አለ፡ ይኸውም በባለሌቱ የተከማቸው ሀብት መጥፊያው ሲሆን ነው።
14ባለጸጋው በክፉ አጋጣሚ ሀብቱን በሚያጣበት ጊዜ ለልጁ፥ እርሱ ላሳደገው፥ በእጁ የሚተውለት አይኖረውም።
15ሰው ከእናቱ ማኅፀን ራቁቱን እንደ ተወለደ፥ ራቁቱን ደግሞ የምድሩን ሕይወት ይሰናበታል። ከሥራው አንዱን በእጁ መውሰድ አይችልም።
16ሌላው እጅግ ክፉ ነገር፥ ሰው እንደ መጣ እንዲሁ ደግሞ መሄዱ ነው። ስለዚህ ለንፋስ በመሥራት ሰው የሚያገኘው ትርፍ ምንድነው?
17በዘመኑ ሁሉ በጨለማ ይበላል፥ በህመምና በቁጣ በብዙ ይበሳጫል።
18ተመልከቱ! እኔ እግዚአብሔር በሰጠን በምድር ሕይወታችን ከፀሐይ በታች በምንደክምበት፥ መልካምና ተስማሚ ሆኖ ያገኘሁት፥ መብላት፥ መጠጣትና ባገኘነው በሥራችን ውጤት ሁሉ መደሰትን ነው። ይህ የሰው ዕድል ፈንታው ነው።
19እግዚአብሔር ለማንኛውም ሰው ሀብትንና ባለጸግነትን፥ ድርሻውን የሚያገኝበትን ችሎታና በሥራው መደሰትን መስጠቱ ይህ የእግዚአብሔር ሥጦታ ነው።
20ለመሥራት በሚያስደስተው ነገር እግዚአብሔር ባተሌ ስለሚያደርገው፥ የሕይወት ዘመኑን እምብዛም አያስባቸውም።