1እንደገና ከፀሐይ በታች ስለሚደረገው ግፍ ሁሉ አሰብሁ። የሚጨቆኑትን ሰዎች ዕንባ ተመልከቱ። የሚያጽናናቸውም የለም። በጨቋኞቻቸው እጅ ኃይል አለ፥ ነገር ግን የተጨቆኑት ሰዎች አጽናኝ የላቸውም።
2ስለዚህ ካሉት የሞቱት፥ እስካሁን በሕይወት ካሉት ቀደም ሲል የሞቱት ይሻላሉ አልሁ።
3ሆኖም ከሁለቱ የሚሻለው ያልኖረው፥ ከፀሐይ በታች የሚደረገውን ክፉ ድርጊት ያላየው ነው።
4ከዚያም የትኛውም ጥረትና የጥበብ ሥራ ባልንጀራውን ለቅንዓት እንደሚያነሣሣው አየሁ። ይህም ደግሞ እንፋሎትና ንፋስን ለማገድ መሞከር ነው።
5ሞኝ ሰው እጁን አጣምሮ ይቀመጣል፥ አይሠራምም፥ ስለዚህ የራሱ ሥጋ ምግቡ ነው።
6ንፋስን ለማገድ በመሞከር ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ በጥሞና የተሠራ አንድ እፍኝ ይሻላል።
7ከዚያም እንደገና ስለሚበልጠው ከንቱነት፥ ከፀሐይ በታች በይበልጥ ተንኖ ስለሚጠፋው እንፋሎት አሰብሁ።
8ብቻውን የሆነ አንድ ሰው አለ። ወንድ ልጅም ሆነ አባት አንድም የለውም። ለሚሠራው ሁሉ ማለቂያ የለውም፥ ዓይኖቹም ባገኘው ብልጽግና አይረኩም። እርሱም፥ "የምለፋው ለማን ነው? ራሴንስ ከደስታ የማርቀው ለምንድነው?" ብሎ ይደነቃል። ይህ የከፋ ሁኔታ ደግሞም እንፋሎት ነው።
9ከአንድ ሰው ይልቅ ሁለቱ የተሻለ ሥራ ይሠራሉ፤ በጋራ ለሥራቸው የተሻለ ገቢ ማግኘት ይችላሉ።
10አንደኛው ቢወድቅ ሌላኛው ጓደኛውን ሊያነሣው ይችላልና። በመሆኑም በወደቀ ጊዜ የሚያነሣው ካልኖረ ብቸኛውን ሰው ሀዘን ይከተለዋል።
11ሁለቱ አብረው ቢተኙ ሊሞቃቸው ይችላል፥ ብቻውን ቢሆን ግን እንዴት ሊሞቀው ይችላል?
12አንድ ሰው ብቻውን ሊሸነፍ ይችላል፥ ሁለቱ ግን ጥቃቱን መመከት ይችላሉ። በሦስት የተገመደ ገመድ ቶሎ አይበጠስም።
13ማስጠንቀቂያዎችን እንዴት መስማት እንዳለበት ከማያውቅ ሞኝ ሽማግሌ ንጉሥ ይልቅ ድሃ፥ ነገር ግን ጥበበኛ የሆነ ወጣት ይሻላል።
14ወጣቱ ከወህኒ ወጥቶ ቢነግሥ ወይም በሀገሩ በድህነት ተወልዶ ቢያድግም ይህ አውነት ነው።
15ይሁንና ከፀሐይ በታች ሕያው የሆነና የሚንቀሳቀሰው ሁሉ ራሳቸውን ንጉሥ ሆኖ ለተነሣው ለሌላው ወጣት ሲያስገዙ አየሁ።
16አዲሱን ንጉሥ መታዘዝ ለሚፈልገው ሕዝብ ሁሉ መጨረሻ የለውም፥ በኋላ ላይ ግን ብዙዎቹ አያመሰግኑትም። በርግጥ ይህ ሁኔታ እንፋሎት፥ ንፋስንም ለማገድ መሞከር ነው።