መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መክብብ 2

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እኔም በልቤ፥ "ና እንግዲህ፥ በደስታ እፈትንሃለሁ። ስለዚህ እንዳሻህ ተደሰት" አልኩ። ግን ተመልከት፥ ይህም ደግሞ ልክ የአፍታ እስትንፋስ ነበር።
2ስለ ሣቅ "እርሱ ዕብደት ነው"፥ ስለ ደስታም "ምን ይጠቅማል?" አልኩ።
3በወይን ጠጅ ራሴን እንዴት እንደማስደስተው በልቤ መረመርሁ። እስካሁን ሞኝነትን ብይዛትም አዕምሮዬ በጥበብ እንዲመራ ተውኩት። ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ከሰማይ በታች ሊያደርጉት የሚገባቸውን መልካም ነገር ለማግኘት ፈለግሁ።
4ታላላቅ ነገሮችን አከናወንኩ። ለራሴ ቤቶችን ሠራሁ፥ ወይንንም ተከልሁ።
5የአትክልትና የመዝናኛ ቦታዎችን ለራሴ ሠራሁ፤ በእነርሱም ላይ ሁሉንም ዓይነት የፍሬ ዛፎች ተከልሁባቸው።
6ዛፎች የሚያድጉበትን ዱር የሚያጠጡ የውሃ ገንዳዎችን አበጀሁ።
7ወንድና ሴት ባሪያዎችን ገዛሁ፤ በቤተ መንግሥቴ የተወለዱ ባሪያዎችም ነበሩኝ። ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነገሡት ሁሉ እጅግ የሚበልጥ የከብት መንጋና የቤት እንስሶች ነበሩኝ።
8ብርና ወርቅን፥ የነገሥታቱንና የአውራጃዎቹንም ሃብት ለራሴ አከማቸሁ። ለእኔ ለራሴ ወንድና ሴት አዝማሪዎች ነበሩኝ፤ እጅግ በበዙት ሚስቶቼና ቁባቶቼም በምድር ማንኛውንም ሰው ሊያስደስተው የሚችለውን ነገር አደረግሁ።
9ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ታላቅና ባለጸጋ ሆንኩ፥ ጥበቤም ከእኔው ጋር ቆየች።
10ዓይኖቼ የፈለጉትን ማናቸውንም ነገር አልከለከልኳቸውም። በምሠራው ሁሉ ልቤ ስለ ተደሰተና ደስታ የሠራሁት ሥራ ሁሉ ብድራት ስለ ነበረ ከየትኛውም ደስታ ልቤን አልከለከልኩትም።
11ከዚያም እጆቼ ያከናወኗቸውን ተግባራት ሁሉ፥ እኔም የሠራኋቸውን ሥራዎች ተመለከትኩ፥ ነገር ግን ሁሉም እንፋሎትና ነፋስን ለማገድ መሞከር ነበር። በእርሱ ውስጥ ከፀሐይ በታች አንድም ትርፍ አልነበረበትም።
12ከዚያም ጥበብን፥ ደግሞም ዕብደትንና ሞኝነትን ለመመርመር ራሴን መለስኩ። አስቀድሞ ከተደረገው በቀር ከዚህኛው ንጉሥ በኋላ የሚመጣው ንጉሥ ምን ለማድረግ ይችላል?
13ከዚያም ልክ ብርሃን ከጨለማ እንደሚሻል ጥበብም ከሞኝነት የሚሻል መሆኑን መረዳት ጀመርሁ።
14ጥበበኛ ሰው የሚሄድበትን እንዲያውቅ ዓይኖቹን በራሱ ላይ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል፥ ሞኙ ግን በጨለማ ይሄዳል፥ ቢሆንም ለእያንዳንዱ የተዘጋጀለት ፍጻሜ ተመሳሳይ መሆኑን አውቃለሁ።
15እኔም በልቤ፥ "በሞኙ ላይ የሚደርሰው በእኔም ላይ ይደርሳል። ስለዚህ በጣም ጥበበኛ ብሆን ምን ልዩነት ያመጣል?" አልኩ። "ይህም ደግሞ እንፋሎት ብቻ ነው" ብዬ በልቤ ደመደምኩኝ።
16ምክንያቱም ጠቢቡም እንደ ሞኙ ለዘላለም አይታሰብም። በሚመጣው ዘመን ሁሉም ነገር የተረሳ ይሆናል። ልክ ሞኙ እንደሚሞት ጠቢቡም ሰው ይሞታል።
17ከፀሐይ በታች የሚሠራው ሥራ ሁሉ ክፉ ስለሆነብኝ ሕይወትን ጠላሁ። ይህም የሆነው ሁሉም ነገር እንፋሎትና ነፋስን ለማገድ መሞከር ስለሆነ ነው።
18ከፀሐይ በታች በሥራ የደከምኩበትን ሁሉ ጠላሁ፥ ከእኔ በኋላ ለሚመጣው ሰው ልተውለት የግድ ነውና።
19እርሱ ጥበበኛ ወይም ሞኝ ይሆን እንደሆነ ማን ያውቃል? ሆኖም ከሰማይ በታች በጥበቤ በሠራሁት ሁሉ ላይ አዛዥ ይሆናል። ይህም ደግሞ እንፋሎት ነው።
20ከዚህ የተነሣ ከፀሐይ በታች በሠራሁት ሥራ ሁሉ ላይ ልቤ ተስፋ መቁረጥ ጀመረ።
21ምክንያቱም አንዱ በጥበብ፥ በእውቀትና በብልሃት ይሠራ ይሆናል፥ ነገር ግን የነበረውን ነገር ሁሉ አንድም ላልለፋበት ሰው ይተውለታል።
22ይህም ደግሞ እንፋሎትና እጅግ የሚያሳዝን ነው። ከፀሐይ በታች ሰው ተግቶ በመሥራቱና ሥራውን ሁሉ ለማጠናቀቅ በልቡ በመሞከሩ ምን ያተርፋል?
23የየዕለት ሥራው በስቃይና በውጥረት የተሞላ ነው፥ ስለዚህ ነፍሱ በሌሊት እረፍት አታገኝም። ይህም ደግሞ እንፋሎት ነው።
24ለማንኛውም ሰው ከመብላት፥ መጠጣትና ከሥራው መልካም በሆነው ከመርካት የሚበልጥበት ምንም ነገር የለም። ይህ እውነት የሚመጣው ከእግዚአብሔር እጅ እንደሆነም አየሁ።
25ከእግዚአብሔር ካልሆነ በስተቀር ማን ሊበላ ይችላል? ወይም የትኛውንም ዓይነት ደስታ ማን ሊደሰት ይችላል?
26እርሱን ደስ ለሚያሰኝ እግዚአብሔር ጥበብን፥ እውቀትንና ደስታን ይሰጠዋል። እንዲሁም ለኃጢአተኛው የመሰብሰብንና የማከማቸትን ሥራ ይሰጠዋል፥ እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኘው ሰው ይሰጠው ዘንድ። ይህም ደግሞ እንፋሎትን ማብዛትና ነፋስን ለማገድ መሞከር ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።