1ይህ በኢየሩሳሌም የነገሠውና የዳዊት ልጅ የሆነው የአስተማሪው ቃል ነው።
2አስተማሪው እንዲህ ይላል፥ "እንደ እንፋሎት ትነት፥ በደመናም ውስጥ እንዳለ እስትንፋስ፥ ሁሉም ነገር ይጠፋል፥ በርካታ ጥያቄዎችን ትቶ።
3ከፀሐይ በታች በሚደክሙበት ሥራ ሁሉ የሰው ልጆች ምን ትርፍ ያገኙበት ይሆን?
4አንደኛው ትውልድ ይሄዳል፥ ሌላኛው ትውልድ ይመጣል፥ ምድር ግን ለዘላለም ትኖራለች።
5ፀሐይ ትወጣለች፥ ትጠልቃለችም፥ ዳግም ወደምትወጣበት ሥፍራ ለመመለስም ትቸኩላለች።
6ነፋስ ወደ ደቡብ ይነፍሳል፥ ወደ ሰሜንም ያከብባል፥ ሁሌም በመንገዱ ይሄዳል፥ እንደገናም ይመለሳል።
7ወንዞች ሁሉ ወደ ባህር ይፈስሳሉ፥ ባህሩ ግን መቼም ቢሆን አይሞላም። ወንዞቹ ወደሚሄዱበት ሥፍራ፥ ወደዚያው ሥፍራ እንደገና ይሄዳሉ።
8ሁሉም ነገር አድካሚ ነው፥ ሊያስረዳ የሚችልም የለም። ዓይን በሚያየው አይረካም፥ ጆሮም በሚሰማው አይሞላም።
9የሆነው ሁሉ ወደፊትም የሚሆን ነው፥ የተደረገውም ሁሉ ወደፊት የሚደረግ ነው። ከፀሐይ በታች አንድም አዲስ ነገር የለም።
10'ተመልከት፥ ይህ አዲስ ነው' ሊባልለት የሚችል አንዳች ነገር አለ? አሁን ያለው ሁሉ ለብዙ ዘመናት አስቀድሞ የነበረ ነው፥ ወደ እኛ ከመምጣቱ በፊት በዘመናት መካከል።
11በቀድሞ ዘመን የሆኑትን ነገሮች የሚያስታውስ ያለ አይመስልም። እጅግ ዘግይተው የሆኑትን ነገሮችና ወደፊት ሊሆኑ ያሉት ሁለቱም የሚታወሱ አይመስሉም።
12እኔ አስተማሪ ነኝ፥ በእስራኤልም ላይ በኢየሩሳሌም ንጉሥ ነበርኩ።
13ከሰማይ በታች የተደረገውን ነገር ሁሉ በጥበብ ለማጥናትና ለመመርመር አዕምሮዬን አሠራሁት። ይህ ምርምር እግዚአብሔር የሰው ልጆች በሥራ እንዲጠመዱ የሰጣቸው አድካሚ ተግባር ነው።
14ከሰማይ በታች የተሠሩትን ሥራዎች ሁሉ አየሁ፥ ተመልከቱ፥ ሁሉም የሚተንና ነፋስን ለማገድ መሞከር ነው።
15የተጣመመ መቃናት አይችልም! የጠፋው መቆጠር አይችልም!
16ለልቤ እንዲህ ስል ተናገርኩ፥ "ተመልከት፥ ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ጥበብን አከማችቻለሁ። አዕምሮዬ ትልቅ ጥበብንና እውቀትን አይቷል።"
17ስለዚህ ጥበብን ለማወቅ ልቤን አሠራሁት፥ ደግሞም ዕብደትንና ሞኝነትን። ይህም ደግሞ ነፋስን ለማገድ እንደ መሞከር መሆኑን አስተዋልኩኝ።
18ጥበብን በማብዛት ውስጥ ብዙ ተስፋ መቁረጥ አለ፥ እውቀትንም የሚያበዛ ሐዘንን ያበዛል።