መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘዳግም 32

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሰማያት ሆይ፥ አድምጡ እኔም እናገራለሁ፤ ምድር ሆይ፥ አንቺም የአፌን ቃል ስሚ።
2ትምህርቴም እንደ ዝናብ ይውረድ፤ ቃሌም እንደ ጤዛ ይንጠባጠብ፤ በቡቃያ ሣር ላይ እንደ ካፊያ፥ ለጋ ተክልም ላይ እንደ ከባድ ዝናብ ይውረድ።
3እኔ የእግዚአብሔርን ስም አውጃለሁ፤ የአምላካችንን ታላቅነት አወድሱ።
4እርሱ ዐለትና ሥራውም ፍጹም፥ መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው። የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፤ ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው።
5በእርሱ ላይ ክፋት ፈጽመዋል። ከነውራቸው የተነሣ ከእንግዲህ ልጆቹ አይደሉም። ወልጋዳና ጠማማ ትውልዶች ናቸው።
6እናንተ ተላላና ጥበብ የጎደላችሁ ሕዝብ፤ለእግዚአብሔር የምትመልሱለት በዚህ መንገድ ነውን? አባታችሁና ፈጣሪያችሁ የሠራችሁና ያበጃችሁእርሱ አይደለምን?
7የጥንቱን ዘመን፥ የብዙ ዓመቶችን አስታውሱ፤ አባቶቻችሁን ጠይቁ ይነግሩማልም፥ ሽማግሌዎቻችንም ጠይቁ ያስረዱአችኋል።
8ታላቁ አምላክ ለአሕዛብ ርስታቸውን በሰጠ ጊዜ የሰውንም ዘር በለያየ ጊዜ፤ በእስራኤል ልጆች ቁጥር ልክ፤ የአሕዛብን ርስት ድንበር ለየ።
9የእግዚአብሔር ድርሻ የገዛ ሕዝቡ ያዕቆብ የተለየ ርስቱ ነውና።
10እርሱን በምድረ በዳ፤ ባዶና ጭው ባለ በረሓ ውስጥ አግኘው፤እንደ ዐይኑ ብሌን ጠበቀው።
11ንስር ጎጆዋን እንደትጠብቅ፤ በጫጩቶቿም ላይ እንደምትረብብ፥ እነርሱን ለመያዝ ክንፎቿን እንደምትዘረጋ በክንፎቿም እንደምትሸከማቸው፥ እግዚአብሔር ክንፎቹን ዘርግቶ፥ ተሸከሞ ወሰዳቸው።
12እግዚአብሔር ብቻ መራው ምንም ባዕድ አምላክ ከእርሱ ጋር አልነበረም።
13በምድር ከፍታ ላይ አስኬደው፤ የእርሻንም ፍሬ መገበው፤ ከዐለት ድንጋይ ማር አበላው፤ ከባልጩትም ድንጋይ ዘይት መገበው። በወንድና በሴት ልጆቹ ተቆጥቶአልና።
14የላሙንና የበጉን መንጋ ቅቤና ወትት የሰቡትን በጎችና ፍየሎች፤ የባሳንን ሙኩት በግ፤ መልካም የሆነውንም ስንዴ ማለፊያውንም የወይን ጠጅ ጠጠህ።
15ይሹሩን ወፈረ፥ ረገጠ፤ ስብ ጠገበ፥ ሰውነቱ ደነደነ፥ ለሰለሰም። የፈጠረውንም አምላክ ተወ፤ የመጠጊያ ዐለት የሆነውን አዳኙንም ናቀው።
16በባዕዳን አማልክታቸው አስቀኑት፤ በአስፈያፊ ጣዖቶቻቸውም አስቆጡት።
17አምላክ ላልሆኑ አጋንንት፥ ላላወቋቸው አማልክት፥ ከጊዜ በኋላ ለተነሡ አማልክት፥ አባቶቻችውም ላልፈሯቸው አማልክት ሠዉ።
18አባት የሆናችሁን ዐለት ከዳችሁት፤ የወለዳችሁን አምላክ ረሳችሁ።
19እግዚአብሔር ይህን አይቶ ተዋቸው፤ በወንድና በሴት ልጆቹ አስጥተውታልና።
20እርሱም እንዲህ ብሎአል፦ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ መጨረሻቸው ምን እንደሚሆንም አያለሁ፤ ጠማማ ትውልድ፤ የማይታሙንም ልጆች ናቸውና።
21አምላክ ላልሆነው አስቀኑኝ፤ በከንቱ ጣዖቶቻቸውም አስቆጡኝ። እኔም ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋል፤ በማያስተውልም ሕዝብ አስቆጣቸዋለሁ።
22በቁጣዬ እሳት ተቀጣጥሎአልና፤እስከ ሲኦል ዘልቆ ይነዳል፤ ምድርን እስከ ሰብሏ ይበላል፤ የተራሮችንም መሠረት ያቀጣጥላል።
23በመዓት ላይ መዓት አመጣባቸዋለሁ። ፍላጻዬንም በእነርሱ ላይ እተኩሳለሁ። የሚያጠፋ ራብ፤በልቶ የሚጨርስ ቸነፈርና ከባድ መቅሠፍት እሰድባቸዋለሁ፤
24የአራዊትን ሹል ጥርስ፥ በምድር የሚሳብ የእባብ መርዝም እሰድባቸዋለሁ።
25ሰይፍ መንገድ ላይ ያስቀራቸዋል፤ በመኝታቸውም ድንጋጤ ይነግሣል፤ጎልማሳውና ልጃገረዷ፤ ሕፃኑና ሽማግሌው ይጠፋሉ።
26ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውን አጠፋለሁ፥ እበትናቸዋለሁም፤አልሁ፤
27ድል ያደረገው እጃችን ነው ብለው፥ ጠላቶቻቸው በስሕተት እንዳይታበዩ፥ የጠላት ማስቆጣት እንዳይሆን እሠጋለሁ።
28እስራኤላውንም አእምሮ የጎደላቸው፤ ማስተዋልም የሌላቸው ናቸው።
29አስተዋዮች ቢሆኑ ኖሮ ይህን በተገነዘቡና መጨረሻቸው ምን እንደሚሆን ባስተዋሉ ነብር።
30መጠጊያ ዐለታቸው ካልሸጣቸው እግዚአብሔር ካልተዋቸው በቀር፥ አንድ ሰው እንዴት ሺሁን ያሳድዳል፥ ሁለቱስ እንዴት አሥር ሺሁን እንዲሸሹ ያደጋሉ?
31የእነርሱ መጠጊያ ዐለታቸው እንደ እኛ መጠጊያ ዐለት አለመሆኑን፤ ጠላቶቻችንም እንኳ አይክዱም።
32ወይናቸው ከሰዶም ወይን ከገሞራም እርሻ ይመጣል፤ የወይናቸው ፍሬ በመርዝ፥ ዘለላቸውም መራራ ነው።
33ወይናቸው የእባብ መርዝ፤ መርዙም የጨካኝ እባብ ነው።
34ይህስ በእኔ ዘንድ ተጠብቆ ያለ፤ በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን?
35በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ፥ ጊዜው ሲደርስ እግራቸው ይሰናከላል፤ የመጥፊያቸው ቀን ቀርቦአል፤ የሚመጣባቸውም ነገሮች ይፈጥንባቸዋል።
36ኃይላቸው መድከሙን ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው አለመቅረቱን በሚያይበት ጊዜ፤ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፤ ለአገልጋዮቹም ይራራል።
37እንዲህም ይላል፦ መጠጊያ ዐለት የሆኗቸው፤ አማልክታቸው ወዴት አሉ?
38የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፤ የመጠጥ ቁርባናችውንም የወይን ጠጅ የጠጡ አማልክት ወዴት ናቸው? እስቲ ይነሡና ይርዷችሁ! እስቲ መጠለያ ይስጧችሁ!
39እኔ ራሴ እርሱ እንደ ሆንሁ እዩ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤እገድላለሁ፤ አድናለሁ፤አቆስላለሁ፤ እፈውሳለሁም፤ ከእጄም የሚያስጥል ማንም የለም።
40እጄን ወደ ሰማይ አነሣለሁ፤ ለዘላለምም ሕያው እንደ ሆንሁ እናገራለሁ።።
41የሚያብራቀርቅ ሰይፌን ስዬ እጄ ለፍርድ ስይዘው፤ ባላጋራዎቼን እበቀላቸዋለሁ፤ ለሚጠሉኝም እንደሥራቸው እከፍላቸዋለሁ።
42ሰይፌ ሥጋ በሚበላበት ጊዜ፥ ፍላጾቼ በደም እንዲሰክሩ አደርጋለሁ፤ ደሙ የታረዱትና የምርኮኞች የጠላት አለቆችም ራስ ደም ነው።
43አሕዛብ ሆይ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ፤ እርሱ የአገልጋዮቹን ደም ይመልሳል፤ጠላቶቹንም ይበቀላል። ምድሪቱንና ሕዝቡን ይቤዣቸዋል።
44ሙሴም ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ጋር መጥቶ የመዝሙር ቃሎችን በሕዝቡ ጆሮ ተናገረ።
45ሙሴም እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለመላው እስራኤል ተናገሮ ጨረሰ።
46እርሱም እንዲህ አላቸው፦ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዟቸው እኔ ዛሬ በግልጥ የምነግራችሁን ቃሎች ሁሉ በልባችሁ አኑሩ።
47ቃሎቹ ለእናንተ ሕይወታችሁ ናቸው፥ ባዶ ቃሎች አይደሉም፥ በእነርሱ ዮርዳንስን ተሻገራችሁ በምትወርሷትም ምድር ረጅም ዘመን ትኖራላችሁ።
48በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረ፦
49ከኢያሪኮ ማዶ ባለው የሞዓብ ምድር ከዓብሪም ተራሮች አንዱ ወደ ሆነው ወደ ናባው ተራራ ወጥተህ ለእስራኤላውያን ርስት አድርጌ የምሰጣትን የከነዓን ምድር አሻግረህ ተመልከት።
50ወንድምህ አሮን በሖር ተራራ ላይ እንደ ሞተና ወደ ወገኖቹ እንደ ተስበስበ ሁሉ አንተም በወጣህበት በዚያ ተራራ ላይ ሙት፤ ወደ ወገኖችህም ተሰብሰብ።
51ይህ የሚሆንበት ምክንያት ሁለታችሁም በሲን ምድረ በዳ በቃዴስ በምሪባ ውሃ አጠገብ በእስራኤላውያን መካከል በእኔ ላይ ባለመታመናችሁ፤ እንዲሁም በእስራኤላውያን መካከል የሚገባውን አክብሮት ባለመስጠታችሁ ነው።
52ስለዚህ ምድሪቱን ከሩቅ ሆነህ ታያታለህ እንጂ ለእስራኤል ሕዝብ ወደምሰጣት ምድር አትገባም።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።