1እግዚአብሔር በኮሬብ ከገባው ቃል ኪዳን በተጨማሪ በሞዓብ ምድር ከእስራኤላውያን ጋር እንዲያደርግ ሙሴን ያዘዘው የኪዳኑ ቃሎች እነዚህ ናቸው።
2ሙሴ እስራኤላውያንን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ እግዚአብሔር በግብፅ በፈርዖን፥ በሹማምንቱ ሁሉና በመላ አገሩ ያደረተውን ሁሉ ዐይኖቻችሁ አይተዋል።
3እነዚያን ከባድ ፈተናዎች ታምራዊ ምልክቶችና ታላቅ ድንቆች በገዛ ዐኖቻችሁ አይታችኋል።
4ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ እግዚአብሔር የሚያስተውል አእምሮ ወይም የሚያይ ዐይን ወይም የሚሰማ ጆሮ አልሰጣችሁም።
5በምድረ በዳ በመራኋችሁ በእነዚያ አርባ ዓመታት ውስጥ ልብሳችሁ አላረጀም፥ የእግራችሁም ጫማ አላለቀም፥
6ቂጣ አልበላችሁም፥ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣችሁም፤ ይህን ያደረግሁት እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንህ ታውቁ ዘንድ ነው።
7ወደዚህ ስፍራ በደረሳችሁ ጊዜ የሐሴንቦን ንጉሥ ሴዎንና የባሳን ንጉሥ ዐግ ሊወጉን መጡ፤ ሆኖም ድል አደረግናቸው።
8ምድራቸውንም ወስደን ለሮቤላውያን ለጋዳውያንና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገን ሰጠን።
9እንግዲህ የምታደርጉት ሁሉ እንዲከናወንላችሁ፤ የዚህ ኪዳን ቃሎች በጥንቃቄ ተከተሉ።
10እናንተ ሁላችሁ መሪዎቻችሁና አለቆቻችሁ፥ ሽማግሌዎቻችሁና ሹሞቻችሁ እንዲሁም ሌሎች የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ዛሬ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቆማችኋል፤
11ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁ እንጨታችሁን እየፈለጡ ውሃዎቻችሁንም እየቀዱ በሰፈራችሁ የሚኖሩ መጻተኞችም አብረአችሁ ቆመዋል።
12እዚህ የቆማችሁ፥ እግዚአብሔር ዛሬ ከእናንተ ጋር ወደ ሚያደርገውና በመሐላ ወደሚያጸናው ኪዳን፥ከእግዚአብሔር ከአምላካችሁ ጋር ትገቡ ዘንድ ለእናንተ በሰጣችሁ ተስፋና፥
13ለአባቶቻችሁ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በማለላቸው መሠረት እርሱ አምላካችሁ ይሆን ዘንድ እናንተም ሕዝቡ መሆናችሁን በዛሬው ዕለት ለማረጋገጥ ነው።
14እኔም ይህ የቃል ኪዳን የማደርገው ከእናንተ ጋር ብቻ አይደለም፤
15አብራችሁን በእግዚአብሔር በአምላካችን ፊት እዚህ ከቆማችሁት ጋር ብቻ ሳይሆን ዛሬ እዚህ ከሌሉትም ጋር ነው።
16በግብፅ ምድር እንዴት እንደኖርንና ወደዚህ ስንመጣም በየአገሮቹ ውስጥ እንዴት እንዳለፍን ራሳችሁ ታውቃላችሁ።
17በመካከላቸውም አስጸያፊ ነገሮቻቸውን፦ የእንጨትና የድንጋይ፥ የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን አይታችኋል፤
18የእነዚህን ሕዝቦች አማልክት ለማምለክ ልቡን ከእግዚአብሔር ከአምላካችን የሚመልስ ወንድ፥ ሴት፥ቤተ ሰብ፥ ወይም ጎሣና ነገድ ዛሬ ከመካከላችሁ አይገኙ፤ ከመካከላችሁ እንዲህ ያለውን መራራ መርዝ የሚያወጣ ሥር እንዳይኖር ተጠንቀቁ።
19እንዲህ ያለው ሰው የዚህን ቃል ኪዳን በሚሰማበት ጊዜ በልቡ ራሱን በመባረክ፦ እንደ ልቤ ግትርነት ብመላለስም እንኳ ሰላም አለኝ ብሎ ያስባል። ይህም እርጥቡን ከደረቁ ጋር ያጠፋል።
20እግዚአብሔር ለዚህ ሰው ፈጽሞ ምሕረት አያደርግለትም፥ ቁጣውና ቅናቱ በእርሱ ላይ ይነድበታል፤ በዚህ መጽሐፍ የተጸፉት ርግማን ሁሉ ይወርድበታል፤ እግዚአብሔርም ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል።
21በዚህ የሕግ መጽሐፍ በተጻፈው የኪዳኑ ርግማን መሠረት እግዚአብሔር እርሱን ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ለጥፋት ይለየዋል።
22የሚቀጥለው ትውልድ ከእናንተ በኋላ የሚተኩት ልጆቻችሁና ከሩቅ አገር የሚመጡ እንግዶች በምድሩቱ የደረሰውን ታላቅ መቅሠፍትና እግዚአብሔር ያመጣባቸውን በሽታዎች ያያሉ፤
23ምድሩቱ በሙሉ የተቃጠለ ጨውና ዲን ዐመድ ትሆናለች፤ አንዳች ነገር አይተከልባት፤ ምንም ነገር አያቆጠቁጥባትም። የሚያድግ ተክል አይገኝባትም። የምደርስባት ውድመት እግዝክአብሔር በታላቅ ቁጣ እንደ ገለባበጣቸው እንደሰዶምና ገሞራ እንደ አዳማና ሊባዮ ጥፋት ይሆናል።
24አሕዛብም ሁሉ፤ እግዚአብሔር በዚች ምድር ላይ ይህን ለምን አደረገባት? ይህ አስፈሪና የሚነድ ቁጣስ ለምን መጣባት? ብለው ይጠይቃሉ።
25ሕዝቡም እንዲህ ይላሉ፦ የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር ያወጣቸውንና ከእነርሱም ጋር ያደረጉትን ቃል ኪዳን ሕዝቡ ስለ ተዉ ነው፤
26ወጥተውም የማያውቋቸውን እርሱም ያላዘዛቸውን ሌሎችን አማልክት ስለአመለኩአቸውና ስለሰገዱላቸውም ነው።
27ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ የተጸፈውን ርግማን ሁሉ እስኪያመጣባት ድረስ የእግዚአብሔር ቁጣው በዚህች ምድር ላይ ነደደ።
28እግዚአብሔር በታላቅ አስፈሪነት፥በቁጣና በንዴት ከምድራቸው ነቀላቸው፤ ወደ ሌላም ምድር ጣላቸው የሚል ይሆናል።
29ምስጢር የሆነው ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ለዘላለም እንድንተገብረው ዘንድ የኛና የልጆቻችን ነው።