1አንድ ሰው አንዲት ሴት ካገባ በኋላ አሳፋሪ ነገር አግኝቶባት ባይደሰትባት የፍቺ ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ይስደዳት።
2ከቤቱ ከወጣች በኋላ ሌላ ባል ሊታገባ ትችላለች።
3ሁለተኛ ባሏም እንደዚሁ ጠልቷት የፍቺ ወረቀት በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ቢሰዳት፥ ወይም ቢሞት፥
4ከዚያ በኋላ ፈቶአት የነበረው የመጀመሪያ ባሏ፥ የረከሰች በመሆኗ እንደ ገና መልሶ ሊያገባት አይችልም፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው። እግዚአብሔር አምላካችሁ ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር ላይ ኃጢአት አታምጡ።
5አዲስ ሚስት በቅርብ ጊዜ ያገባ ሰው፥ ለጦርነት አይሂድ ወይም ሌላ ሥራ እንዲሥራ አይገደድ። ለአንድ ዓመት ነጻ ሆኖ እቤቱ ይቆይ፥ ያገባትን ሚስቱን ደስ ያሰኛት።
6ወፍጮና መጁን ወይም መጁንም እንኳ ቢሆን፥ የብድር መያዣ አድርጋችሁ አትውሰዱ፤ የሰውን ነፍስ መያዣ አድርጎ መውሰድ ይሆናልና።
7አንድ ሰው ከእስራኤላውያን ወንድሞቹ አንዱን ፈንግሎ በመውሰድ ባሪያ ሲያደርገው ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፥ ፈንጋዩ ይሙት። ክፉውን ከመካከላችሁ አስወግድ።
8የለምጽ ደዌን በተመለከተ ሌዋውያን ካህናት የሚሰጡአችሁን መመሪያ በትክክል ለመፈጸም ጥንቃቄ አድርጉ። እኔ ለእነርሱ የሰጠሁትን ትእዛዝ በጥንቃቄ ተከተሉ።
9ከግብፅ ከወጣችሁ በኋላ በመንገድ ላይ ሳላችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ በሙሴ እህት በምርያም ላይ ያደረገባትን አስታውሱ።
10ማናቸውንም ነገር ለባልንጀራችሁ ስታበድሩ መያዣ አድርጎ የሚሰጣችሁን ለመቀበል ወደ ቤቱ አትግቡ።
11እንንተ ከውጭ ሆናችሁ ጠብቅ፥ ያበደራችሁም ሰው መያዣውን ከቤት ያምጣላችሁ።
12ሰውየው ድኻ ከሆነ መያዣውን ከእናንተ ዘንድ አታሳድሩበት።
13መደረቢያውን ለብሶት እንዲያድር ፀሐይ ሳትጠልቅ መልሱለት። ከዚያም ያመሰግናችኋል፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ ፊትም የጽድቅ ሥራ ሆኖ ይቆጠርላችኋል።
14ድኻና ችግረኛ የሆነውን የምንዳ ሠራተኛ እስራኤላዊ ወንድማችሁም ሆነ፥ከከተሞቻችሁ ባንዲቱ የሚኖረውን መጻተኛ አትበዝብዙት፤
15የሠራበትን ሒሳብ በዕለቱ ፀሐይ ሳትጠልቅ ክፈሉት፤ ድኻ በመሆኑ በጉጉት ይጠባበቀዋልና። ያለበለዚያ ወደ እግዚአብሔር ይጮኸና ኃጢአት ይሆንባችኋል።
16አባቶች ስለ ልጆቻቸው፥ ልጆችም ስለ አባቶቻቸው አይገደሉ፤ እያንዳንዱ በራሱ ኃጢአት ይገደል።
17መጻተኛው ወይም አባት ለሌለው ልጅ ፍትሕ አትንፈጉት፤ ባል የሞትባትንም መደረቢያ መያዣ አታድርጉ።
18እናንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበራችሁና እግዚአብሔር አምላካችሁ ከዚያ እንደ ተቤዣችሁ አስታውሱ፤ ይህን እንድታደርጉ ያዘዙአችሁ ለዚህ ነው።
19የእርሻችሁን ሰብል በምታጭዱበት ጊዜ ተረስቶ የቀረ ነዶ ቢኖር፥ ያን ለመውሰድ ተመልሳችሁ አትሂዱ፤እግዚአብሔር አምላካችሁ በእጃችሁ ሥራ ሁሉ እንዲባርካችሁ ነዶውን ለመጻተኛው፥ አባት ለሌለውና ባል ለሞተባት ተዉ።
20የወይራ ዛፋችሁን ፍሬ በምታራግፉበት ጊዜ በየቅርንጫፉ ላይ የቀረውን ለመቃረም ተመልሳችሁ አትሂዱ ለመጻተኛ፥ አባት ለሌለውና ባል ለሞተባት ተዉ።
21የወይን ተክላችሁን ፍሬ ስትሰበስቡ ቃርሚያውን ለመሰብሰብ አትመለሱበት የቀረውን ለመጻተኛው፥ አባት ለሌለውና ባል ለሞተባት ተዉ።
22በግብፅ ባሮች እንደነበራችሁ አስታውሱ፤ ይህን እንድታደርጉ ያዘዙአሁን ለዚህ ነው።