መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘዳግም 21

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እግዚአብሔር አምላካችሁ እንድትወርሱአት በሚሰጣችሁ ምድር ላይ አንድ ሰው ተገድሎ ሜዳ ላይ ቢገኝና ገዳዩም ማን እንደ ሆነ ባይታወቁ፥
2ሽማግሌዎቻችሁና ዳኞቻችሁ ወጥተው የተገደለ ሰው ሬሳው ወድቆ ከተገኘበት አንሥቶ በአቅራቢያው እስካሉት ከተሞች ድረስ ያለውን ርቀት ይለኩ።
3ከዚያም የተገደለ ሰው ሬሳው ወድቆ ከተገኘበት ስፍራ በጣም ቅርብ የሆነችው ከተማ ሽማግሌዎች ለሥራ ያልደረሰችና ቀንበር ያልተጫነባትን ጊደር ይዘው፥
4ከዚያ በፊት ታርሶ ወይም ተዘርቶበት ወደማይታወቅ ወራጅ ውሃ ወዳለበት ሸለቆ ያምጡት። በዚያ ሸለቆም የጊደሪቱን አንገት ይስበሩ፥
5እንዲያገለግሉና በእግዚአብሔር ስም እንዲባርኩ፥ በማንኛውም የክርክርና የጥቃት ጉዳዮች ሁሉ ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ፥ እግዚአብሔር አምላካችሁ መርጦአቸዋልና የሌዊ ልጆች ካህናቱ ወደ ፊት ይቅረቡ።
6ከዚያም ሬሳው በተገኘበት አቅራቢያ ከተማ የሚኖሩ ሽማግሌዎች ሁሉ፥ በሸለቆው ውስጥ፥ አንገቷ በተሰበረው ጊደር ላይ እጃቸውን ይታጠቡ፤
7እንዲህም ብለው ይናገሩ፥ እጆቻችን ደም አላፈሰሱም፤ ድርጊቱ ሲፈጸምም ዐይኖቻችን አላዩም።
8እግዚአብሔር ሆይ፥ ስለ ተቤዥኸው ሕዝብህ ስለ እስራኤል ብለህ ይህን ስርየት ተቀበል፥ ሕዝብህንም በፈሰሰው ንጹሕ ደም በደለኛ አታድርግ። ስለ ፈሰሰውም ደም ስርየት ይደረግላቸዋል።
9በዚህም መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ቀና የሆነውን ስታደርጉ የንጹሑን ደም የማፍሰስ በደልን ከመካከላችሁ ታስወግዳላችሁ።
10ከጠላቶቻችሁ ጋር ጦርነት ልትገጥሙ ወጥታችሁ አምላካችሁ እግዚአብሔር እነርሱን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአችሁ በማረካችሁ ጊዜ፥
11ከምርኮኞቹ መካከል ቆንጆ ሴት አይታችሁ ብትማርኩ፥ ሚስታችሁ ልታደርጉአት ትችላላችሁ፤
12ወደ ቤታችሁ ውሰዱአት፥ ጠጉሯን ትላጭ፥ ጥፍሯንም ትቁረጥ።
13ስትማርኩአት የለበሰችውንም ልብስ ታውልቅ፥ እቤታችሁ ተቀምጣ ለአባትና ለናቷ ወር ሙሉ ካለቀሰችላቸው በኋላ፥ ከእርሷ ጋር ለመተኛና ባል ልትሆለት፥ እርሷም ሚስት ልትሆናችሁ ትችላለች።
14ነገር ግን በእርሷ ደስተኛ ባትሆን፥ ወደምትፈልገው እንድትሄድ ነጻነት ስጡአት፥ ውርደት ላይ ስለ ጠላችኋት በገንዘብ ልትሸጡአት ወይም እንደ ባሪያ ልትቆጥሩአት አይገባችሁም።
15አንድ ሰው ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት አንደኛዋን የሚወዳት፥ ሌላዋን ግን የሚጠላት ቢሆን፥ ሁለቱም ወንዶች ልጆችን ወልደውለት፥ በኩር ልጁ ግን የተወለደው ከማይወዳት ሚስቱ ቢሆን፥
16ንብረቱን ለልጆቹ በሚያወርስበት ጊዜ፥ የብኩርናን መብት ከማይወዳት ሚስቱ ከወለደው በኩር ልጅ ገፎ ከሚወዳት ሚስቱ ለተወለደው ልጁ በአድልዎ መስጠት አይገባውም፤
17በዚህ ፈንታ፥ ከተጠላችው ሚስቱ ለተወለደው ልጅ ካለው ሁብት ሁሉ ሁለት እጥፍ ድርሻውን በመስጠት ብኩርናውን ያስታውቅ ያ ልጅ የአባቱ ኃይል መጀመሪያ ነውና የብኩርና መብት የራሱ ነው።
18አንድ ሰው የአባቱን ወይም የእናቱን ትእዛዝ የማይሰማ፥ ቢቀጡትም የማይታረም እልከኛና ዐመፀኛ ልጅ ቢኖረው፥
19አባትና እናቱ ይዘው በሚኖሩበት ከተማ በር ወዳሉት አለቆች ያምጡት፥
20ይህ ልጃችን እልከኛና ዐመፀኛ ነው፥ አይታዘዘንም አባካኝና ሰካራም ነው ብለው ለአለቆች ይንገሯቸው።
21ከዚያም በኋላ የከተማዪቱ ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይወገሩት፥ ክፉውንም ከመካከላችሁ ታስወግዳላችሁ፥ እስራኤልም ሁሉ ይህን ሰምቶ ይፈራል።
22አንድ ሰው ለሞት የሚያበቃ በደል ፈጽሞ ቢገደልና ሬሳው በእንጨት ላይ ቢሰቀል፥
23ሬሳውን በእንጨት ላይ እንደ ተሰቀለ አታሳድሩት ምክንያቱም በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሚሰጣችሁን ምድር እንዳታረክሱ በዚያኑ ዕለት ቅበሩት።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።