1እግዚአብሔር አምላካችሁ ምድራቸውን ለእናንተ የሚሰጥባቸውን አሕዛብ በሚደመስሳቸው ጊዜና እናንተም እነርሱን አስለቅቃችሁ በከተሞቻቸውና በቤቶቻቸው በምትቀመጡበት ጊዜ፥
2እግዚአብሔር አምላካችሁ ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር አማካይ ስፍራ ሦስት ከተሞችን ለራሳችሁ ምረጡ፥
3ሰው የገደለ ሁሉ እንዲሸሽባቸው እግዚአብሔር አምላካችሁ ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር መንገዶችን ሠርታችሁ በሦስት ክፈሉአቸው።
4በተንኮል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ገድሎ ሕይወቱን ለማትረፍ ለሚሸሽ ሰው መመሪያው የሚከተለው ነው።
5እነሆ፥ አንድ ሰው ከባልንጀራው ጋር እንጨት ለመቁረጥ ወደ ጫካ ቢሄድ፥ ዛፉን ለመጣል መጥረቢያውን በሚሰነዝርበት ጊዜ ብረቱ ከእጀታው ወልቆ ባልንጀራውን በመምታት ቢገድለው፥ ያ ሰው ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ ሕይወቱን ማትረፍ ይችላል።
6አለበለዚያ በተንኮል ሳይሆን ድንገት ሳያስበው ባልንጀራውን ቢገድል፥ መንገዱ ረጅም ከሆነ ደም ተበቃዩ በንዴት ተከታትሎ ይደርስበትና መገደል የማይገባውን ሰው ሊገድል ይችላል። ይህ ከመሆኑ በፊት ባልንጀራውን ያልጠላ ከሆነ መሞት አይገባውም።
7ሦስት ከተሞችን ለራሳችሁ እንድትመርጡ ያዘዙአችሁ በዚሁ ምክንያት ነው።
8ለአባቶቻችሁ በመሐላ በገባላቸው ቃል መሠረት አምላካችሁ እግዚአብሔር ወሰናችሁን ሲያሰፋውና ለእነርሱ በሰጣቸው መሠረት ምድሪቷን ሁሉ ሲሰጣችሁ፤
9እግዝክአብሔር አምላካችሁን እንድትወዱና ምን ጊዜም በመንገዱ እንድትሄዱ ዛሬ የማዛችሁን እነዚህን ሕግጋት ሁሉ በጥንቃቄ የምትጠብቁ ከሆነ በእነዚህ ላይ ሌሎች ሦስት ከተሞችን ትጨምራላችሁ።
10እግዚአብሔር አምላካችሁ ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር የንጹሕ ሰው ደም እንዳይፈስና በሚፈሰውም ደም በደለኛ እንዳትሆኑ ይህን አድርጉ።
11ነገር ግን አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢጠላው አድፍጦ ጥቃት ቢያደርስበት፥ ቢገድለውና ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ ቢሸሽ፥
12የሚኖርባት ከተማ ሽማግሌዎች ሰው ልከው ከከተማው ያስመጡት፥ እንዲገድለውም ለደም ተበቃዩ አሳልፈው ይስጡት።
13አትራራለት፥ ነገር ግን መልካም እንዲሆንላችሁ የንጹሑን ደም በደል ከእስራኤል አስወግዱ።
14እግዚአብሔር አምላካችሁ እንድትወርሱአት በሚሰጣችሁ ምድር ውስጥ ለእናንተ በሚተላለፍላችሁ ርስት ላይ የቀድሞ ሰዎች ያስቀመጡትን የባልጀራችሁን የድንበር ምልክት አታንሡ።
15በማንኛውም ወንጀል ወይም ሕግ በመተላለፍ ሰውን ጥፋተኛ ለማድረግ አንድ ምስክር አይበቃም፥ጉዳዩ በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች ምስክርነት መረጋገጥ አለበት።
16ተንኮለኛ የሆነ ምስክር አንድን ሰው በሐሰት ለመመስከር ቢነሣ፤
17ክርክሩ የሚመለከታቸው ሁለቱ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት በዚያ ወቅት በሚያገለግሉት ካህናትና ፈራጆች ፊት ይቁሙ።
18ፈፋጆችም ጉዳዩን በጥልቅ ይመርምሩት፥
19ያም ምስክሩ በወንድሙ ላይ በሐሰት የመሰከረ መሆኑ ከተረጋገጠ በወንድሙ ላይ ለማድረግ ያሰበውን በእርሱ ላይ አድርጉበት ክፉውን ከመካከላችሁ አስወግዱ።
20የቀሩትም ሰዎች ይህን ሰምተው ይፈራሉ፤ እንዲህ ያለው ክፉ ነገርም ለወደፊቱ በመካከላችሁ ከቶ አይደገምም።
21ርኅራኄ አታድርጉ ሕይወት ለሕይወት፥ ዐይን ለዐይን፥ ጥርስ ለጥርስ፥ እጅ ለእጅ፥ እግር እግር ይመለስ።