1ሌዋውን ካህናት፥ የሌዊ ነገድ ሁሉ ከእስራኤል ጋር የመሬት ድርሻ ወይም ርስት ስለማይኖራቸው ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርበው ድርሻቸው ነውና ይብሉ።
2እግዚአብሔር በሰጣቸው ተስፋ መሠረት እርሱ ራሱ ርስታቸው ስለሆነ በወንድሞቻቸው መካከል ርስት አይኖራቸውም።
3ኮርማ ወይም በግ የሚሠዋው ሕዝብ ለካህኑ የሚሰጠው ድርሻ ወርቹን፥ ሁለት ጉንጮችንና የሆድ ዕቃውን ነው።
4የእህላችሁን፥ የአዲሱን ወይናችሁንና የዘይታችሁን በኩራት እንዲሁም ከበጎቻችሁ በመጀመሪያ የተሸለተውን ጠጉር ትሰጣላችሁ።
5በእግዚአብሔር ስም ቆሞ ለዘላለም ያገለግል ዘንድ እግዚአብሔር አምላክህ ከነገዶቻችሁ ሁሉ እርሱንና ዘሮቹን መርጦአል።
6አንድ ሌዋዊ ከሚኖርበት ከየትኛውም በእስራኤል ካሉት ከተሞቻችሁ መካከል በፍጹም ፈቃድ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ስፍራ ቢመጣ፥
7በእግዚአብሔር ፊት ቆመው እንደሚያገለግሉት ሌዋውያን ወንድሞቹ፥ እርሱም በእዚግአብሔር በአምላኩ ስም ያገልግል።
8ከቤተ ሰቡ ንብረት ሽያጭ ላይ ገንዘብ ቢቀበል እንኳ ባልንጀሮቹ ከሚያገኙት ጥቅም እኩል ይካፈላል።
9እግዚአብሔር አምላካችሁ ወደሚሰጣችሁ ምድር በምትገቡበትጊዜ በዚያ የሚኖሩት አሕዛብ የሚፈጽሙትን አስጸያፊ መንገድ አትከተሉ።
10በመካከላችሁ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሥዋ ሟርተኛ፥ ወይም መተተኛ፥ ሞራ ገለጭ፥ ጠንቋይ፥ ወይም በድግምት የሚጠነቁል፥
11መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከላችሁ ከቶ አይገኝ።
12እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፥ ከእነዚህ አጸያፊ ልምዶች የተነሣ እግዚአብሔር አምላካችሁ እነዚያን አሕዛብ ከፊታችሁ ያስወጣቸዋል።
13በእግዚአብሔር በአምላካችሁ ፊት ነውር የሌላው ይሁን።
14ምድራቸውን የምታስለቅቃቸው አሕዛብ፥ መተተኞችን ወይም ሟርተኞችን ያዳምጣሉ፤ እናንተ ግን ይህን እንድታደርጉ እግዚአብሔር አምላካችሁ አልፈቀደላችሁም።
15እግዚአብሔር አምላካችሁ ከገዛ ወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል። እርሱን አድምጡ።
16በኮሬብ ጉባኤ በተደረገበት ዕለት እንዳልሞት የእግዚአብሔር የአምላካችሁን ድምፅ አንስማ፤እንዲህ ያለውንም አስፈሪ እሳት ደግመን አንይ ብላችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁን የጠየቃችሁት ይህ ነውና።
17እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ የተናገሩት መልካም ነው።
18ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ። ቃሌን በአፉ አደርጋለሁ፤ የማዘውንም ሁሉ ይነግራቸዋል።
19ማንም ሰው ነቢዩ በስሜ የሚናገረውን ቃሌን ባይሰማ፤ እኔ ራሴ ተጠያቂነት አደርገዋለሁ።
20ነገር ግን እንዲናገር እኔ ያላዘዝሁትን ቃል በድፍረት በስሜና በሌሎች አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ ይገደል።
21እናንተም በልባችሁ እግዚአብሔር ያልተነገረውን መልእክት እንዴት ማወቅ እንችላለን? ብትሉ፥
22ነቢዩም በእግዚአብሔር ስም የተናገርው ካልተፈጸመ ወይም እውነት ሆኖ ካልተገኘ፤ መልእክቱ እግዚአብሔር የተናገርው አይደለም። ያ ነቢይ በድፍረት ተናግሮታልና እርሱን አትፍራው።