1እንከን ወይም ጉድለት ያለበትን በሬ ወይም በግ እግዚአብሔር ለአምላክችሁ አትሠዉ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነውና።
2እግዚአብሔር በሚሰጣችሁ ከተሞች በሮች አብሮአችሁ የሚኖር ወንድ ወይም ሴት ኪዳኑን በማፍረስ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ሲፈጽም ቢገኝ፥
3ትእዛዜንም በመተላለፍ ባዕዳን አማልክትን ያመለከ፥ ለእርሱም ማለትም ለፀሐይ ወይምለጨረቃ ወይም ለሰማይ ከዋክብት የሰገደ፥
4እናንተ ይህ መደረጉን ብትሰሙ ነገሩን በጥንቃቄ መርምሩ፥ የተባለውም እውነት ከሆንና እንዲህ ያለ አስጸያፊ ነገር በእስራኤል ዘንድ መፈጸሙ ከተረጋገጠ፥
5ይህን ክፉ ድርጊት የፈጸመውን ወንድ ወይም ሴት ወደ ከተማ ደጅ ወስዳችሁ ያን ሰው እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገሩት።
6ሞት የሚገባው ሰው በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች ምስክርነት ይገደል፥ ነገር ግን በአንድ ሰው ምስክርነት ብቻ ማንም ሰው አይገደል።
7ሲገደልም መጀመሪያ የምስክሮቹ እጅ ቀጥሎም የሕዝቡ ሁሉ እጅ ይረፍበት ክፉን ከመካከላችሁ አስወግዱ።
8በአንድ የነፍስ ግድያ ዓይነትና በሌላ በአንድ ዓይነት ሕጋዊ ክርክርን በሌላ ወይም በአንድ የክስ ዓይነትና በሌላ መካከል ውሳኔ የሚጠይቅ ማንኛውም ጉዳይ ቢነሣ፥ ከአቅማችሁ በላይ የሆነ ጉዳይ በከተሞቻችሁ ውስጥ ቢያጋጥማችሁ፥ ተነሥታችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ ወደሚመርጠው ስፍራ ውጡ።
9ካህናት ወደ ሆኑት ሌዋውያንና በዚያን ጊዜ ዳኛ ወደ ሆነው ሰው ሄዳችሁ ስለ ጉዳዩ ጠይቁአቸው፥ እነርሱም ውሳኔውን ይነግሩአችኋል።
10እናንተም እግዚአብሔር በሚመርጠው ስፍራ እነርሱ በሚሰጡአችሁ ውሳኔ መሠረት ፈጽሙ። እንድፈጽሙ የሚሰጡአችሁን መመሪያ ሁሉ በጥንቃቄ አድርጉ፥
11በሚያስተምሩአችሁ ሕግና በሚሰጡአችሁ መመሪያዎች መሠረት ፈጽሙ፥ እነርሱ ከሚነግሩአችሁ ቀኝም ግራም አትበሉ።
12እግዚአብሔር አምላካችሁን ለማገልገል በዚያ የሚቆመውን ካህን ወይም ዳኛ የሚንቅ ይገደል፥ ከእስራኤልም መካከል ክፉውን አስወግዱ።
13ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲሰማ ይፈራል፤ ከዚያ ወዲያም እንዲህ ያለውን የንቀት ድርጊት አይደግመውም።
14እግዚአብሔር አምላካችሁ ወደሚሰጣችሁ ምድር ስትገቡ፥ በምትወርሱአትና በምትቀመጡባት ምድር በዙርያዬ እንዳሉት አሕዛብ ሁሉ፥ እኔም በላዬ ንጉሥ ላንግሥ ብትሉ፥
15ከዚያ፥ እግዚአብሔር አምላካችሁ የሚመርጠውን ንጉሥ በላይህ ታነግሣለህ፥ ከገዛ ወንድሞችህ መካከል እንጂ እስራኤላዊ ወንድምህ ያልሆነውን ባዕድ በላይህ አታንግሥ።
16ንጉሡም ብዙ ፈረሶችን ለራሱ አያብዛ ወይም ደግሞ የፈረሰኞችን ቁጥር ለመጨመር ሕዝቡን ወደ ግብፅ አይመልስ፤
17እግዚአብሔር በዚያ መንገድ ፈጽሞ አትመለሱ፥ ብሎአችኋልና፤ ልቡ እንዳይስትም ብዙ ሚስቶችን አያግባ፥ ብዙ ብር ወይም ወርቅ ለራሱ አያብዛ።
18በመንግሥቱ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበትም ጊዜ የዚህን ሕግ ቅጅ ከሌዋውያን ካህናት ወስዶ በጥቅልል መጽሐፍ ለራሱ ይጻፍ።
19እግዚአሔር አምላኩን ማክበር ይማር ዘንድ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉና ይህን ሥርዓት በጥንቅቄ ይጠብቅ ዘንድ ከእርሱ ጋር ይሁን፤በሁሉም ቀኖች ያንብበው።
20ይህን የሚያደርገው ከወንድሞቹ ላይ ልቡ እንዳይኮራ፥ ከትእዛዘትም ወደ ኋላ እንዳይመለስ፥ እርሱና ልጆቹም ረጅም ዘመን ይገዙ ዘንድ፥ ከሕጉ ቀኝ ወይም ግራም አበል።