1እግዚአብሔር አምላካችሁ በአቢብ ወር ከግብፅ በሌሊት ስላወጣችሁ የአቢብ ወር ጠብቁ፥ የእግዚአብሔር የአምላካችሁን ፋሲካ አክብሩበት።
2እግዚአብሔር ለሰሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ በሚመርጠው ስፍራ ከበግና ከፍየል ወይም ከመንጋችሁ አንዱን እንስሳ እግዚአብሔር በአምላካችሁ ፋሲካ አድርጋችሁ ሠዉ።
3ከቦካ ቂጣ ጋር አትብሉ፤ ከግብፅ የወጣችሁ በችኮላ ነውና፥ ከግብፅ የወጣችሁበትን ጊዜ በሕይወታችሁ ዘመን ሁሉ ታስቡ ዘንድ ያልቦካ ቂጣ ሰባት ቀን ብሉ።
4ከምድራችሁ ሁሉ ላይ በእናንተ ዘንድ ለሰባት ቀን እርሾ አይገኝ በመጀመሪያው ዕለት ምሽት ከምትሠዉም ላይ ማናቸውም ሥጋ እስከ ጧት ድረስ እንዲቆዩ አታድርጉ።
5እግዚአብሔር አምላካችሁ በሚሰጣችሁ በማናቸውም ከተማ በሮች ላይ ፋሲካን መሠዋት አይገባችሁም።
6በዚህ ፈንታ፥ ለስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር አምላካችን በመረጠው ስፍራ ፀሐይ ስትጠልቅ በምሽት ላይ ከግብፅ ከወጣችሁበት ሰዓት ላይ በዚያ ፋሲካ ሰዉ።
7ሥጋውንም ጠብሳችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ በሚመርጠው ስፍራ ብሉ፥ ሲነጋም ወደ ድንኳናችሁ ተመልሳችሁ ሂዱ።
8ለስድስት ቀንም ያልቦካ ቂጣ ብሉ፤ በሰባተኛው ቀን በእግዚአብሔር በአምላካችሁ የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ ሥራም አትሥሩበት።
9እህላችሁን ማጨድ ከምትጀምሩበት ዕለት አንሥቶ ለራሰችሁም ሰባት ሳምንታትን ቁጠሩ።
10ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር አምላካችሁ በባረካችሁ መጠን በፈቃዳችሁ የምታመጡትን ስጦታ በማቅረብ በመከሩ በዓል እግዚአብሔር አምላካችሁን አክብሩ።
11እናንተ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ወንዶችና ሴቶች አጋልጋዮቻችሁ በከተሞቻችሁ ያለ ሌዋዊና መጻተኛ በመካከላችሁ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና ባል የሞተባቸው እግዚአብሔር አምላካችሁ ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን በሚመርጠው ስፍራ በእግዚአብሔር በአምላካችሁ ፊት ደስ ይበላችሁ።
12እናንተም በግብፅ ባሪያዎች እንደ ነበራችሁ አስታውሱ፥ እነዚህንም ሥርዓቶች በጥንቃቄ ጠብቁ አድርጉም።
13የእህላችሁን ምርት ከዐውድማችሁ ፤ ወይናችሁንም ከመጭመቂያችሁ ከሰበሰባችሁ በኋላ የዳስን በዓል ሰባት ቀን አክብሩ።
14በበዓላችሁ እናንተና ወንድና ሴት ልጆቻችሁ፥ ወንድና ሴት አገልጋዮቻችሁ፥ በከተማው ያለ ሌዋዊ መጻተኛ፥ አባት አልባውና ባል የሞተባት ደስ ይበላችሁ።
15እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ በዓሉን ሰባት ቀን አክብሩ፥ እግዚአብሔር አምላካችሁ በእህል ምርታችሁና በእጆቻችሁ ሥራ ሁሉ ይበርካችኋል፤ ደስታችሁም ፍጹም ይሆናል።
16ወንዶቻችሁ ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ በቂጣ በዓል፥ በመከር በዓልና በዳስ በዓል ላይ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በእግዚአብሔር በአምላካችሁ ፊት ይቅረቡ፥ ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ባዶ እጁን አይቅረብ፥
17በዚህ ፈንታ፥ እግዚአብሔር አምላካችሁ በባረካችሁ መጠን እያንዳንዱ እንደ ችሎታው ይስጥ።
18እግዝዚአብሔር አምላካችሁ በሚሰጣችሁ ከተማ ሁሉ ለየነገዶቻችሁ ዳኞችንና አለቆችን ሹሙ፥ እነርሱም ሕዝቡን በቅን ፍርድ ይዳኙ፥
19ፍርድ አታዛቡ፥ አድልዎ አታደርጉ፥ ጉቦም አትቀበሉ፥ ጉቦ የጠቢባንን ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና።
20በሕይወት እንድትኖሩና እግዚአብሔር አምላካችሁ የሚሰጣችሁን ምድር እንድትወርሱ ቅን ፍርድን ብቻ ተከተሉ።
21ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ በምታደርጉት መሠዊያ አጠገብ የአሼራን ምስል የእንጨት ዐምድ አታቁሙ።
22እግዚአብሔር አምላካችሁ የሚጠላውን ማምለኪያ ዐምድ ለእናንተ አታቁሙ።