1በመካከላችሁም፦ ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ፥ ምልክት ወይም ተአምራት ቢሰጣችሁ፥ እንደ ነገራችሁም
2ምልክቱ ወይም ተአምራቱም ቢፈጸም፥ እርሱም፦ የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት ሄደን እንከተል እናምልካቸውም ቢላችሁ፥
3እግዚአብሔር አምላካችሁን በፍጹም ልባችሁ፥ በፍጹም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደሆነ ያውቅ ዘንድ እግዚአብሔር አማላካችሁ ሊፈትናችሁ ነውና፥ የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም አላሚ አትስሙ።
4እግዚአብሔር አምላካችሁን ተከተሉ፥ እርሱንም አክብሩ፥ ትእዛዘትንም ጠብቁ፥ ድምፁንም ስሙ፥ እርሱንም አምልኩት፥ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ።
5ከግብፅ ምድር ካወጣችሁና ከባርነት ቤት ካዳናችሁ ከእግዚአብሔር ከአምላካችሁ ሊያስታችሁ ስለተናገረ ያ ነቢይ ወይም ያ ሕልም አላሚ ይገደል። ያም ነቢይ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንድትሄዱበት ካዘዛችሁ መንገድ ሊያወጣችሁ ነው። ስለዚህ ክፉውን ነገር ከመካከላችሁ አርቁ።
6የእናታችሁ ልጅ፥ ወንድማችሁ ወይም ወንድ ልጃችሁ ወይም ሴት ልጃችሁ ወይም በብብታችሁ ያለች ሚስታሁ ወይም እንደ ነፍሳችሁ የምትቆጥሩት ወዳጃችሁ በስውርም ሊፈትናችሁ፦ ኑ፥ እናንተ ወይም አባቶቻችሁ የማታውቁአችሁን አማልክት ሄደን እናምልክ ብሉአችሁ፥
7ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ሌላኛው ምድር ዳር ድረስ ወደ እናንተ የቀረቡት ከእናንተም የራቁት በዙሪያችሁ ያሉ አሕዛብ ከሚያመልኩአቸው አማልክት ቢያስታችሁ እሺ አትበሉ።
8አትስማሙአቸው፤አትስማቸውም። ዓይናችሁም አይራራላቸው፥ አትምራቸውም፥ አትሸሽጋቸውም።
9በዚህ ፈንታ ፈጽማችሁ ግደሉአቸው፤ እርሱን ለመግደል የእናንተ እጅ በእርሱ ላይ ይሁን፤ ከዚያም በኋላ የሕዝቡ ሁሉ እጅ በላዩ ይሁን።
10ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ካወጣችሁ ከእግዚአብሔር ከአምላካችሁ ሊያርቃችሁ ወድዶአልና፥ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገሩት።
11እስራኤልም ሁሉ ይህን ሰምተው ይፈራሉ፥ በመካከላችሁም እንዲህም ያለ ክፉ ሥራ ለማድረግ አይቀጥሉም።
12እግዚአብሔር አምልካችሁ ልትኖሩባችሁ በሚሰጣችሁ በአንዲቱ ከተማችሁ እንዲህ ሲባል ብትሰሙ፡-
13አንዳንድ ክፉ ሰዎች ከእናንተ መካከል ወጥተው፦ የማታውቋቸውን ሌሎችን አማልክት ሄደን እናምልክ ብለው የከተማቸውን ሰዎች አሳቱ፥ ሲሉ ብትሰሙ፤
14ታጣራላችሁ፥ ትመረምራላችሁ፥ በሚገባም ትጠይቃላችሁ። እነሆም፥ ይህም ክፉ ነገር በመካከላችሁ እንደ ተደረገ እውነት ሆኖ ቢገኝ።
15የዚያችን ከተማ ሰዎች በሰይፍ ስለት ፈጽሞ ትመታቸዋላችሁ፤ ከተማይቱን በእርስዋም ያለውን ሁሉ እንስሳውንም በሰይፍ ስለት ታጠፉአቸዋላችሁ።
16ዕቃዋንም ሁሉ ወደ አደባባይዋ ትሰበስባላችሁ፥ ከተማይቱንም ዕቃዋንም ሁሉ ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ በእሳት ፈጽማችሁ ታቃጥላላችሁ፤ እንደ ገና የማትሠራ ሆና ለዘላለም እንደ ፈረሰች ትቀራለች።
17ለጥፋት ከተለዩ ነገሮች ምንም እርም ነገር በእጃችሁ አይገኙ። እግዚአብሔር ከቁጣ ትኩሳት ይመለስ ዘንድ፥ ለአባቶቻችሁም እንደማለላቸው ይምራችሁና ይራራላችሁ ዘንድ፥ ያበዛላችሁም ዘንድ ነው።
18ዛሬ እኔ የማዝዛችሁን ትእዛዘት ሁሉ ትጠብቁ ዘንድ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ደስ የሚያሰኘውን ታደርጉ ዘንድ የእግዚአብሔር የአምላካችሁን ቃል ስሙ።