1በዚያን ጊዜም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ እንደ መጀመሪያ ያሉትን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠርበህ ወደ እኔ ወደ ተራራ ውጣ፤ ለአንተም የእንጨት ታቦት ሥራ።
2በሰበርሃቸው በመጀመሪያዎቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃላት በእነዚህ ጽላቶች ላይ እጽፋለሁ፤ አንተም በታቦቱ ውስጥ ታደርጋቸዋለህ።
3ከግራርም እንጨት ታቦትን ሠራሁ፥ እንደፊተኞቹም ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠረብሁ፥ ሁለቱንም ጽላቶች በእጄ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ።
4በተራራው ሥር የጉባዔው ቀን እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳት መካከል ሆኖ የተናገራችሁን አሥርቱን ቃላት በመጀመሪያ ተጽፈው እንደ ነበረ በጽላቶቹ ላይ ጻፈ፤ ከዚያም እግዚአብሔር እነርሱን ለእኔ ሰጠኝ።
5ተመልሼም ከተራራው ወረድሁ፤ ጽላችቶችንም በሠረሁት ታቦት ውስጥ አደረግኋቸው፤እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ በዚያ ሆኑ።
6የእስራኤልም ልጆች ከብኤሮት ብኔ ያዕቃን ወደ ሞሴራ ተጓዙ። በዚያ አሮን ሞተ፥ በዚያም ተቀበረ፥ በእርሱም ፋንታ ልጁ አልዓዛር ካህን ሆኖ አገለገለ።
7ከዚያም ወደ ጉድጎዳ ተጓዙ፤ከጉድጎዳም ወደ ውኃ ምንጮች ምድር ወደ ዮጥባታ ተጓዙ።
8በዚያን ጊዜም እግዚአብሔር የሌዊን ነገድ እግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ይሸከሙና እርሱንም እንዲያገለግሉ፥ በፊቱም ይቆሙ ዘንድ በስሙም እንዲባርኩ መረጠ።
9ስለዚህ ለሌዊ ከወንድሞቹ ጋር ክፍልና ርስት የለውም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው እግዚአብሔር ርስቱ ነው።
10በተራራውም ላይ እንደ መጀመሪያውም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቆየሁ። እግዚአብሔርም እንደገናም ሰማኝ፤ እግዚአብሔርም ሊያጠፋችሁ አልፈለገም።
11እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ተነሥተህ በሕዝቡ ፊት ሆነህ ሕዝቡን በጉዞው ምራው፤ ለአባቶቻቸው የማለሁላቸውን ምድር ሄደው ይገባሉ።
12እስራኤል ሆይ፥ አሁንስ አምላክህን እግዚአብሔርን ትፈራ ዘንድ በመንገዱም ሁሉ ትሄድ ዘንድ፥ አምላክህንም እግዚአብሔርን ትውድድ ዘንድ፥ በፍጹም ልብህ፥ በፍጹምም ነፍስህ ታመልከው ዘንድ መልካምም እንዲሆንልህ
13ዛሬ ለአንተ የማዘዘውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሥርዓት ትጠብቅ ዘንድ ከሆነ በቀር እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው?
14እነሆ፥ ሰማይና ሰማየ ሰማያትም፥ ምድርም በእርስዋም ያለው ሁሉ የእግዚአብሔር የአምላካችሁ ነው።
15ብቻ እግዚአብሔር ስለ አባቶቻችሁ ደስ ተሰኝቶአል፥ እነርሱንም ወድዶቸዋል፤ ከእነርሱም በኋላ እናንተን ዘራችሁን እንደ ዛሬው ሁሉ ከአሕዝብ ሁሉ መካከል መረጣችሁ።
16ስለዚህ እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ፥ አንገተ ደንዳኖች አትሁኑ።
17እግዚአብሔር አምላካችሁ የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም በፍርድ የማያደላ፥ መማለጃም የማይቀበል።
18እግዚአብሔር ለድሃ አደጉና ባል ለሞተባት ይፈርዳል፥ ምግብና ልብስም የሚሰጥ ነው።
19ስለዚህ እናንተም በግብፅ አገር ስደተኞች ስለ ነበራችሁ ስደተኛውን ውደዱ።
20እግዚአብሔር አምላካችሁን ፍሩ፥ እርሱንም አምልኩት። በእርሱም ተጣበቁ፤ በስሙም ማሉ።
21እርሱ ዓይኖቻችሁ ያዩትን እነዚህን ታላላቆችንና የሚያስፈሩትን ነገሮች ያደረገላችሁ ክብራችሁ ነው፤ አምላካችሁም ነው፤ ።
22አባቶቻችሁ ሰባ ሰዎች ሆነው ወደ ግብፅ ሄዱ፤ አሁንም እግዚአብሔር አምላካችሁ ብዛታችሁን እንደ ሰማይ ክዋክብት አደረገ።