መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዳንኤል 8

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ንጉሥ ቤልሻዘር በነገሠ በሦስተኛው ዓመት አስቀድሞ ከተገለጠልን ራእይ በኋላ እኔ ዳንኤል ሌላ ራእይ አየሁ።
2በራእዩም በኤሳም አውራጃ በሱሳ ግንብ ራሴን አየሁት፤ በራእዩም በኡባል የውሃ መውረጃ አጠገብነበርሁ፤
3ዓይኔን አንስቼ ስመለከት እነሆ፣ ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራ በግ በወንቁ አጠገብ ቆሞ አየሁ፤ ቀንዶቹም ረጃጅሞች ነበር፤ ከቀንዶቹም አንዱ ከሌላው ይረዝማል፤ ረጅሙ ቀንድ የበቀለው ዘግይቶ ቢሆንም ከአጭሩ ይልቅ በርዝመቱ የላቀ ነበር።
4አውራ በጉም ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ በቀንዱ ሲጎሽም አየሁ። ምንም ዐይነት እንስሳ ሊቋቋመው አልቻለም፤ ከእጁም ሊያድን የሚችል አልነበረም፤ የፈለገውን ሁሉ አደረገ፤ ታላቅም ሆነ።
5ስለዚህ ነገር እያሰብሁ ሳለሁ፣ በዐይኖቹ መካከል ትልቅ ቀንድ ያለው አውራ ፍየል፣ መሬት ሳይነካ ምድርን ሁሉ እያቋረጠ በድንገት ከምዕራብ መጣ፤
6በወንዙ አጠገብ ቆሞ ወዳየሁት፣ ሁለት ቀንድ ወዳለው አውራ በግ ተንደርዶ መጣበት፤ በታላቅ ቁጣም መታው።
7እየወጋውና ሁለቱን ቀንዶቹን እየሰበረ፣ በጭካኔ አውራውን በግ ሲጎዳው አየሁ፤ አውራ በጉም ለመቋቋም ጉልበት አልነበረውም። ፍየሉ በምድር ላይ ጥሎ ረገጠው፤ አውራ ብጉንም ከፍየሉ እጅ ለማዳን የሚችል አልነበረም።
8ፍየሉም ታላቅ ሆነ፤ ነገር ግን በኃይሉ በበረታ ጊዜ፣ ትልቁ ቀንዱ ተሰበረ፤ በቦታውም ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት የሚያመለክቱ አራት ታላላቅ ቀንዶች በቀሉ።
9ከእነዚህም ቀንዶች መካከል በአንዱ ላይ አንድ ትንሽ ቀንድ በቀለ፤ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ተከበረችው የእስራኤል ምድር በኃይል አደገ።
10ከሰማይ ሠራዊት ጋር ጦርነት እስኪገጥም ድረስ አደገ፤ ከሰማይና ከክዋክብት ሠራዊት የተወሰኑትን ወደ ምድር ጣለ፣ ረጋገጣቸውም።
11ከሰማይ ሠራዊት አለቃ ጋር እስኪተካከል ድረስ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ የልዑሉንም የዘወትር መሥዋዕት ወሰደበት፤ የመቅደሱንም ስፍራ አረከሰ።
12ከዐመፅ የተነሳም የቅዱሳን ሠራዊት ለፍየሉ ቀንድ አልፎ ተሰጠ፤ የሚቃጠል መሥዋዕቱም እንዲቆም ተደረገ። እውነትን ወደ ምድር ይጥላል የሚያደርገውም ሁሉ ይከናወንለታል።
13ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ሌላውም ቅዱስ እንዲህ አለው፤ “ስለ ዘወትሩ መሥዋዕት፣ ለጥፋት ምክንያት ስለሆነው ዐመፅ፣ ከእግር በታች እንዲረገጡ ዐልፈው ስለሚሰቱት መቅደስና ሠራዊት የታየው ራእይ የሚፈጸመው መቼ ነው?”
14እርሱም፣ “እስከ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ምሽቶችና ማለዳዎች ድረስ ይቆያል፤ ከዚያም መቅደሱ እንደገና ይነጻል” አለኝ።
15እኔ ዳንኤል ራእዩን ስመለከትና ሳስተውል ሳለ፣ ሰውን የሚመስል ከፊት ለፊቴ ቆመ፤
16ከኡባልም፣ “ገብርኤል ሆይ፤ ለዚህ ሰው የራእዩን ትርጕም ንገረው” ብሎ የሚጮህ የሰው ድምፅ ሰማሁ።
17እኔ ወደቆምሁበት እየቀረበ ሲመጣ፣ ደንግጬ በግንባሬ ተደፋሁ፣ እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ራእዩ ስለ ዘመኑ ፍጻሜ እንደሆነ አስተውል” አለኝ።
18እየተናገረኝ ሳለ፣ በምድር ላይ በግንባሬ ተደፋሁ፤ በከባድ እንቅልፍም ተዋጥሁ፣ እርሱ ግን ዳሰሰኝና በእግሮቼ አቆመኝ።
19እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ራእዩ በመጨረሻው ዘመን ሊሆን ያለውን የሚያመለክት ስለሆነ፣ በኋላ በቁጣው ዘመን ምን እንደሚሆን እነግርሃለሁ።
20ያየኸው ሁለት ቀንዶች የነበሩት አውራ በግ፣ የሜዶንና የፋርስን መንግሥታት ያመለክታል።
21ተባዕቱ ፍየል የግሪክ ንጉሥ ሲሆን፣ በዐይኖቹም መካከል ያለው ትልቁ ቀንድ የመጀመሪያው ንጉሥ ነው።
22የተሰበረውን ቀንድ የተኩት አራቱ ቀንዶቹ፣ ከመንግሥቱ የሚወጡትን አራት መንግሥታትን ያመለክታሉ፣ ነገር ግን ከእርሱ ጋር የሚተካከል ኃይል አይኖራቸውም።
23“በዘመነ መንግሥታቸው በስተ መጨረሻ፣ ዐመፀኞች ፍጹም እየከፉ በሚሄዱበት ጊዜ፣ አስፈሪ ፊት ያለው አታላይ ንጉሥ ይነሣል።
24እጅግ ብርቱ ይሆናል፤ ነገር ግን በገዛ ኃይሉ አይደለም። አሠቃቂ ጥፋት ይፈጽማል፤ የሚያደርገው ሁሉ ይከናወንለታል፤ ኃያላን ሰዎችንና ቅዱሳኑን ሕዝብ ያጠፋል።
25እጅግም ተንኮለኛ ስለሆነ በማታለል ይበለጽጋል፤ በልዑላን ልዑልም ላይ ይነሣል፤ ይሁን እንጂ እርሱም ይጠፋል ነገር ግን በሰው ኃይል አይደለም።
26የተሰጠህ የምሽቱና የማለዳው ራእይ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ የሚሆነውን ስለሚያመለክት ራእዩን ዘግተህ አትምበት።”
27እኔ ዳንኤል ዐቅሜ ተሟጦ ነበር፤ ለብዙ ቀናት ታመምሁ፣ ተኛሁም። ከዚያም በኋላ ተነሥቼ ወደ ንጉሡ ሥራ ሄድሁ። ባየሁት ራእይ ተደናግጬ ነበር፤ ነገሩም የገባው ማንም አልነበረም።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።