1ዳርዮስ በመንግሥቱ ሁሉ ላይ እንዲገዙ አንድ መቶ ሃያ መሳፍንትን መሾም ፈለገ፤
2በእነዚህም ላይ ሦስት የበላይ አስተዳዳሪዎችን አደረገ፣ ከእነርሱም አንዱ ዳንኤል ነበረ። ንጉሡ ጉዳት እንዳይደርስበት መሳፍንቱ ተጠሪነታቸው ለሦስቱ የበላይ አስተዳዳሪዎች እንዲሆን ተደረገ።
3ከመሳፍንቱና ከበላይ አስተዳዳሪዎቹ ሁሉ ይልቅ ዳንኤል ልዩ የጥበብ መንፈስ የሞላበት ሆኖ በመገኘቱ፣ ንጉሡ በመላው ግዛቱ ላይ ሊሾመው አሰበ።
4በዚህ ምክንያት የበላይ አስተዳዳሪዎቹና መሳፍንቱ ዳንኤል በሚያከናውነው የመንግሥት ሥራ እንከን ለማግኘት ፈለጉ፤ ነገር ግን ዳንኤል ታማኝ ጠንቃቃና በሥራው እንከን የሌለበት ስለነበር በእርሱ ላይ ስህተት ሊያገኙ አልቻሉም።
5እነዚህም ሰዎች፣ “ከአምላኩ ሕግ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ካልሆነ በቀር፣ ይህን ሰው የምንከስበት ምንም ሰበብ አናገኝበትም” አሉ።
6ከዚያም የበላይ አስተዳዳሪዎቹና አሳፍንቱ ዕቅድ ካወጡ በኋላ በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ!
7ንጉሥ ሆይ፤ እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ማንም ሰው ወደ ሌላ አምላክ መጸለይ እንደሌለበት ንጉሡ ዐዋጅ እንዲያወጣ ትእዛዙም እንዲፈጸም፤ ይህንም የተላለፈ ወደ አንበሶች ጉድጓድ እንዲጣል፣ የመንግሥት የበላይ አስተዳዳሪዎች፣ መኳንንት፣ መሳፍንት፣ አማካሪዎችና አገረ-ገዦች ሁሉ በአንድነት ተስማምተዋል፤
8ንጉሥ ሆይ፤ ይህን ዐዋጅ አውጣ፤ እንደማይሻረውና እንደማይለወጠው የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንዲሆን ትእዛዙን በጽሑፍ አድርገው።”
9ስለዚህ ንጉሡ ዳርዮስ ዐዋጁ ተጽፎ እንዲወጣ አደረገ።
10ዳንኤልም ዐዋጁ እንደወጣ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ሄደ፤ መስኮቶቹን በኢየሩሳሌም አንፃር ተከፍተው ባሉበት በሰገነቱ ቀድሞ ያደርግ እንደነበረው በቀን ሦስት ጊዜ ተንበርክኮ ጸለየ አምላኩንም አመሰገነ።
11ሰዎቹም በአንድ ላይ ሄደው ዳንኤልን ሲጸልይና አምላኩን ሲማጸን አገኙት።
12ወደ ንጉሡም ሄደው፤ “ንጉሥ ሆይ፤ በሚቀጥሉት ሠላሳ ቀናት ማንም ሰው ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደ ሰውም ሆነ ወደ ማንኛውም አምላክ ቢጸልይ በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ እንደሚጣል ዐዋጅ አውጥተህ አልነበረምን?” ሲሉ እርሱ ስላወጣው ዐዋጅ ጠየቁት። ንጉሡም፤ “ዐዋጁ እንደማይሻረው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጸና ነው” ሲል መለሰ።
13እርሱም ንጉሡን፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል፣ አንተም ሆነ በጽሑፍ ያወጣኸውን ዐዋጅ አያከብርም፤ አሁንም በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት።
14ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ፤ ዳንኤልንም ከዚህ ትእዛዝ የሚያድንበትን መንገድ አሰላሰለ፤ ፀሐይ እስክትጠልቅም ድረስ የተቻለውን ሁሉ አደረገ።
15ከዚያም ሰዎቹ በአንድ ላይ ወደ ንጉሡ ቀርበው፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሜዶንና በፋርስ ሕግ መሠረት፣ አንድ ንጉሥ የጣው ዐዋጅም ሆነ ትእዛዝ ሊለወጥ እንደማይችል ዕወቅ” አሉት።
16ስለዚህ ንጉሡ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም ዳንኤልን አመጡት፤ ወደ አንበሶቹም ጉድጓድ ጣሉት። ንጉሡም ዳንኤልን፣ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ያድንህ” አለው።
17ድንጋይ አምጥተው በጉድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፤ ንጉሡም በዳንኤል ላይ የተፈጸመው እንዳይለወጥ በራሱ የቀለበት ማሕተምና በመሳፍንቱ ቀለበቶች አተመበት።
18ንጉሡም ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፤ በዚያም ሌሊት ምግብ ሳይበላ፣ የሚያዝናናውም ነገር ሳይቀርብለት ዐደረ፤ እንቅልፍም ከእርሱ ራቀ።
19በማለዳም ገና ጎሕ ሲቀድ፣ ንጉሡ ተነሥቶ ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ እየተጣደፈ ሄደ።
20ወደ ጉድጓዱም ቀርቦ በሐዘን ድምፅ ዳንኤልን፣ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ፤ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሎአልን?” ብሎ ጠየቀው።
21ዳንኤልም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤
22ንጉሥ ሆይ፤ በፊቱ ቅን ሆኜ ስለተገኘሁ፣ በአንተም ፊት በደል ስላልተገኘብኝ አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ፤ እነርሱም አልጎዱኝም።”
23ንጉሡ እጅግ ተደሰተ፤ ዳንኤልን ከጉድጓድ እንዲያወጡት አዘዘ። ዳንኤል በአምላኩ ታምኖ ነበርና ከጉድጓድ በመጣ ጊዜ፣ አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም።
24በንጉሡ ትእዛእ ዳንኤልን የከሰሱት ሰዎች ተይዘው እንዲመጡ ተደረገ፤ እነርሱም ተይዘው ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር በአንበሶቹ ጉድጓድ ውስጥ ተጣሉ። ወደ ጉድጓዱም መጨረሻ ገና ሳይደርሱ አንበሶቹ ቦጫጩቋቸው፤ ዐጥንቶቻቸውንም ሁሉ ሰባበሩ።
25ከዚያ በኋላ ንጉሥ ዳርዮስ፣ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሕዝቦች፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ሁሉ እንዲህ የሚል መልእክት ጻፈ፤ “ሰላም ይብዛላችሁ!
26በማንኛውም የመንግሥቴ ግዛት ሰው ሁሉ፣ የዳንኤልን አምላክ እንዲፈራና እንዲያከብር ይህን ዐዋጅ አውጥቻለሁ። “እርሱ ለዘላለም የሚኖር ሕያው አምላክ ነውና መንግሥቱም አይጠፋም፤ ለግዛቱም መጨረሻ የለውም
27እርሱ ይታደጋል፣ ያድናልም በሰማይና በምድር ምልክቶችንና ድንቆችን ያደርጋል ዳንኤልን ከአንበሶች አፍ አድኖታል።
28ስለዚህ ዳንኤል በዳርዮስ መንግሥትና በፋርሳዊው በቂሮስ ዘመነ መንግሥት ሁሉ ኑሮው ተሳካለት።