1ንጉሥ ቤልሻዛር በሺህ ለሚቆጠሩ መኳንንቱ ታላቅ ግብዣ አደረገ፣ በሺሁም ፊት የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር።
2ቤልሻዘር የወይን ጠጅ እየጠጣ ሳለ፣ አባቱ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ያመጣቸውን የወርቅና የብር መጠጫዎችን እርሱና መኳንንቱ፣ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ እንዲያመጡለት አዘዘ።
3አገልጋዮቹም እነዚያን ከኢየሩሳሌም ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተወሰዱትን የወርቅ ዕቃዎች አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቱ፣ ሚስቶቹና ቁባቶቹም ጠጡባቸው።
4የወይን ጠጁንም እየጠጡ የወርቅና የብር፣ የናስ፣ የብረት፣ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክቶቻቸውን አመሰገኑ።
5በዚያን ቅጽበት የሰው እጅ ጣቶች ታዩ፤ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በመቅረዙ ትይዩ ባለው በግድግዳው ልስን ላይ ጻፉ፤ ንጉሡም ይጽፍ የነበረውን እጅ አየ፤
6በዚያን ጊዜ የንጉሡ ፊት ተለዋወጠ በድንጋጤም ተሞላ፤ እጆቹና እግሮቹ ከዱት፤ ጉልበቶቹም ተብረከረኩ።
7ንጉሡም ድምፁን ከፍ አድርጎ አስማተኞችን፣ ኮከብ ቆጣሪዎችንና መተተኞችን እንዲያስገቡለት አዘዘ፤ ለባቢሎናውያኑ ጠቢባን ንጉሡ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ጽሕፈት አንብቦ ትርጉሙን የሚነግረኝን ሐምራዊ መጎናጸፊያ አለብሰዋለሁ፤ የወርቅ ሐብልም በዐንገቱ አጠልቅለታለሁ፤ በመንግሥቴም ሥልጣን ሦስተኛውን ማዕረግ ይይዛል።”
8ከዚያም የንጉሡ ጠቢባን ሁሉ ገቡ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ሊያነብም ሆነ ትርጉሙ ምን እንደሆነ ለንጉሡ ሊነግር የሚችል ማንም አልነበረም።
9ንጉሥ ቤልሻዘር ፈራ ፊቱም እጅግ ተለወጠ፤ መኳንንቱም ግራ ግብቶአቸው ተደናገጡ።
10ንግሥቲቱም የንጉሡንና የመኳንንቱን ድምፅ ሰምታ ወደ ግብዣው አዳራሽ ገባች፤ እንዲህም አለች፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፣ አትደንግጥ፣ ፊትህም አይለዋወጥ
11በመንግሥትህ ውስጥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት አንድ ሰው አለ፤ ይህ ሰው በአባትህ ዘመን እንደ አማልክት ጥበብና ማስተዋል ዕውቀትም የሞላበት ሆኖ ተገኝቶአል፤ አባትህ ንጉሥ ናቡከደነፆርም የጠንቋዮች፣ የአስማተኞች፣ የኮከብ ቆጣሪዎችና የመተተኞች አለቃ አደረገው።
12ንጉሡ ብልጣሶር ብሎ የጠራው ይህ ዳንኤል መልካም መንፈስ፥ ዕውቀትና ማስተዋል ያለው ሆኖ ተገኘ፤ ሕልምን የመተርጎም፣ እንቆቅልሽን የመፍታትና የተሰወረውን የመግለጥ ልዩ ችሎታም ነበረው። ስለዚህ ዳንኤልን አስጠራ፣ እርሱም የጽሕፈቱን ትርጉም ይነግርሃል።”
13ዳንኤልንም ወደ ንጉሥ አቀረቡት፤ ንጉሡም እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ አባቴ ከይሁዳ ማርኮ ካመጣቸው መካከል አንዱ የሆንኸው ዳንኤል አንተ ነህን?
14የአማልክት መንፈስ በውስጥህ እንዳለ፣ ዕውቀት፣ ማስተዋልና ልዩ ጥበብ እንዳለህ ሰምቻለሁ፤
15ይህን ጽሕፈት አንብበው ትርጉሙ ምን እንደሆነ ይነግሩኝ ዘንድ ጠቢባንና አስማተኞች በፊቴ ቀርበው ነበር፣ ነገር ግን ሊገልጡት አልቻሉም።
16አንተ ግን መተርጎምና አስቸጋሪ የሆነውን ነገር መፍታት እንደምትችል ሰምቻለሁ። ይህን ጽሕፈት አንብበ ትርጉሙን ብትነግረኝ፣ ሐምራዊ መጎናጸፊያ ያለብሱሃል፣ የወርቅ ሐብል በዓንገትህ ያጠልቁልሃል፣ በመንግሥት ሥልጣንም ሦስተኛውን ማዕረግ እንድትይዝ ትደረጋለህ።”
17ዳንኤልም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ስጦታዎችህን ለራስህ አድርግ፤ ሽልማቶችህንም ለሌላ ሰው ስጥ፤ ይሁን እንጂ ጽሕፈቱን ለንጉሡ አነባለሁ፤ ትርጉሙ ምን እንደሆነም እነግረዋለሁ።”
18“ንጉሥ ሆይ፤ ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር ገናናነትንና ታላቅነትን፣ ክብርንና ግርማን ሰጠው።
19ከሰጠው ታላቅ ሥልጣን የተነሣ ሕዝቦችና መንግሥታት፣ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችም ሁሉ ተንቀጠቀጡለት ፈሩትም። ንጉሡም ሊገድል የፈለገውን ይገድል፣ ሊያድን የፈለገውን ሊያድን፣ ሊሾም ይፈለገውን ይሾም፣ ሊያዋርድ የፈለገውንም ያዋርድ ነበር።
20ነገር ግን ልቡ በትዕቢት በጸናና በእብሪት በተሞላ ጊዜ ከዙፋኑ ተወገደ፤ ክብሩም ተገፈፈ።
21ከሰው መካከል ተሰደደ፤ የእንስሳም አእምሮ ተሰጠው፤ ከዱር አህዮች ጋር ኖረ፤ እንድች በሬም ሣር በላ፤ ልዑል አምላክ በሰዎች መንግሥት ላይ እንደሚገዛና እነርሱምን ለወደደው እንደሚሰጥ እስኪያውቅ ድረስ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ።
22“ቤልሻዘር ሆይ፤ አንተ ልጁ ሆነህ ይሁ ሁሉ ብታውቅም፣ ራስህን ዝቅ አላደረግህም፤
23ይልቁንም በሰማይ አምላክ ላይ በመታበይ ራስህን ከፍ ከፍ አደረግህ፤ የመቅደሱን መጠጫዎች አስመጣህ፤ አንተና መኳንንትህ፣ ሚስቶችህና ቁባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው፣ ማየት፣ መስማት፣ ማስተዋልም የማይችሉትን የብርና የወርቅ የናስና የብረት፣ የእንጨትና የድንጋይ አማልክትን አመሰገንህ። ሕይወትህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ ግን አላከበርህም።
24ስለዚህ እርሱ ጽሕፈቱን ይጻፈውን እጅ ላከ።
25የተጻፈውም ጽሕፈት፣ ‘ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ’ ይላል
26የቃሉም ትርጉም ይህ ነው፤ ‘ማኔ’ ማለት እግዚአብሔር የመንግሥትህን ዘመን ቆጠረው፣ ወደ ፍጻሜም አደረሰው ማለት ነው።
27‘ቴቄል’ ማለት በሚዛን ተመዝነህ ቀለህም ተገኘህ ማለት ነው።
28‘ፋሬስ’ ማለት መንግሥትህ ተከፈለ፣ ለሜዶናውያንና ለፋርስ ሰዎች ተሰጠ ማለት ነው።”
29ከዚህ በኋላ በቤልሻዘር ትእዛዝ ዳንኤልን ሐምራዊ መጎናጸፊያ አለበሱት፣ የወርቅ ሐብል በዐንገቱ ኣይ አጠለቁለት፣ በመንግሥቱም ሥልጣን ሦስተኛውን ማዕረግ እንዲይዝ እንዲያደርጉት በዐዋጅ አዘዘ።
30በዚያኑ ሌሊት የባቢሎናውያን ንጉሥ ቤልሻዘር ተገደለ፤
31የሥልሳ ሁለት ዓመት ዕድሜ የነበረው ሜዶናዊው ዳርዮስም መንግሥቱን ወሰደ።