1ከንጉሥ ናቡከደነፆር፥በምድር ሁሉ ለሚኖሩ አሕዛብ፥ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ ለሚናገሩ ሁሉ፦ «ሰላማችሁ ይብዛ።
2ልዑል አምላክ ስላደረገልኝ ምልክቶችና ድንቆች እነግራችሁ ዘንድ መልካም ሆኖ ታየኝ።
3ምልክቶቹ እንዴት ታላላቅ ናቸው! ድንቆቹም እንዴት ብርቱዎች ናቸው! መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።
4እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደስ ብሎኝ፥ በቤተ መንግሥቴም በብልጽግና ፍሥሐ እያደረግሁ እኖር ነበር።
5ነገር ግን የአስፈራኝን ሕልም አለምሁ፤ ተኝቼም ሳለሁ ያየኋቸው ምስሎችና የአእምሮዬ ራዕዮች አወኩኝ።
6ስለዚህ ሕልሙን ይተረጉሙልኝ ዘንድ የባቢሎንን ጠቢባን ሁሉ በፊቴ እንዲያቀርቧቸው ትእዛዝ አወጣሁ።
7በዚያን ጊዜ አስማተኞች፥ሙታን ሳቢዎች፥ጠቢባንና ኮከብ ቆጣሪዎች መጡ፤ ሕልሙንም ነገርኳችው፥ ነገር ግን ሊተረጉሙልኝ አልቻሉም።
8በመጨረሻም፥ እንደ አምላኬ ስም ብልጣሶር ተብሎ የተጠራውና የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ዳንኤል ገባ። ሕልሙን ነገርኩት።
9«የአስማተኞች አለቃ ብልጣሶር ሆይ፦የቅዱሳን አማልክት መንፈስ እንዳለብህና የሚያስችግርህ ምሥጢር እንደሌለ አውቄአልሁና፤ በሕልሜ ምን እንዳየሁና ትርጉሙ ምን እንደሆነ ንገረኝ አልኩት።
10በአልጋዬ ላይ ትኝቼ ሳልሁ በአእምሮዬ ያየኋቸው ራዕዮች እነዚህ ነበሩ፦ ተመለከትኩ፥ በምድርም መካከል ዛፍ ነበረ፥ቁመቱም እጅግ ታላቅ ነበረ።
11ዛፉ አደገ፥በረታም። ጫፉ ሰማይ ደረሰ፥ እስከ መላው ዓለም ዳርቻ ድርስም ይታይ ነበረ።
12ቅጠሎቹ ያማሩ፥ ፍሬዎቹም የተት ረፈረፉ ነበሩ፤ ለሁሉ የሚሆን ምግብም በላዩ ነበረበት። የዱር አራዊት ከበታቹ ጥላ አግኝተው ነበር፥ የሰማያት አእዋፍም በቅርንጫፎቹ ይኖሩ ነበር። ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ከእርሱ ይመገቡ ነበር።
13በአልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ በአእምሮዬ አየሁ፥ አንድ ቅዱስ መልእክተኛም ከሰማያት ወረደ።
14እርሱም ጮኽ፥ እንዲህም አለ፦ ዛፉንና ቅርንጫፎቹን ቁረጡ፥ ቅጠሎቹን አራግፉ፥ ፍሬውንም በትኑ። አራዊቱ ከሥሩ፥ አእዋፍም ከቅርንጫፎቹ ይሽሹ።
15የሥሮቹን ጉቶ፥ በሜዳው ለምለም ሳር መካከል በብረትና በናስ ማሰሪያ እንደታሰረ በመሬት ውስጥ ተውት። በሰማያት ጠል ይረስርስ፥ በምድር ዛፎች መካከል ከአራዊት ጋር ይኑር።
16አእምሮው ከሰው አእምሮ ይለወጥ፥ ሰባት ዓመታትም እስኪያልፉ ድረስ የአውሬ አእምሮ ይሰጠው።
17በመልእክተኛው በተነገረው አዋጅ ይህ ውሳኔ ሆነ። ልዑሉ በሰዎች መንግሥታት ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለተናቁ እጅግ ትሑታን ለሆኑ ሰዎች እንኳን ሳይቀር፥ ሊያነግሠው ለወደደው ለማንም እንደሚስጥ ሕያዋን ሁሉ ያውቁ ዘንድ ይህ የቅዱሱ ውሳኔ ነው።
18እኔ ንጉሡ ናቡከደነፆር ይህን ሕልም አልሜአለሁ። አሁንም አንተ ብልጣሶር፥ በመንግሥቴ ካሉ ጠቢባን ሰዎች አንዳቸውም ሊተረጉሙልኝ አልቻሉምና ትርጉሙን ንገረኝ። አንተ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በውስጥህ ስላለ ልትተረጉም ትችላለህ።»
19በዚያን ጊዜ ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል፥ ለትንሽ ጊዜ እጅግ ታወከ፥ ሐሳቡም አስደነገጠው። ንጉሡም አለው፦ «ብልጣሶር ሆይ ሕልሙ ወይም ትርጉሙ አያስደንግጥህ።» ብልጣሶርም እንዲህ ሲል መለስ፥ «ጌታዬ ሆይ፥ ሕልሙ ለሚጠልህ፥ ትርጉሙም ለጠላቶችህ ይሁን።
20ያየኽው ዛፍ፥ ያድግ የነበረውና የበረታው፥ ጫፉም ወደ ሰማያት የደረሰው፥ እስከ መላው ዓለም ዳርቻ ድረስ የታየው፥
21ቅጠሎቹያምሩ የነበሩት፥ ፍሬዎቹም የተትረፈረፉት፥ ስለዚህም ለሁሉ የሚሆን መብል የነበረበት፥ ከበታቹም የምድር አራዊት ጥላ ያገኙበት፥ የሰማያት አእዋፍም ይኖሩበት የነበረ፥
22ያ ዛፍ፥ እጅግ ኃያል የሆንከው ንጉሥ አንተ ነህ። ታላቅነትህ እስከ ሰማያት፥ ሥልጣንህም እስከ ምድር ዳርቻ ደረሰ።
23አንተ ንጉሥ ሆይ፥ አንድ ቅዱስ መልእክተኛ ከሰማይ ሲወርድና እንዲህ ሲል አየህ፦«ዛፉን ቁረጡና አጥፉት፥ ነገር ግን የሥሮቹን ጉቶ በሜዳው ለምለም ሣር መካከል በብረትና በናስ ማሰሪያ እንደታሰረ በመሬት ውስጥ ተውት። በሰማያት ጠል ይረስርስ። ሰባት ዓመታት እስኪያልፉ ድረስ ከአራዊት ጋር በሜዳ ይኑር።
24ንጉሥ ሆይ ትርጉሙ ይህ ነው። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ይህ በአንተ ላይ የወጣ የልዑሉ አዋጅ ነው።
25ከሰዎች መካከል ተለይተህ ትባረራለህ፥ በሜዳም ከአራዊት ጋር ትኖራለህ። እንደ በሬ ሣር እንድትበላ ትደረጋለህ፥ በሰማያትም ጠል ትረሰርሳለህ፥ ልዑሉ በአሕዛብ መንግሥታት ላይ እንደሚገዛና እንዚህንም መንግሥታት እርሱ ለወደደው ለማንም ሊሰጣቸው እንደሚችል እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዓመታት ያልፉብሃል።
26የዛፉን የሥሩን ጉቶ ይተዉት ዘንድ እንደታዘዘው፥ እንዲሁ ሰማይ እንደሚገዛ ከተማርህ በኋላ መንግሥትህ ይመለስልሃል።
27ስለዚህ ንጉሥ ሆይ ምክሬ በፊትህ ተቀባይነት ያግኝ። ኃጢአት ማድረግህን አቁምና ትክክል የሆንውን ሥራ።
28እነዚህ ነገሮች ሁሉ በናቡከደነፆር ላይ ደረሱ።
29ከዐሥራ ሁለት ወሮች በኋላ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ሲመላለስ፣
30“ይህች ለንግሥናዬ መኖሪያ፣ ለክብሬም ግርማ እንድትሆን የመሠረትኋት ባቢሎን አይደለችምን?” አለ።
31ንጉሡ ይህን ገና ተናግሮ ሳይጨርስ እንዲህ የሚል ቃል ከሰማይ መጣ፣ “መንግሥትህ ከአንተ እንደ ተወሰደ ተነግሮአል፤
32ከሰዎች ትገለላለህ፤ መኖሪያህ ዱር ውስጥ ከአራዊት ጋር ይሆናል። እንደ በሬ ሣር ትበላለህ። ልዑል በሰዎች መንግሥት ላይ እንደሚገዛና እርሱ ለፈለገው እንደሚሰጥ እስክትገነዘብ ድረስ ሰባት ዓመታት ያልፉብሃል።”
33ይህ ቃል ናቡከደነፆር ላይ የተፈጸመው ወዲያውኑ ነበር፤ ከሰዎች ተገለለ፤ እንደ በሬ ሣር በላ፤ ሰውነቱ ከሰማይ በሚወርድ ጠል ረሰረሰ፤ ጠጉሩ እንደ ንስር ላባ፣ ጥፍሩም እንደ ወፍ ጥፍር ሆነ።
34ጊዜው ከተፈጸመ በኋላ እኔ ናቡከደነፆር ዐይኖቼን ወደ ሰማይ አነሣሁ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ። “ልዑልንም ባረክሁት ለዘላለም የሚኖረውን እርሱን አመሰገንሁት አከበርሁት። እርሱ ለዘላለም ይነግሣልና መንግሥቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ዘመን ነው።
35የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ኢምንት ይቆጠራሉ፤ በሰማይ ሰራዊትና በምድር ሕዝቦች መካከል የወደደውን ያደርጋል። የሚያስቆመው ወይም የሚከራከረው የለም። “ለምን እንዲህ አደረግህ?” የሚለውም የለም።
36አእምሮዬ እንደ ተመለሰልኝ ወዲያውኑ ከመንግሥቴ ክብር ግርማዊነቴና ሞገስ ተመለሰልኝ። አማካሪዎቼና ሹማምንቴ ፈለጉኝ። ወደ ዙፋኔ ተመለስሁ፤ የበለጠ ታላቅነትም ተሰጠኝ።
37እኔ ናቡከደነፆር አሁን የሰማይን ንጉሥ እባርካለሁ፤ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ። ሥራዎቹ ትክክል መንገዶችም ጽድቅ ናቸው። በትዕቢታቸው የሚራመዱትን ያዋርዳል።