1ንጉሡ ናቡከደነፆር ርዝመቱ ስድሳ ክንድ ስፋቱ ስድስት ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አሠራ። በባቢሎንም ክፍለ አገር በዱራ ሜዳ አቆመው።
2ከዚያም ናቡከደነፆር አማካሪዎችን፥ የግምጃ ቤት ኃላፊዎችን፥ ዳኞችን፥ የአጥቢያ ፈራጆችንና የክፍላተ አገር ከፍተኛ ባለ ሥልጣናትን ሁሉ ጨምሮ የክፍለ አገር አስተዳዳሪዎች፥ የክልል አስተዳዳሪዎችና የአካባቢ አስተዳዳሪዎች ላቆመው ምስል ምረቃ እንዲመጡ፥ በአንድ ላይ እንዲሰበሰቡ መልእክት ላከ።
3በዚያን ጊዜም አማካሪዎችን፥ የግምጃ ቤት ኋላፊዎችን፥ ዳኞችን፥ የአጥቢያ ፈራጆችንና የክፍላተ አገር ከፍተኛ ባለ ሥልጣናትን ጨምሮ የክፍለ አገር አስተዳዳሪዎች፥ የክልል አስተዳዳሪዎችና የአካባቢ አስተዳዳሪዎች ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ በአንድነት ተሰበሰቡ። በፊቱም ቆሙ።
4ከዚያም አዋጅ ነጋሪ እየጮኽ እንዲህ አለ፡- «አሕዛብ፥ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የምትናገሩ ሁሉ፥
5የመለከትና የእንቢልታ፥ የመስንቆና የክራር፥ የበገናና የዋሽንት፥ የዘፈንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ወድቃችሁ እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል።
6ማንም የማይወድቅና የማይሰግድ፥ በዚያው ጊዜ በሚንቦገቦገው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።»
7ስለዚህም አሕዛብ ሁሉ የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመስንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዋሽንቱን፥ የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ አሕዛብ ሁሉ፥ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ወድቀው ሰገዱ።
8በዚህ ጊዜም አንዳንድ ከለዳውያን መጥተው አይሁድን ከሰሱ።
9ለንጉሡ ናቡከደነፆርም እንዲህ አሉ፦ «ንጉሥ ሆይ ለዘላለም ኑር!
10ንጉሥ ሆይ፥አንተ የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመስንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዋሽንቱን፥ የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ የሰማ ማንኛውም ሰው ለወርቁ ምስል እንዲውድቅና እንዲሰግድ ትዕዛዝ አውጥተህ ነበር።
11ማንም ያልወደቀና ያላመለከ በሚንቦገቦገው የእሳት እቶን ውስጥ ሊጣል ይገባዋል።
12አሁን ግን በባቢሎን ክፍለ አገር ጉዳይ ላይ የሾምካቸው፥ ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብድናጎ የሚባሉ አንዳንድ አይሁድ አሉ። ንጉሥ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች አንተን ከምንም አይቆጥሩም። አማልክትህን አያመልኩም፥ አያገለግሉምም ወይም ላቆምከው የወርቁ ምስል አይሰግዱም።»
13በዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር በቁጣና በብስጭት ተሞላ፤ ሲድራቅን፥ ሚሳቅንና አብድናጎን ወደ እርሱ እንዲያመጡአቸው አዘዘ። ስለዚም እነዚህን ሰዎች ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው።
14ናቡከደነፆርም አላቸው፦«ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብድናጎ አማልክቴን አለማምለካችሁ ወይም ላቆምኩት የወርቅ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን?
15አሁንም የመለከቱንና የእንቢልታውን፥የመስንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዋሽንቱን፥ የዘፈኑንም ድምፅ ሁሉ በሰማችሁ ጊዜ ለመውደቅ እና ላሠራሁት ምስል ለመስግድ ዝግጅዎች ከሆናችሁ ሁሉም መልካም ይሆናል። ካላመለካችሁ ግን ወዲያው ወደ ሚንቦገቦገው የእሳት እቶን ትጣላላችሁ። ከእጄስ ሊያድናችሁ የሚችል አምላክ ማነው?»
16ሲድራቅ፥ሚሳቅና አብድናጎም ለንጉሡ እንዲህ ሲሉ መለሱ፦«ናቡከደነፆር ሆይ በዚህ ጉዳይ መልስ ልንሰጥህ አያስፈልገንም።
17መልስ መስጠት የሚገባን ከሆነ፥ የምናገለግለው አምላካችን ከሚንቦገቦገው የእሳት እቶን ሊያድነን ይችላል፥ ንጉሥ ሆይ፥ ከእጅህም ያድነናል።
18ነገር ግን ንጉሥ ሆይ ባያድነን እንኳን፥አማልክትህን እንደማናመልክና ላቆምከውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ በአንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን።
19በዚያን ጊዜ ናቡከደነፆር በቁጣ ተሞላ፤ በሲድራቅ፥ በሚሳቅና በአብድናጎ ላይ ፊቱ ተለወጠባቸው። የእቶኑ እሳት ብዙውን ጊዜ ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ እንዲነድድ አዘዘ።
20ከዚያም ከሠራዊቱ ጥቂት በጣም ብርቱ ሰዎችን፥ ሲድራቅን፥ሚሳቅንና አብድናጎን አሥረው ወደ ሚንቦገቦገው የእቶኑ እሳት እንዲጥሉአችው አዘዘ።
21እነርሱም መጎናጸፊያቸውን፥ ቀሚሳቸውን፥ ጥምጥማቸውንና ሌሎች ልብሶቻቸውን እንደ ለበሱ ታስረው ወደ ሚንቦገቦገው የእቶን እሳት ተጣሉ።
22የንጉሡ ትእዛዝ ጥብቅ ስለነበረና የእቶኑ እሳት እጅግ ነዶ ስለነበረ፥ ሲድራቅን፥ ሚሳቅንና አብድናጎን የወሰዱአቸውን ሰዎች ነበልባሉ ገደላቸው።
23እነዚህ ሦሥት ሰዎች እንደ ታሰሩ በሚንቦገቦገው የእቶን እሳት ውስጥ ወደቁ።
24ከዚያም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ፥ ፈጥኖም ተነሣ። አማካሪዎቹንም፦ «ሦሥት ሰዎችን አስረን እሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን?» ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም ለንጉሡ፦ «ንጉሥ ሆይ እርግጥ ነው» ብለው መለሱ።
25እርሱም፦ «እኔ ግን ያልታሰሩ አራት ሰዎች በእሳት ውስጥ ሲመላለሱ አያልሁ፥ጉዳትም አላገኛቸውም። የአራተኛው ማንጸባረቅ የአማልክትን ልጅ ይመስላል።» አለ።
26ከዚያም ናቡከደነፆር ወደ እሳቱ እቶን በር ቀረቦ፦ «የልዑል አምላክ ባሪያዎች ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብድናጎ ኑ ውጡ! ወደዚህ ኑ!» ብሎ ተጣራ። በዚያን ጊዜም ሲድራቅ፥ ሚሳቅና አብድናጎ ከእሳቱ ውስጥ ወጡ።
27በአንድነት የተሰበሰቡት የክፍላተ አገር አስተዳዳሪዎች፥ የክልል አስተዳዳሪዎች፥ ሌሎች አስተዳዳሪዎችና የንጉሡ አማካሪዎች እነዚህን ሰዎች ተመለከቱ። እሳቱ ሰውነታቸውን አልጎዳውም፥ የራሳችው ጸጉር አልተቃጠለም፥ መጎናጸፊያቸው አልተጎዳም፥ የእሳቱም ሽታ በላያቸው አልነበረም።
28ናቡከደነፆርም እንዲህ አለ፦«መልአኩን የላከውንና ለአገልጋዮቹ መልእክቱን የሰጠውን የሲድራቅን፥የሚሳቅንና የአብድናጎን አምላክ እናመስግን። በእርሱ በመታመን ትእዛዜን ችላ ብለዋል፥ ከአምላካቸውም ሌላ ማንኛውንም ሌላ አምላክ ከማምለክ ወይም ለእርሱ ከመስገድ ይልቅ ሰውነ ታቸውን አሳልፈው መስጠትን መርጠዋል።
29ስለዚህ እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና፥በሲድራቅ፥ሚሳቅና አብድናጎ አምላክ ላይ ክፉ የሚናገር ማንኛውም ሕዝብ፥አገር ወይም ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ይቆራረጣሉ፥ቤቶቻቸውም የቆሻሻ ክምር ይሆናሉ ብዬ አዝዤአለሁ።
30ከዚያም ንጉሡ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብድናጎን በባቢሎን አውራጃ ሾማቸው።