1ናቡከደነፆር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም አለመ፤ አእምሮው ታወከ፥ ሊተኛም አልቻለም።
2ከዚያም አስማተኞችና ሙታን ሳቢዎች እንዲመጡ አዘዘ፤ ጠንቋዮችንና ጠቢባንን ደግሞ ጠራ፤ ስለ ሕልሙ እንዲነግሩት ፈለጋቸው፤ ስለዚህ ገቡና በንጉሡ ፊት ቆሙ።
3ንጉሡ አላቸው፥«ሕልም አልሜአልሁ፥ሕልሙም ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ አእምሮዬ ተጨንቋል።»
4ከዚያም ጠቢባኑ በአረማይክ፥ «ንጉሥ ሆይ ለዘላለም ንገሥ! ሕልሙን ለእኛ ለባሪያዎችህ ተናገር፥ እኛም ፍቺውን እናስታውቅሃለን» ብለው ለንጉሡ ተናገሩ።
5ንጉሡም ለጠቢባኑ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፥«ሕልሙን ካልገለጣችሁልኝና ካልተረጎማችሁት፥ ሰውነታችሁ እንዲቆራረጥና ቤታችሁም የቆሻሻ ክምር እንዲሆን ወስኜአለሁ።
6ነገር ግን ሕልሙንና ትርጉሙን ከነገራችሁኝ፥ ከእኔ ዘንድ ሥጦታ፥ ሽልማትና ታላቅ ክብር ትቀበላላችሁ። ስለዚህ ሕልሙንና ትርጉሙን ንገሩኝ።»
7እነርሱም እንደገና እንዲህ ሲሉ መለሱ፥ «ንጉሡ ሕልሙን ለአገልጋዮቹ ይንገር፥ እኛም ትርጉሙን እንነግርሃለን።»
8ንጉሡም መለሰላቸው፥ «ይህን ጉዳይ በተመለከተ ውሳኔዬ ምን ያህል ጽኑ እንደሆነ ስላወቃችሁ ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት እንደምትፈልጉ በእርግጥ አውቃለሁ።
9ነገር ግን ሕልሙን ባትነግሩኝ፥ ሁላችሁን አንድ ቅጣት ይጠብቃችኋል። ሐሰት የሆኑ አሳች አሳቦችን ለማዘጋጅት ወስናችኋል፥ አሳቤንም እስክለውጥ ድረስ ልትነግሩኝ በአንድነት ተስማምታችኋል። ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፥ ያን ጊዜም ልትተረጉሙልኝ እንደምትችሉ አውቃለሁ።»
10ጠቢባኑም ለንጉሡ እንዲህ ሲሉ መለሱ፥«የንጉሡን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ሰው በምድር አይገኝም። አስማተኞችን፥ ሙታን ሳቢዎችን ወይም ጠቢባንን እንዲህ ዓይነት ጥያቄ የጠየቀ ታላቅና ኃያል ንጉሥ የለም።
11ንጉሡ የሚጠይቀው ነገር አስቸጋሪ ነው፥ በሰዎች መካከል ከማይኖሩት አማልክት በስተቀር ይህንን ለንጉሡ መንገር የሚችል ማንም የለም።
12ይህም ንጉሡን አስቆጣው እጅግም አበሳጨው፥ በባቢሎንም በጥበባቸው የሚታወቁትን ሁሉ እንዲያጠፉአቸው አዘዘ።
13ስለዚህም አዋጁ ወጣ፤ በጥበባቸው የሚታወቁት ሁሉ ሊገድሉ ሆነ፥ ዳንኤልንና ጓደኞቹንም ሊገድሉአቸው ፈለጉአቸው።
14በዚያን ጊዜ ዳንኤል በባቢሎን በጥበባቸው የሚታወቁትን ሁሉ ሊገድል ለመጣው ለንጉሡ የዘበኞች አዛዥ ለአርዮክ በጥንቃቄና በማስተዋል መለሰለት።
15ዳንኤልም «የንጉሡ አዋጅ ለምን አስቸኳይ ሆነ?» ሲል የንጉሡን አዛዥ ጠየቀው፤ አርዮክም የሆነውን ለዳንኤል ነገረው።
16በዚያን ጊዜ ዳንኤል ገባና ትርጉሙን ለንጉሡ የሚያስታውቅበት ቀጠሮ ከንጉሥ እንዲሰጠው ጠየቀ።
17በዚያን ጊዜ ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄደና የሆነውን ለአናንያ፥ ለሚሳኤልና ለአዛርያ ነገራቸው።
18እርሱም እነርሱም በጥበባቸው ከሚታወቁት ከተቀሩት የባቢሎን ሰዎች ጋር አብረው እንዳይገደሉ፥ ስለዚህ ምሥጢር ከሰማይ አምላክ ምሕረት እንዲለምኑ አጥብቆ ነገራቸው።
19በዚያች ሌሊት ምሥጢሩ ለዳንኤል በራዕይ ተገለጠለት። በዚያን ጊዜ ዳንኤል የሰማይን አምላክ አመሰገነ፥ አለም፦
20«ጥበብና ኃይል የእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ ይሁን።»
21ጊዜዎችንና ወቅቶችን ይለውጣል፤ነገሥታትን ይሽራል በዙፋናቸውም ነገሥታትን ያስቀምጣል። ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል።
22እርሱ በጨለማ ያለውን ያውቃልና ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነውና የጠለቁትንና የተሰወሩትን ነገሮች ይገልጣል።
23የአባቶቼ አምላክ ስለ ሰጠኽኝ ጥበብና ኃይል አመሰግንሃለሁ፥እባርክሃለሁም። የለመንህን ነገር አስታውቀኽኛል፥ንጉሡን ያሳሰበውን ነገር አስታውቀኽናል።
24ከዚህም በኋላ ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን ሁሉ እንዲገድል ንጉሡ ኃላፊነት ወደ ሰጠው ወደ አርዮክ ሄደ። ሄዶም አለው፦«በባቢሎን የሚገኙትን ጠቢባን አትግድል። ወደ ንጉሡ ይዘኽኝ ግባ እኔም የሕልሙን ትርጉም ለንጉሥ እናገራለሁ።»
25ከዚያም አርዮክ በፍጥነት ዳንኤልን ወደ ንጉሡ አስገባና አለ፦«የንጉሡን ሕልም ትርጉም የሚገልጥ ሰው ከይሁዳ ምርኮኞች መካከል አግኝቼአለሁ።
26ንጉሡም (ብልጣሶር ተብሎ የሚጠራውን) ዳንኤልን አለው፦«ያየሁትን ሕልምና ትርጉሙን ልትነግረኝ ትችላለህን?»
27ዳንኤልም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፦«ንጉሡ የጠየቀው ምሥጢር ጥበብ ባላቸው፥ በሙታን ሳቢዎች፥ በአስማተኞችና በኮከብ ቆጣሪዎችም ሊገለጥ አይችልም።
28ነገር ግን ምሥጢር የሚገልጥ አምላክ በሰማያት ውስጥ አለ፤ ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ! እርሱም በሚመጡት ዘመናት ሊሆን ያለውን አስታውቆሃል። በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለህ ያየኽው ሕልምህና የአእምሮህ ራዕዮች እነዚህ ናቸው፦
29ንጉሥ ሆይ! በአልጋህ ላይ ሆነህ ሊሆኑ ስላሉ ነገሮች ታስብ ነበር፤ ምሥጢርንም የሚገልጠው ሊሆን ያለውን አስታውቆሃል።
30እኔ ከሌሎች ሰዎች የሚበልጥ ጥበብ ስላለኝ ይህ ምሥጢር አልተገለጠልኝም። ንጉሥ ሆይ! ይህ ምሥጢር ለእኔ የተገለጠው አንተ ትርጉሙን ትረዳ ዘንድና የውስጥ አሳብህንም ታውቅ ዘንድ ነው።
31ንጉሥ ሆይ! ትልቅ ምስል አየህ ተመለከትህም። ምስሉም እጅግ ታላቅና አንጸባራቂ ነበር፥ በፊትህም ቆሞ ነበር። ማንጸባረቁም አስፈሪ ነበር።
32የምስሉ ራስ ከወርቅ የተሠራ ነበር። ደረቱና ክንዶቹ ከብር የተሠሩ ነበሩ። ወገቡና ጭኖቹ ከናስ፥
33እግሮቹም ከብረት የተሠሩ ነበሩ። መርገጫ እግሮቹ ከፊሉ ከብረት ከፊሉ ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ።
34የሰው እጆች ሳይነኩት ድንጋይ ሲፈነቀል፥ ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትንም የምስሉን መርገጫ እግሮች ሲመታቸውና ሲያደቃቸው ተመለከትህ።
35ከዚያም ብረቱ፥ሸክላው፥ ናሱ፥ ብሩና ወርቁ ወዲያው እንክትክታቸው ወጣ፤ በመከርም ወቅት በአውድማ ላይ እንዳል እብቅ ሆኑ። ነፋሱም ጠርጎ ወሰዳችው ምልክታቸውም አልቀረም። ነገር ግን ምስሉን የመታው ድንጋይ ታላቅ ተራራ ሆነ ምድርንም ሞላ።
36ሕልምህ ይህ ነበር። አሁን ትርጉሙን ለንጉሥ እንናግራለን።
37አንተ ንጉሥ ሆይ! የሰማይ አምላክ መንግስትን፥ ኃይልን፥ብርታትንና ክብርን የሰጠህ የነገሥታት ንጉሥ ነህ።
38የሰው ልጆች የሚኖሩበትን ስፍራ ሁሉ በእጅህ ሰጠህ። የምድር እንሰሳትንና የሰማያት ወፎችን በእጅህ ሰጠህ፤ በእነርሱ ሁሉ ላይም ግዢ አደረገህ። አንተ የምስሉ የወርቅ ራስ ነህ።
39ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሳል፤ከዚያም በኋላ በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሦሥተኛ የናስ መንግሥት ይነሳል።
40ብረት ሌሎች ነገሮችን እንደሚሰባብርና ሁሉን ነገር እንደሚያደቅቅ፥እንዲሁ እንደ ብረት ብርቱ የሆነ አራተኛ መንግሥት ይነሳል። እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያደቅቃቸዋል ይፈጫቸዋልም።
41እግሮቹና ጣቶቹ በከፊል ከሸክላ በከፊል ከብረት ተሠርተው እንዳየህ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፤ ለስላሳ ሸክላ ከብረት ጋር ተደባልቆ እንዳየህ እንዲሁ የተወሰነ የብረት ብርታት ይኖረዋል።
42የእግሮቹ ጣቶች በከፊል ከብረት በከፊል ከሸክላ ተሠርተው እንዳየህ መንግሥቱ በከፊል ብርቱ በከፊል ደካማ ይሆናል።
43ብረትና ለስላሳ ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ እንዲሁ ሕዝቡም ድብልቅ ይሆናል፤ብረትና ሸክላ እ ንደማይዋሓድ እነርሱም አብረው አይዘልቁም።
44በእነዚያ ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይጠፋና በሌላ ሕዝብ የማይሸንፍ መንግሥት ያቆማል። ሌሎቹን መንግሥታት ይፈጫቸዋል ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤ እርሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
45የሰው እጆች ሳይነኩት ድንጋይ ከተራራ ሲፈነቀል እንዳየህ እንዲሁ ነው። እርሱም ብረቱን፥ ናሱን፥ ሸክላውን፥ ብሩንና ወርቁን አደቀቃቸው። ንጉሥ ሆይ! ከዚህ በኋላ ሊሆን ያለውን ታላቁ አምላክ አስታውቆሃል። ሕልሙ እውነተኛ ፍቺውም የታመነ ነው።
46ንጉሥ ናቡከደነፆርም በዳንኤል ፊት በግንባሩ ተደፋ አከበረውም፤ መሥዋዕትና ዕጣን እንዲይቀርቡለት አዘዘ።
47ንጉሡ ዳንኤልን እንዲህ አለው፦«ይህን ምሥጢር መግለጥ ችለሃልና፥ ምሥጢርን ሁሉ የሚገልጠው አምላክህ በእውነት የአማልክት አምላክ፥ የነገሥታት ጌታ ነው።»
48ከዚያም በኋላ ንጉሡ ዳንኤልን እጅግ አከበረው፥ብዙ አስደናቂ ሥጦታዎችንም ሰጠው። በባቢሎን ክፍለ አገር ሁሉ ላይ ገዢ አደረገው። በባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ላይ ዋነኛ አስተዳዳሪ ሆነ።
49ዳንኤልም ለንጉሡ ጥያቄ አቀረበ፥ ንጉሡም ሲድራቅን፥ሚሳቅንና አብድናጎን በባቢሎን ክፍለ አገር ላይ አስተዳዳሪዎች አድርጎ ሾማቸው። ዳንኤል ግን በንጉሡ ቤተ መንግሥት ተቀመጠ።