መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዳንኤል 10

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የፋርስ ንጉስ ቂሮስ በነገሰ በሦስተኛው ዓመት ብልጣሶር ለተባለው ዳንኤል ራዕይ ታየው መልዕክቱ እውነት ነው፤ ስለ ታላቅ ጦርነትም የሚገልፅ ነበር፡፡ መልእክቱንም ይገነዘብ ዘንድ በራዕዩ ማስተዋል ተሰጠው፡፡
2በዚያ ጊዜ እኔ ዳንኤል ለሦስት ሳምንት አለቀስኩ፤
3ሦስቱም ሳምንት እስኪፈፀም ድረስ ጥሩ ምግብ አልበላሁም፤ ስጋም ሆነ የወይን ጠጅ ወደ አፌ አልገባም፤ ቅባትም አልተቀባሁም፡፡
4በመጀመሪያው ወር አያ አራተኛው ቀን፤ በታላቁ በጤግሮስ ወንዝ ዳር ቆሜ፤
5ቀና ብዬ ስመለከት፣ በፊቴ በፍታ የለበሰ እና በወገቡም ላይ ምርጥ የወርቅ ቀበቶ የታጠቀ አንድ ሰው አየሁ፡፡
6አካሉ እንደ እንቁ፣ ፊቱ እንደ መብረቅ፣ ዐይኖቹ እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹ እንደ ጋለ ናስ የሚያብረቀርቁ ድምፁም እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበር፡፡
7ራዕዩን ያየሁት እኔ ዳንኤል ብቻ ነበርሁ፤ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች አላዩም፤ ነገር ግን ታላቅ ፍርሃት ስለ ወደቀባቸው ሸሽተው ተደበቁ፡፡
8ስለዚህ ይህን ታላቅ ራዕይ እያየሁ ብቻዬን ቀረሁ፤ ምንም ጉልበት አልነበረኝም፤ መልኬ እጅጉን ገረጣ፤ ኃይልም አጣሁ፡፡
9ከዚያም የቃሉን ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ፣ በግንባሬ በምድር ላይ ተደፍቼ በከባዱ እንቅልፍ ተኛሁ፡፡
10እነሆም አንድ እጅ ዳሰሰኝ፤ እየተንቀጠቀጥሁም በእጄና በጉልበቴ አቆመኝ፤
11እርሱም፤ “ እጅግ የተወደድህ ዳንኤል ሁይ፣ አሁን ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን አስተውል፤ ቀጥ ብለህም ቁም አለኝ፡፡ ይህን ሲለኝም፤ እየተንቀጠቀጥሁ ተነስቼ ቆምሁ፡፡
12ደግሞም እንዲ አለኝ፤ “ዳንኤል ሁይ፣ አትፍራ ማስተዋልን ለማግኘትና በአምላክህም ፊት ራስህን ለማዋረድ ከወሰንክበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ ቃልህ ተሰምቷል፤ እኔም የቃልህን መልስ ይዤ መጥቻለሁ፡፡
13ነገር ግን የፋርስ መንግስት አለቃ ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል ሊረዳኝ ወጣ፡፡
14ራዕዩ ሊፈፀም ገና ብዙ ዘመን ስለሚቀረው ወደፊት በህዝብህ ላይ የሚሆነውን ልገልፅልህ አሁን ወደአንተ መጥቻለሁ፡፡”
15ይህን እየተናገረኝ ሳለ፣ ፊቴን ወደ ምድር አቀረቀርሁ፣ የምናገረውንም አጣሁ፡፡
16ከዛም የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሮቼን ዳሰሰ፣ እኔም አፌን ከፈትኩ፣ መናገርም ጀመርኩ፤ በፊቴ የነበረውንም እንዲህ አልኩት፤ “ ጌታዬ ሆዬ ከራዕዩ የተነሳ ተሰቃይቻለሁ ሃይልም አጣሁ፤
17ጉልቤቴ ከዳኝ፤ መተንፈስም አቅቶኛል፣ እኔ አገልጋይህ ከአንተ ጋር መነጋገር እንዴት እችላለሁ?”
18እንደገናም ሰው የሚመስለው ዳሰሰኝ አበረታኝም፡፡
19እርሱም፤ “እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፤ አትፍራ፤ ሰላም ላንተ ይሁን፤ በርታ፤ ፅና” አለኝ፡፡ እየተናገረኝም ሳለ፣ በረታሁና፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አበረትተኸኛልና ተናገር” አልሁት፡፡
20እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ለምን ወደ አንተ እንደ መጣሁ ታውቃለህ? የፋርስን መንግሥት ለመውጋት እመለሳለሁ፤ እኔም ስሄድ የግሪክ አለቃ ይመጣል።
21አስቀድሜ ግን በእውነት መጽሐፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ ከእነዚህ አለቆች ጋር ለመዋጋት ከአለቃችሁ ከሚካኤል በስተቀር የሚረዳኝ የለም።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።