1ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት ሰዎች እንዲሁም ፊቴን በሥጋ አይተውት ስለማያውቁ ስለ ብዙዎች ምን ያህል ብርቱ ትግል እንዳደረግሁ እንድታውቁ እወዳለሁ።
2ልባቸው ተጽናንቶና በፍቅር ተሳሰረው ፍጹም የሆነ የመረዳት ብልጽግና እንዲኖራቸውና የእግዚአብሔርን ምስጢር የሆነውን እውነት ክርስቶስን እንዲያውቁ እታገላለሁ።
3የጥበብና የዕውቀት ሀብት ሁሉ የተሰወረው በእርሱ ነው።
4ይህን የምላችሁ ማንም በሚያታልል ንግግር እንዳያስታችሁ ነው።
5በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን እንኳ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ። የእናንተን መልካም ሥርዐትና በክርስቶስ ያላችሁን ጽኑ እምነት እያየሁ ደስ ይለኛል።
6ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ።
7በእርሱም ተመሥርታችሁና ታንጻችሁ፤ እንደ ተማራችሁትም በእምነት ተደላድላችሁ ኑሩ፤ ምስጋናም ይብዛላችሁ።
8በክርስቶስ ላይ ባልተመሠረተ በሰው ሠራሽ ልማድና በዓለማዊ ነገሮች፥ በፍልስፍናና በከንቱ ሽንገላ ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠንቀቁ።
9የእግዚአብሔር ፍጹም ሙላት በእርሱ ይኖራልና።
10በእርሱም ተሞልታችኋል። እርሱ የአለቅነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ ነው።
11በእርሱም ተገርዛችኋል፤ ይህም መገረዛችሁ የሥጋዊ አካል በማስወገድ በሰው እጅ የተደረገ ሳይሆን በክርስቶስ የተደረገ ነው።
12በተጠመቃችሁ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ተቀበራችሁ፤በእርሱም ክርስቶስን ከሞት ባስነሣው በእግዚአብሔር ኅይል በእምነት ተነሥታችኋል።
13እናንተም በበደላችሁና በሥጋችሁ ባለመገረዝ ሙታን ሳላችሁ፤ እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን አድርጎ መተላለፋችንንም ሁሉ ይቅር ብሎአል።
14እርሱ ይከሰን የነበረውን የዕዳ ጽሑፍ ደመሰሰው። ሁሉንም በመስቀል ላይ ቸንክሮ ከእኛ አስወገደው።
15ኅይላትንና ባለሥልጣናትን በመስቀሉ ድል አድርጎ በይፋ እንዲጋለጡ አደረጋቸው።
16እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም የበዓላትን ቀናት ወይም የወር መባቻን፤ ወይም ሰንበትን በማክበር ምክንያት ማንም አይፍረድባችሁ።
17እነዚሁ ሁሉ ወደ ፊት ሊመጡ ላሉት ነገሮች እንደ ጥላ ናቸው፤ እውነተኛው አካል ግን በክርስቶስ ነው።
18አስመሳይ በሆነ ትሕትና የመላእክትን አምልኮ በመፈለግ ማንም ዋጋ እንዳያሳጣችሁ። እንዲህ ያለው ሰው ስለሚያየው ነገር በሥጋዊ አስተሳሰቡ ይታበያል።
19እርሱም ራስ ከሆነ ከክርስቶስ ጋር አልተያያዘም። በእግዚአብሔር በተሰጠው እድገት በመገጣጠሚያና በጅማት አካልን በሙሉ አያይዞ የሚመግበውና ለአካል ሙሉ ዕድገት የሚሰጠው ራስ ነው።
20ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፣ ለዓለማዊ ነገሮች እየታዘዛችሁ ስለ ምን ትኖራላችሁ? ትእዛዞቹም፦
21«አትያዝ፤አትቅመስ፤ አትንካ!» የሚሉ ናቸው።
22እነዚህ ሁሉ የሰው ትእዛዛትና ትምህርቶች ሥራ ላይ ከዋሉ በኋላ የሚጠፉ ናቸው።
23እነዚህ ትእዛዞች ሰው ሰራሽ «ጥበብ» አምልኮና የሐሰት ትሕትና ሰውነትንም በማጎሳቆል ላይ የሚያተኩሩ፤ ነገር ግን ሥጋዊ ስሜትን በመቆጣጠር ረገድ ዋጋ ቢሶች ናቸው።