1ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ። እነሆ፥የጸደይ አዝመራ መብቀል በሚጀምርበት ጊዜ የአንበጣን መንጋ ፈጠረ፥ ተመለከትሁም፥ ከንጉሥ አጨዳ በኋላ ዘግይቶ የበቀለ አዝመራ ነበር።
2የምድሪቱን ሣር በልተው ከጨረሱ በኋላ፤ «ጌታ እግዚአብሔር ሆይ እባክህ ይቅር በል፥ ያዕቆብ በዚህ ውስጥ እንዴት ይቆማል? እርሱ ታናሽ ነውና» አልሁ።
3እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ «ይህ አይሆንም» አለ።
4ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፦እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ለመፍረድ ጠራ። እርሱም በምድር ውስጥ የሚገኘውን ሰፊና ጥልቅ ውኃ አደረቀ፥ ምድሪቱንም ደግሞ በላ።
5እኔ ግን፦«ጌታ እግዚአብሔር ሆይ እባክህ ተው፥ያዕቆብ በዚህ ውስጥ እንዴት ይቆማል? እርሱ ታናሽ ነውና» አልሁ።
6እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ «ይህም ደግሞ አይሆንም» ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
7እንዲህም አሳየኝ፦ እነሆም ፥ጌታ በእጁ ቱምቢ ይዞ በቅጥሩ አጠገብ ቆሞ ነበር።
8እግዚአብሔርም፦ «አሞጽ ምን ታያለህ?» አለኝ፥ እኔም «ቱምቢ» አልሁኝ። ከዚያም ጌታ፦«ተመልከት፥በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱምቢ አኖራለሁ። ከእንግዲህም ወዲያ አልምራቸውም።
9የይስሐቅ ከፍታ ቦታዎች ይጠፋሉ፥ የእስራኤል መቅደሶች ይፈርሳሉ፥ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሳለሁ።»
10ከዚያም የቤቴል ካህን አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፦«አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል በአንተ ላይ እያሤረ ነው። ምድሪቱም ቃሎቹን ልትሸከም አትችልም።
11አሞጽ እንዲህ ሲል ተናግሮአል፦'ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፥ እስራኤልም በእርግጥ ከምድሩ ተማርኮ ይሄዳል'።»
12አሜስያስም፥ አሞጽን እንዲህ አለው፦«ባለ ራዕዩ ሆይ፥ ወደ ይሁዳ ምድር ተመልሰህ ሽሽ፥ በዚያም እንጀራ ብላ ትንቢትም ተናገር።
13ነገር ግን ቤቴል የንጉሡ መቅድስና የመንግሥት መኖሪያ ነውና ከእንግዲህ ወድያ በዚህ ትንቢት አትናገር።»
14ከዚያም አሞጽ አሜስያስን እንዲህ አለው፦ «እኔ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም። እኔ እረኛና የዋርካ ዛፎች ጠባቂ ነኝ።
15ነገር ግን እግዚአብሔር የበግ መንጋ ከመጠበቅ ወሰደኝና እንዲህ አለኝ፦'ሂድ፥ ለሕዝቤ ለእስራኤል ትንቢት ተናገር።'
16አሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስማ። አንተ፥ «'በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፥ በይስሐቅም ቤት ላይ አትናገር' ትላለህ።
17ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦' ሚስትህ በከተማይቱ ውስጥ ሴተኛ አዳሪ ትሆናለች፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ምድርህ እየተለካ ይከፋፈላል፥ በረከሰ ምድር ትሞታለህ፥ እስራኤልም በእርግጥ ከምድሩ ተማርኮ ይጋዛል።»