መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 9

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሳውል ግን በጌታ ደቀ መዛሙርት ላይ ለግድያም እንኳ እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደ፤
2የጌታን መንገድ ከሚከተሉት ወንዶችም ሆነ ሴቶች ቢያገኝ፣ ወደ ኢየሩሳሌም አስሮ እንዲያመጣቸው፣ ለምኵራቦች ደብዳቤ እንዲሰጠውም ሊቀ ካህናቱን ጠየቀ።
3እየሄደ ሳለ ደማስቆ አጠገብ ሲደርስ፣ በድንገት ከሰማይ ብርሃን በዙሪያው በራበት፤
4በምድር ላይ ወደቀ፤ “ሳውል፣ ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ” የሚል ድምፅ ሰማ።
5ሳውልም፣ "ጌታ ሆይ፣ ማን ነህ?" ብሎ መለሰ፤ ጌታም፣ “አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ፤
6ነገር ግን ተነሥተህ ወደ ከተማው ግባ፤ ማድረግ ያለብህም ይነገርሃል” አለ።
7ከዚያም ከሳውል ጋር የተጓዙት ሰዎች ድምፁን እየሰሙ፣ ማንንም ግን ሳያዩና ሳይነጋገሩ ቆሙ።
8ሳውል ከወደቀበት ተነሣ፤ ዐይኑን ሲከፍትም ምንም ማየት አልቻለም፤ ስለዚህም በእጅ እየመሩ ወደ ደማስቆ አስገቡት።
9ሦስት ቀን ዕውር ሆኖ ቆየ፤ አልበላም አልጠጣምም።
10በዚያ ጊዜ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር በደማስቆ ነበር፤ ጌታም ለእርሱ በራእይ፣ “ሐናንያ” አለው። እርሱም፣ “ጌታ ሆይ፣ እነሆኝ” አለ።
11ጌታም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ተነሥና ቀጥተኛ ወደሚባለው ጎዳና ሂድ፤ በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚባል የጠርሴስ ሰውን ፈልግ፤ እርሱ እዚያ እየጸለየ ነውና፤
12እርሱ እንዲያይ ሐናንያ የሚባል ሰው ሲገባና በእርሱ ላይ እጁን ሲጭንበት በራእይ አይቶአል።”
13ሐናንያም መልሶ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፣ ስለዚህ ሰው በኢየሩሳሌም ባሉት ሕዝብህ ላይ ምን ያህል ክፋት እንደ ፈጸመባቸው ከብዙዎች ሰምቻለሁ።
14ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከሊቀ ካህናቱ ሥልጣን ተቀብሎአል።”
15ጌታ ግን መልሶ እንዲህ አለው፤ “ሂድ፤ እርሱ በአሕዛብ፣ በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት ስሜን ለመሸከም የተመረጠ ዕቃየ ነውና፤
16ስለ ስሜ ሲል ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበትም አሳየዋለሁና።
17ስለዚህ ሐናንያ ሄደ፤ ወደ ቤትም ገባ፤ እጁን በሳውል ላይ በመጫንም፣ “ወንድሜ ሳውል ሆይ፣ ስትመጣ በመንገድ ላይ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ እንድታይና መንፈስ ቅዱስን እንድትሞላ ወዳንተ ልኮኛል።”
18ወዲያው እንደ ቅርፊት ያለ ነገር ከሳውል ዐይን ወደቀ፤ ማየትም ጀመረ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤
19በላ፣ በረታም። ሳውል በደማስቆ ውስጥ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብዙ ቀን ቆየ።
20ወዲያውም ኢየሱስን የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በምኵራብ ውስጥ ዐወጀ።
21የሰሙትም ሁሉ በመደነቅ እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ያጠፋው አይደለምን? የመጣውም አስሮ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሊያቀርባቸው ነው።”
22ሳውል ግን ለመስበክ በረታ፣ በደማስቆ ይኖሩ የነበሩ አይሁድንም ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን በማረጋገጥ ግራ አጋባቸው።
23ከብዙ ቀን በኋላ፣ አይሁድ ሊገድሉት ዐሰቡ።
24ሳውል ግን ዐሳባቸውን ዐወቀባቸው። ሊገድሉት የከተማይቱን በሮች ቀንም ሌሊትም ይጠብቁ ነበር።
25ደቀ መዛሙርቱ ግን በግድግዳው በኩል በቅርጫት አወረዱት።
26ሳውል ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ በመጣ ጊዜ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመገናኘት ሞከረ፤ ነገር ግን ደቀ መዝሙር መሆኑን በመጠራጠር ሁሉም ፈሩት።
27ይሁን እንጂ፣ በርናባስ ወስዶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ አቀረበው። ሳውል ጌታን በመንገድ ላይ እንዴት እንዳየው፣ ጌታም እንደ ተናገረው፣ በኢየሱስ ስም ደማስቆ ውስጥ በድፍረት እንዴት እንደ ሰበከም ነገራቸው።
28ሳውል ኢየሩሳሌም ውስጥ ሲገባና ከዚያም ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተገናኘ። በጌታ ኢየሱስ ስም በድፍረት ተናገረ፤
29ከግሪክ አይሁድ ጋርም ተከራከረ፤ ሊገድሉት ሙከራ ማድረጋቸውን ግን አላቋረጡም።
30ወንድሞች ስለዚህ ባወቁ ጊዜ፣ ወደ ቂሣርያ አውርደው ወደ ጠርሴስ ላኩት።
31ከዚያም በኋላ የይሁዳ ሁሉ፣ የገሊላና የሰማርያ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ነበራት፣ ታነጸችም፤ እግዚአብሔርን በመፍራትና በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት ቤተ ክርስቲያን በቍጥር አደገች።
32ጴጥሮስም በየቦታው ሲዘዋወር፣ በልዳ ከተማ ወደሚኖሩ ቅዱሳንም ወረደ።
33እዚያም፣ ሽባ በመሆኑ ስምንት ዓመት የአልጋ ቊራኛ የነበረን ኤንያ የሚባለውን አንድ ሰው አገኘ።
34ጴጥሮስ፣ “ኤንያ ሆይ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሥና ዐልጋህን አንጥፍ” አለው። ወዲያውም ተነሣ።
35በልዳና በሰሮና የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ሰውየውን አዩትና ወደ ጌታ ተመለሱ።
36በኢዮጴም ጣቢታ የምትባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበረች፤ የስሟ ትርጕም “ዶርቃ” ማለት ነው። ይች ሴት በመልካም ምግባርና ለድኾች በምታደርጋቸው የርኅራኄ ሥራዎች የተሞላች ነበረች።
37በዚያም ወቅት ታመመችና ሞተች፤ ዐጥበውም ሰገነት ላይ አስቀመጧት።
38ልዳ በኢዮጴ አጠገብ በመሆኑና ደቀ መዛሙርቱም የጴጥሮስን በዚያ መኖር ስለ ሰሙ፣ “ሳትዘገይ ወደ እኛ ና” ብለው በመለመን ሁለት ሰዎችን ወደ እርሱ ላኩ።
39ጴጥሮስም ተነሣና ከተላኩት ጋር ሄደ። እዚያ ሲደርስ፣ ወደ ሰገነቱ አወጡት። መበለታቱም ሁሉ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር ሳለች ትለብሳቸው የነበሩትን ቀሚሶችና ልብሶች እያሳዩትና እያለቀሱ በአጠገቡ ቆሙ።
40ጴጥሮስ ሁሉንም ከክፍሉ አስወጣቸውና ተንበርክኮ ጸለየ፤ ከዚያም ወደ አስከሬኑ በመዞር፣ “ጣቢታ ሆይ፣ ተነሺ” አለ። ዐይኖቿን ከፈተች፤ ጴጥሮስንም ስታየው ተነሥታ ተቀመጠች።
41ጴጥሮስም እጇን ይዞ አነሣት፤ አማኞችንና መበለታቱን ጠርቶም በሕይወት እንዳለች ሰጣቸው።
42ይህ ጉዳይ በመላው ኢዮጴ የታወቀ ሆነ፤ ብዙ ሰዎችም በጌታ አመኑ።
43ጴጥሮስ በኢዮጴ ቍርበት ፋቂ ከነበረ ስምዖን ከሚባል ሰው ጋር ብዙ ቀን ቆየ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።