መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 8

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሳውል በእስጢፋኖስ ሞት ተስማምቶ ነበር። በዚያም ጊዜ በኢየሩሳሌም በነበረችዋ ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ተነሣ፤ አማኞችም ሁሉ ከሐዋርያት በቀር በይሁዳና በሰማርያ ተበታተኑ።
2በመንፈሳዊ ነገር የተጉ ሰዎች እስጢፋኖስን ቀበሩት፤ መሪር ልቅሶም አለቀሱለት።
3ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን በጣም ጐዳ፤ ከቤት ወደ ቤት በመሄድም ክርስቲያን ወንዶችንና ሴቶችን ጐትቶ አወጣቸው፤ ወኅኒ ቤት ውስጥም አስገባቸው።
4የተበታተኑት አማኞች ግን ቃሉን እየሰበኩ በየቦታው ዞሩ።
5ፊልጶስ ወደ ሰማርያ ከተማ ወረደ፣ ለሕዝቡም ክርስቶስን ሰበከላቸው።
6እጅግ ብዙ ሰዎች ፊልጶስን ሲሰሙትና ያደረጋቸውንም ምልክቶች ሲያዩ፣ በአንድነት እርሱ ለተናገረው ትኵረት ሰጡ።
7ምክንያቱም ከብዙ ሰዎች ርኩሳን መናፍስት እየጮኹ ወጥተው፣ አያሌ ሽባዎችና ዐንካሶችም ተፈውሰው ነበር።
8ስለዚህ በዚያች ከተማ ውስጥ ብዙ ደስታ ነበር።
9ነገር ግን በዚያች ከተማ ውስጥ ቀደም ሲል የጥንቈላ ሥራ ይሠራ የነበረ ሲሞን የሚባል ሰው ነበረ፤ ተፈላጊ ሰው እንደ ሆነ እየተናገረ የሰማርያን ሰዎች ያስደንቅ ነበር።
10ሳምራውያን በሙሉ ከትንሹ እስከ ትልቁ፣ “ይህ ሰው ታላቅ የሚባለው የእግዚአብሔር ኀይል ነው” እያሉ በሚገባ ያደምጡት ነበር።
11በጥንቈላ ሥራው ለረጅም ጊዜ ያስገርማቸው ስለ ነበር አደመጡት።
12ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ፊልጶስ የሰበከውን ወንጌል ሲያምኑ ግን ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ።
13ሲሞንም ደግሞ አመነ፤ ከተጠመቀም በኋላ ከፊልጶስ ጋር መሆንን ቀጠለ፤ የተደረጉ ምልክቶችንና ታላላቅ ተኣምራትን ባየ ጊዜም ተደነቀ።
14በኢየሩሳሌም የነበሩ ሐዋርያት ሰማርያ የእግዚአብሔርን ቃል የተቀበለች መሆኗን ሲሰሙ፣ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላኩላቸው።
15እነርሱም እዚያ ወርደው መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ጸለዩላቸው።
16መንፈስ ቅዱስ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በማንኛቸውም ላይ አልወረደም ነበርና፣ እነርሱ በጌታ ኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር።
17ከዚያም ጴጥሮስና ዮሐንስ እጃቸውን ጫኑባቸው፣ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ።
18በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጥ ሲያይ፣ ሲሞን ገንዘብ አቀረበላቸው።
19“እኔም እጁን የምጭንበት ሰው ሁሉ መንፈስ ቅዱስን መቀበል እንዲችል ይህን ሥልጣን ስጡኝ” አላቸው።
20ነገር ግን ጴጥሮስ እንዲህ አለው፤ “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ ለማግኘት አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ።
21ልብህ ለእግዚአብሔር የቀና አይደለምና በዚህ ጉዳይ ውስጥ ዕድል ወይም ድርሻ የለህም።
22እንግዲህ ለዚህ ክፋትህ ንስሓ ግባ፤ ምናልባትም ለልብህ ዐሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ጌታን ለምን።
23በኀጢአት እስራትና በመራርነት መርዝ ውስጥ እንዳለህ አያለሁና።”
24ሲሞንም መልሶ፣ “ከተናገራችኋቸው አንዱም በእኔ ላይ እንዳይፈጸም ወደ ጌታ ጸልዩልኝ” አላቸው።
25ጴጥሮስና ዮሐንስ ከመሰከሩና የጌታን ቃል ከተናገሩ በኋላ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በመንገድም ለብዙ የሰማርያ መንደሮች ወንጌልን ሰበኩ።
26የጌታ መልአክ ፊልጶስን፣ “ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ተነሥና ሂድ” አለው። (ይህ መንገድ በበረሓ ውስጥ ነው።)
27እርሱም ተነሣና ሄደ። እነሆ፣ በኢትዮጵያውያን ንግሥት በሕንደኬ ሥር ትልቅ ሥልጣን የነበረው አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ነበረ። ሰውዬው በንግሥቲቱ ንብረት ሁሉ ላይ ኀላፊነት ነበረው። ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር።
28ከኢየሩሳሌም በመመለስ ላይ ሳለ፣ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ትንቢተ ኢሳይያስን እያነበበ ነበር።
29መንፈስ ፊልጶስን፣ “ሂድ ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው።
30ፊልጶስ ወደ ጃንደረባው ሮጠ፣ ትንቢተ ኢሳይያስንም ሲያነብ ሰማው፤ “የምታነበውን ትረዳዋለህ?” አለው።
31ኢትዮጵያዊውም፣ “የሚመራኝ ከሌለ እንዴት ልረዳው እችላለሁ?” አለው። ወደ ሠረገላው እንዲወጣና ዐብሮት እንዲቀመጥ ፊልጶስን ለመነው።
32ኢትዮጵያዊው ያነበው የነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይህ ነው፦ “እንደ በግ ለመታረድ ተነዳ፤ በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል ጠቦት፣ አፉን አልከፈተም፤
33በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ትውልዱን ማን ይናገራል? ሕይወቱ ከምድር ተወግዶአልና።”
34ጃንደረባው ፊልጶስን፣ “እባክህ ነቢዩ ስለ ማን ነው የሚናገረው? ስለ ራሱ ወይስ ስለ ሌላ ነው?” አለው።
35ፊልጶስም መናገር ጀመረ፤ ከዚህም ከኢሳይያስ መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ሰበከው።
36እየሄዱ ሳሉ ውሃ አለበት ዘንድ ደረሱ፤ ጃንደረባው፣ “ተመልከት፣ እዚህ ውሃ አለ፤ እንዳልጠመቅ ምን ይከለክለኛል?” አለ።
37ፊልጶስም፣ “በፍጹም ልብህ ካመንህ፣ መጠመቅ ትችላለህ” አለ። ኢትዮጵያዊውም መልሶ፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ” አለ።
38ኢትዮጵያዊው ሠረገላው እንዲቆም አዘዘና፣ ፊልጶስም ጃንደረባውም ወደ ውሃው ወረዱ፤ ፊልጶስም አጠመቀው።
39ከውሃው ውስጥ ሲወጡ፣ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ወሰደው፤ ጃንደረባውም ከዚያ ወዲያ አላየውም፤ ደስ ብሎትም ጕዞውን ቀጠለ።
40ነገር ግን ፊልጶስ በአዛጦን ታየ። በዚያ አገር ውስጥ በማለፍ ቂሣርያ እስኪደርስ ድረስ፣ ለከተሞች ሁሉ ወንጌልን ሰበከ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።