1በቂሣርያ ከተማ ውስጥ የኢጣሊቄ ክፍለ ሰራዊት በሚባል የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚባል ሰው ነበረ።
2እርሱም መንፈሳዊ፣ ከቤተ ሰቡ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክ፣ ለአይሁድ ብዙ ገንዘብ የሚሰጥና ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር የሚጸልይ ሰው ነበረ።
3ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲመጣ በራእይ በግልጽ ታየው። መልአኩ፣ “ቆርኔሌዎስ!” አለው።
4ቆርኔሌዎስ መልአኩን አተኵሮ ተመለከተውና ፈርቶ እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ ሆይ፣ ይህ ምንድን ነው?” መልአኩም መልሶ፣ “ጸሎትህና ምጽዋትህ በመታሰቢያነት ወደ እግዚአብሔር ደርሶአል።
5ጴጥሮስም ተብሎ የሚጠራውን ስምዖን የሚባለውን ሰውየ ለማስመጣት አሁን ወደ ኢዮጴ ከተማ ሁለት ሰዎችን ላክ።
6ሰውየው ቤቱ በባሕሩ አጠገብ ከሚገኝ ስምዖን ከሚባለው ከቆዳ ፋቂው ጋር አለ” አለው።
7ያነጋግረው የነበረው መልአክ እንደ ሄደ፣ ቆርኔሌዎስ ከሚያገለግሉት ወታደሮች መካከል እግዚአብሔርን ያመልክ የነበረ አንድ ወታደርንና ከቤት አሽከሮቹ ሁለቱን ጠራ።
8ቆርኔሌዎስ የሆነውን ሁሉ ነግሮአቸው ወደ ኢዮጴ ላካቸው።
9በሚቀጥለው ቀን ስድስት ሰዓት አካባቢ፣ በጕዞ ላይ ሳሉና ወደ ከተማዋ ሲቃረቡ፣ ጴጥሮስ ሊጸልይ ወደ ሰገነቱ ወጣ።
10ራበውና አንዳች ነገር ለመብላት ፈለገ፤ ነገር ግን ሰዎች ምግብ በማዘጋጀት ላይ ሳሉ፣ በተመስጦ ውስጥ ገባ፤
11ሰማይ ተከፍቶ፣ ትልቅ ሸማ የሚመስል አንድ መያዣ በአራቱ ጠርዞቹ ተይዞ ወደ ምድር ሲወርድም አየ።
12በውስጡም አራት እግር ያላቸው እንስሳት ሁሉና በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራን፣ የሰማይ ወፎችም ነበሩበት።
13“ጴጥሮስ ሆይ፣ ተነሥና ዐርደህ ብላ” የሚል ድምፅ ለጴጥሮስ መጣ።
14ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፣ አይሆንም፤ ምክንያቱም እኔ ርኩስና አስጸያፊ የሆነ ምንም ነገር ፈጽሞ በልቼ አላውቅም” አለ።
15እንደገናም ድምፅ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ጴጥሮስ መጣ፤ “እግዚአብሔር ቅዱስ ያደረገውን ርኩስ ብለህ አትጥራው” የሚል ድምፅ።
16ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፤ ከዚያም መያዣው ወዲያው ወደ ሰማይ ተመልሶ ተወሰደ።
17ጴጥሮስ ያየው ራእይ ምን ትርጕም ሊኖረው እንደሚችል በጣም ግራ ገብቶት ሳለ፣ ወደ ቤት የሚያስሄደውን መንገድ ጠይቀው ካገኙ በኋላ እነሆ፣ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች በበሩ ፊት ለፊት ቆሙ።
18ድምፃቸውን ከፍ በማድረግም ጴጥሮስ የሚባለው ስምዖን በዚያ መኖሩንና አለመኖሩን ጠየቁ።
19ጴጥሮስ ስለ ራእዩ በማሰብ ላይ ሳለ፣ መንፈስ ቅዱስ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፣ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል።
20ተነሥና ውረድ፤ ከእነርሱም ጋር ሂድ። ዐብረሃቸው ለመሄድ አትፍራ፤ ምክንያቱም የላክኋቸው እኔ ነኝ።”
21ስለዚህም ጴጥሮስ ወደ ሰዎቹ ወርዶ፣ “የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ። የመጣችሁት ለምንድን ነው?” አላቸው።
22እነርሱም እንዲህ አሉት፤ "እግዚአብሔርን የሚያመልክ፣ በአይሁድ ሕዝብ ሁሉ ዘንድም የተመሰገነ ቆርኔሌዎስ የሚባል ጻድቅ ሰው፣ ወደ ቤቱ ሰው ልኮ እንዲያስመጣህ የእግዚአብሔር መልአክ ነገረው፤ እንዲህ ያደረገውም ከአንተ መልእክትን መስማት እንዲችል ነው።”
23ጴጥሮስም እንዲገቡና ከእርሱና ዐብረውት ከነበሩ ሰዎች ጋር እንዲቈዩ በእንግድነት ተቀበላቸው። በማግስቱ ጧት ጴጥሮስ ተነሣና ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ በኢዮጴ ከነበሩት ወንድሞችም አንዳንዶቹ ዐብረውት ሄዱ።
24በሚቀጥለው ቀን ቂሣርያ ደረሱ። ቆርኔሌዎስ እየጠበቃቸው ነበር፤ ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹንም ጠርቶ እንዲሰበሰቡ አደረገ።
25ጴጥሮስ ሲገባ፣ ቆርኔሌዎስ አግኝቶት እግሩ ላይ ወድቆ ሰገደለት።
26ነገር ግን ጴጥሮስ አነሣውና፣ “ተነሥ ቁም፤ እኔ ራሴም ሰው ነኝ” አለው።
27ጴጥሮስ ከቆርኔሌዎስ ጋር እየተነጋገረ ወደ ውስጥ ሲገባ፣ የተሰበሰቡ ብዙ ሰዎችን አገኘ።
28እንዲህም አላቸው፤ "አይሁዳዊ የሆነ ሰው ከሌላ ሕዝብ ከሆነ ጋር መገናኘት ወይም እርሱን መጎብኘት በሕግ እንደማይፈቀድለት እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። ነገር ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኩስ ወይም አስጸያፊ ብዬ መጥራት እንደማይገባኝ ለእኔ አሳይቶኛል።
29ሲላክብኝ ሳልከራከር የመጣሁት ከዚህ የተነሣ ነው። ስለዚህ ለምን እንደ ላካችሁብኝ እጠይቃችኋለሁ።"
30ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለ፤ “ከአራት ቀን በፊት ልክ በዚህ ሰዓት በዘጠኝ ሰዓት በቤቴ ውስጥ እጸልይ ነበር፤ እነሆም ነጭ ልብስ ለብሶ ፊት ለፊቴ ቆመና፣
31‘ቆርኔሌዎስ ሆይ፣ ጸሎትህ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰምቶአል፤ ምጽዋትህም መታሰቢያ ሆኖልሃል።
32ስለዚህ ወደ ኢዮጴ ሰው ላክና ጴጥሮስም የሚባለውን ስምዖንን ወደ አንተ ጠርተህ አስመጣ። እርሱ በቆዳ ፋቂው በስምዖን ቤት በባሕር አጠገብ ተቀምጦአል’ አለኝ።
33ስለዚህ ወዲያው ላክሁብህ። አሁን መምጣትህ መልካም አደረግህ። አሁን እንግዲህ እኛ ሁላችን እግዚአብሔር እንድትናገር ያዘዘህን ሁሉ ለመስማት በእግዚአብሔር ፊት እንገኛለን።"
34ጴጥሮስም እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በእውነት ተገንዝቤአለሁ።
35ይልቁን በማንኛውም ሕዝብ ውስጥ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ የጽድቅ ተግባራትንም የሚፈጽም ሁሉ በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።
36እግዚአብሔር በሁሉ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሰላምን የምሥራች ባወጀበት ጊዜ፣ ወደ እስራኤል ሕዝብ የላከውን መልእክት ታውቃላችሁ፦
37ዮሐንስ ካወጀው ጥምቀት በኋላ፣ በገሊላ በመጀመር በይሁዳ ሁሉ የታዩትን የተፈጸሙ ሁነቶችን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤
38ሁነቶቹም እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስና በኀይል እንዴት እንደ ቀባው የናዝሬቱን ኢየሱስን የሚመለከቱ ናቸው። ኢየሱስ መልካም እያደረገና ለዲያብሎስ የተገዙትን እየፈወሰ ዞረ፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና።
39በዕንጨት ላይ ሰቅለው የገደሉት ይህ ኢየሱስ ከአይሁድ አገርም በኢየሩሳሌምም ለፈጸማቸው ተግባራት ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን።
40ይህን ሰው እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው፤ እንዲገለጥም አደረገው፤
41ይኸውም እግዚአብሔር አስቀድሞ መርጦአቸው ለነበሩ ምስክሮች እንጂ፣ ለሕዝቡ ሁሉ አይደለም፦ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ዐብረነው የበላንና የጠጣን እኛው ራሳችን ነን።
42ለሕዝቡ እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ላይ እንዲፈርድ፣ እግዚአብሔር የመረጠው ይህ እንደ ሆነ እንድንመሰክር አዘዘን።
43በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኀጢአትን ይቅርታ እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ የሚመሰክሩት ስለ እርሱ ነው።”
44ጴጥሮስ እነዚህን ነገሮች ገና እየተናገረ ሳለ፣ መልእክቱን በሚሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው።
45ከተገረዙት ወገን የሆኑ አማኞች፦ ከጴጥሮስ ጋር የመጡትም ሁሉ ተደነቁ፤ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ በአሕዛብም ላይ ወርዶ ነበር።
46እነዚህ አሕዛብ በሌሎች ቋንቋዎች ሲናገሩና እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ሰምተዋቸዋልና። ከዚያም በኋላ ጴጥሮስ መልሶ፣
47“እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እነዚህ ሰዎች እንዳይጠመቁ ማን ውሃ ሊከለክላቸው ይችላል?” አለ።
48በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁም አዘዛቸው። ከዚያ በኋላ ከእነርሱ ጋር ጥቂት ቀን እንዲቈይ ጴጥሮስን ለመኑት።