መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 7

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሊቀ ካህናቱም፣ “እነዚህ ነገሮች እውነት ናቸውን?” አለ።
2እስጢፋኖስ እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “ወንድሞችና አባቶች ሆይ፣ አድምጡኝ፤ የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ከመኖሩ በፊት በመስጴጦምያ ሳለ ተገለጠለት፤
3እግዚአብሔርም፣ 'አገርህንና ዘመዶችህን ተውና እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ' አለው።
4ከዚያም በኋላ፣ ጊዜ አብርሃም ከከለዳውያን ምድር ወጥቶ በካራን ኖረ፤ ከዚያም፣ አባቱ ከሞተ በኋላ፣ እግዚአብሔር አሁን እናንተ ወደምትኖሩበት፣ ወደዚህ ምድር አመጣው።
5ከዚህ ምድር ምንም ርስት፣ የእግር ጫማ ለማሳረፍ የሚበቃ እንኳ አልሰጠውም። ነገር ግን አብርሃም ገና ልጅ ያልነበረው ቢሆንም እንኳ፣ እግዚአብሔር ምድሪቱን ርስት አድርጎ ለእርሱና ከእርሱ በኋላ ለዘሮቹ እንደሚሰጥ ቃል ገባ።
6እግዚአብሔር ለአብርሃም እንደዚህ እየተናገረው ነበር፤ ይኸውም ዘሮቹ ለተወሰነ ጊዜ በባዕድ ምድር እንደሚኖሩ፣ እዚያ ያሉ ኗሪዎችም በባርነት ውስጥ እንደሚያስገቧቸውና ለአራት መቶ ዓመታት እንደሚያስጨንቋቸው ነው።
7‘በባርነት የሚኖሩበትን ሕዝብም እፈርድበታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ይወጣሉ፤ በዚህም ስፍራ ያመልኩኛል’ አለ እግዚአብሔር።
8እግዚአብሔር ለአብርሃም የግዝረትን ኪዳን ሰጠው፤ አብርሃምም የይስሐቅ አባት ሆነ ይስሐቅንም በስምንተኛው ቀን ገረዘው፤ ይስሐቅ የያዕቆብ አባት ሆነ፤ ያዕቆብም የዐሥራ ሁለቱ አለቆች አባት።
9አለቆች በዮሴፍ ላይ በቅናት ተነሣሥተው ወደ ግብፅ ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ነበረ፤
10ከመከራውም ሁሉ አዳነው፤ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ፊትም ሞገስና ጥበብ ሰጠው። ፈርዖንም ዮሴፍን በግብፅና በቤቱ ባለው ሁሉ ላይ ገዥ አደረገው።
11በመላው ግብፅና በከነዓን ራብና ትልቅ ጭንቀት መጣ፤ አባቶቻችንም ምንም ምግብ አላገኙም።
12ነገር ግን ያዕቆብ እህል በግብፅ ውስጥ እንደ ነበረ ሲሰማ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ አባቶቻችንን ላካቸው።
13በሁለተኛው ጊዜ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን ገለጠ፤ የዮሴፍ ቤተ ሰብም ከፈርዖን ጋር ተዋወቀ።
14ከዘመዶቹ ሁሉ ጋር፣ ሰባ ዐምስት ሰዎች ሆኖ ወደ ግብፅ እንዲመጣ፣ ለአባቱ ለያዕቆብ እንዲነግሩ ዮሴፍ ወንድሞቹን መልሶ ላካቸው።
15ስለዚህ ያዕቆብ ወደ ግብፅ ወረደ፤ ከጊዜ በኋላም፣ እርሱና አባቶቻችን በዚያ ሞቱ።
16ወደ ሴኬም ተወስደውም አብርሃም በሴኬም ከኤሞር ልጆች በብር ገዝቶት በነበረው መቃብር ተቀበሩ።
17እግዚአብሔር ለአብርሃም ገብቶት የነበረው የተስፋ ቃል ጊዜ ሲቃረብ፣ ሕዝቡ በግብፅ ውስጥ በቍጥር እያደጉና እየበዙ ሄዱ፤
18በግብፅ ሌላ ንጉሥ፣ ስለ ዮሴፍ ያላወቀ ንጉሥ እስከ ተነሣ ድረስ።
19ይኸው ንጉሥ ሕዝባችንን አታለለ፤ አባቶቻችንንም አስጨነቀ፤ ሕዝቡም ሕፃናታቸውን በሕይወት እንዳይኖሩ ወደ ውጭ መጣል ነበረባቸው።
20በዚያ ጊዜ ሙሴ ተወለደ፤ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት በጣም ያማረ ነበር፤ በአባቱ ቤትም ሦስት ወር አደገ።
21ሙሴ ወንዝ ውስጥ ሲጣል፣ የፈርዖን ሴት ልጅ ወስዳ እንደ ልጇ አሳደገችው።
22ሙሴ በግብፃውያን ትምህርት ሁሉ የሠለጠነ፣ በንግግሩና በሥራውም ታላቅ ሰው ነበር።
23አርባ ዓመት ሲሆነው ግን ወንድሞቹን፣ የእስራኤልን ልጆች የመጐብኘት ዐሳብ ወደ ልቡ መጣ።
24አንድ እስራኤላዊ ሲጠቃ አይቶ፣ ሙሴ ተከላከለለት፤ ያጠቃውንም ግብፃዊ ተበቀለው፤
25ሙሴ በእርሱ እጅ እግዚአብሔር እያዳናቸው መሆኑን ወንድሞቹ ያስተውላሉ ብሎ ዐሰበ፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም።
26በሚቀጥለው ቀን ሙሴ እየተጣሉ ወደ ነበሩ እስራኤላውያን መጣ፤ እርስ በርስ ሊያስታርቃቸውም ሞከረ፤ ‘እናንተ ሰዎች ሆይ፣ ወንድማማቾች ናችሁ፤ እርስ በርስ ለምን ትጐዳዳላችሁ?’ አለ።
27ባልንጀራውን የጐዳው ግን ሙሴን ገፈተረው፤ እንደዚህም አለው፤ 'በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ ያደረገህ ማን ነው?
28ግብፃዊውን ትናንት እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?'
29ሙሴ ይህን ከሰማ በኋላ ሸሽቶ ሄደ፤ የሁለት ልጆች አባት በሆነበት በምድያም ምድር መጻተኛ ሆነ።
30አርባ ዓመት ሲያልፍ፣ በሲና ተራራ ምድረ በዳ፣ በቊጥቋጦ ውስጥ በእሳት ነበልባል መልአክ ታየው።
31ሙሴ እሳቱን ሲያይ፣ በሚታየው ተደነቀ፤ ሊመለከተው ሲቀርብም፣ እንዲህ የሚል የጌታ ድምፅ መጣ፤
32‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ ነኝ።’ ሙሴ ተንቀጠቀጠ፣ መመልከትም አልቻለም።
33ጌታም ለሙሴ እንዲህ አለው፤ ‘የቆምህበት ስፍራ ቅዱስ ነውና ጫማህን አውልቅ።
34በግብፅ ውስጥ ያሉትን የሕዝቤን ሥቃይ በእርግጥ አይቻለሁ፤ የሥቃይ ጩኸታቸውን ሰምቻለሁ፤ ላድናቸውም ወርጃለሁና አሁን ና፤ ወደ ግብፅ እልክሃለሁ።’
35“በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ ያደረገህ ማን ነው?” ባሉት ጊዜ ተቀባይነትን ያሳጡት ይህ ሙሴ፦ እግዚአብሔር ገዥም ታዳጊም አድርጎ የላከው ነው። እግዚአብሔር ሙሴን በቊጥቋጦው ውስጥ በታየው መልአክ እጅ ላከው።
36በግብፅና በቀይ ባሕር፣ በአርባ ዓመታቱ ወቅትም በምድረ በዳ ተአምራትንና ምልክቶችን ካደረገ በኋላ፣ ሙሴ ሕዝቡን ከግብፅ አወጣቸው።
37‘እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል’ ብሎ ለእስራኤል ሕዝብ የተናገረው ያው ሙሴ ነው።
38ይህ ሰው ሲና ተራራ ላይ ያናግረው ከነበረው መልአክ ጋር በምድረ በዳው በጉባኤ ውስጥ የነበረ ሰው ነው። ሰው ከአባቶችችን ጋር ነበረ፤ ለእኛ ሊሰጥ ሕያው ቃልን የተቀበለ ሰውም ነው።
39ይህ አባቶቻችን ለመታዘዝ እንቢ ያሉት ሰው ነው፤ እነርሱም ገፉት፤ በልባቸውም ወደ ግብፅ ተመለሱ።
40በዚያ ጊዜ አሮንን እንዲህ አሉት፤ ‘የሚመሩንን አማልክት ሥራልን። ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ይህ ሙሴ፣ ምን እንዳጋጠመው አናውቅም።'
41ስለዚህ እስራኤላውያን በእነዚያ ቀኖች ጥጃ ሠርተው ለጣዖቱ መሥዋዕት አቀረቡ፤ ከእጆቻቸው ሥራ የተነሣም ደስ አላቸው።
42እግዚአብሔር ግን ዘወር አለ፤ የሰማይ ከዋክብትን እንዲያመልኩም አሳልፎ ሰጣቸው፤ በነቢያት መጽሐፍ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፣ አርባ ዓመት በምድረ በዳ፣ የታረዱ እንስሳትንና መሥዋዕቶችን አቀረባችሁልኝን?
43የሞሎክን ድንኳን፣ ሬምፉም የሚባለውን አምላክ ኮከብም፣ ልታመልኳቸው የሠራችኋቸውን ምስሎችም ተቀበላችሁ፤ እኔም ከባቢሎን ወዲያ እሰድዳችኋለሁ።’
44አባቶቻችን የምስክሩ ድንኳን በምድረ በዳ ነበራቸው፤ ይኸውም ባየው ምሳሌ መሠረት መሥራት እንዳለበት እግዚአብሔር ሙሴን ሲያናግረው እንዳዘዘው ያለ ነው።
45ይህ አባቶቻችን በተራቸው ከኢያሱ ጋር ወደ ምድሪቱ ያመጡት ድንኳን ነው። እግዚአብሔር በአባቶቻችን ፊት ባስወጣቸው አሕዛብ አገር ውስጥ ሲገቡ፣ ይህ ሆነ። እስከ ዳዊት ዘመን ድረስ እንደዚህ ነበር፤
46ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አገኘ፤ ለያዕቆብ አምላክም ማደሪያ ስፍራን ለማግኘት ለመነ።
47ነገር ግን ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤት ሠራለት።
48ይሁን እንጂ፣ ልዑሉ በእጅ በተሠሩ ቤቶች ውስጥ አይኖርም፤ ይህም ነቢዩ እንዲህ ብሎ እንደሚናገረው ነው፦
49ሰማይ ዙፋኔ፣ ምድርም የእግሬ መርገጫ ነው። ምን ዐይነት ቤት ልትሠሩልኝ ትችላላችሁ? ይላል ጌታ፤ ወይስ የማርፍበት ስፍራ የት ነው?
50እጄ እነዚህን ሁሉ አልሠራችምን?
51እናንተ ዐንገተ ደንዳኖች፣ ልባችሁንና ጆሮዎቻችሁን ያልተገረዛችሁ፣ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ፤ አባቶቻችሁ እንዳደረጉትም ታደርጋላችሁ።
52ከነቢያት የእናንተ አባቶች ያላሳደዱት የትኛው ነው? እነርሱ ከጻድቁ መምጣት ቀድመው የተናገሩ ነቢያትን ገድለዋል፤ እናንተም አሁን ጻድቁን የምትክዱና የምትገድሉ ሆናችኋል፤
53መላእክት ያጸኑትን ሕግ ብትቀበሉም አልጠበቃችሁትም።”
54አሁን የሸንጎው አባላት እነዚህን ነገሮች ሲሰሙ፣ በልባቸው እጅግ ተቈጡ፣ ጥርሳቸውንም በእስጢፋኖስ ላይ አፋጩ።
55እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ፣ ወደ ሰማይ አተኵሮ ተመለከተ፣ የእግዚአብሔርንም ክብር አየ፤ ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየው።
56እስጢፋኖስ፣ “እነሆ፣ ሰማያት ተከፍተው፣ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየሁ” አለ።
57የሸንጎው አባላት ግን በታላቅ ድምፅ ጮኹ፤ ጆሮአቸውንም በመድፈን በአንድነት እየሮጡ ወደ እስጢፋኖስ ሄዱ፤
58ከከተማው አውጥተውም በድንጋይ ወገሩት፤ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚባል አንድ ወጣት እግር አጠገብ አኖሩ።
59እስጢፋኖስን ሲወግሩት፣ ወደ እግዚአብሔር ይጣራ፣ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ነፍሴን ተቀበል” እያለ ይናገርም ነበር።
60ተንበረከከና በታላቅ ድምፅ፣ “ጌታ ሆይ፣ ይህን ኀጢአት አትቊጠርባቸው” ብሎ ጮኸ። ይህን ተናግሮም፣ አንቀላፋ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።