1በእነዚህ ወራት፣ የደቀ መዛሙርት ቊጥር እየበዛ በሄደ ጊዜ፣ ከግሪክ የመጡት አይሁድ በዕብራውያን ላይ ማጕረምረም ጀመሩ፤ ምክንያቱም መበለቶቻቸው በየዕለቱ የምግብ ዕደላ ላይ ቸል ተብለውባቸው ነበር።
2ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ደቀ መዛሙርቱን ሁሉ ጠርተው እንዲህ አሏቸው፤ “የምግብ አገልግሎትን ለመስጠት ብለን የእግዚአብሔርን ቃል መተው ለእኛ ተገቢ አይደለም።
3ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፣ በዚህ ኀላፊነት ላይ ልንሾማቸው የምንችል መልካም አርአያነት ያላቸውን፣ መንፈስና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ መካከል ምረጡ።
4እኛ ግን፣ ሁልጊዜ በጸሎትና በቃሉ አገልግሎት እንቀጥላለን።”
5ንግግራቸው ሕዝቡን ሁሉ ደስ አሰኘ። ስለዚህ እምነትና መንፈስ ቅዱስ የሞላበትን እስጢፋኖስን፣ ፊልጶስን፣ ጵሮኮሮስን፣ ኒቃሮናን፣ ጢሞናን፣ ጳርሜናንና ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረውን አንጾኪያዊውን ኒቆላዎስን መረጡ።
6አማኞቹ እነዚህን ሰዎች፣ በጸለዩላቸውና ከዚያም እጃቸውን በላያቸው በጫኑት በሐዋርያት ፊት አቀረቧቸው።
7ስለዚህም የእግዚአብሔር ቃል አደገ፤ የደቀ መዛሙርት ቊጥርም በኢየሩሳሌም ውስጥ በብዛት ጨመረ፤ ከካህናትም ብዙዎቹ ለእምነት ታዛዦች ሆኑ።
8እስጢፋኖስ ጸጋንና ኀይልን ተሞልቶ፣ በሕዝቡ መካከል ታላላቅ ድንቆችንና ምልክቶችን ያደርግ ነበር።
9ነገር ግን ነጻ የወጡት ሰዎች ምኵራብ ከሚባለው ምኵራብ፣ ከቀሬናና ከእስክንድርያ፣ ከኪልቅያና ከእስያም የሆኑ ጥቂት ሰዎች ተነሡ። እነዚህ ሰዎች ከእስጢፋኖስ ጋር ይከራከሩ ነበር።
10ነገር ግን ሰዎቹ እስጢፋኖስ የተናረገረበትን ጥበብና መንፈስ መቋቋም አልቻሉም።
11ከዚያም፣ “እስጢፋኖስ በሙሴና በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ሲናገር ሰምተናል” እንዲሉ አንዳንድ ሰዎችን በምስጢር አሳመኑ።
12ሰዎቹን፣ ሽማግሌዎቹን፣ የሕግ መምህራኖቹንም አነሣሡ፤ እስጢፋኖስንም ይዘው ወደ ሸንጎው አቀረቡት።
13እንዲህ ብለው የሚናገሩ ሐሰተኛ ምስክሮችንም አመጡ፤ “ይህ ሰው ይህን ቅዱስ ስፍራና ሕጉን ተቃውሞ መናገርን አያቆምም።
14ምክንያቱም ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል፤ ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዐትም ይለውጠዋል ሲል ሰምተነዋል።”
15በሸንጎው ውስጥ የተቀመጡት ሁሉ አተኵረው ተመለከቱት፤ ፊቱም እንደ መልአክ ፊት ሆኖ አዩት።