መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 4

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ጴጥሮስና ዮሐንስ ለሕዝቡ እየተናገሩ ሳሉ፣ ካህናቱና የቤተ መቅደሱ ሹም፣ ሰዱቃውያንም ወደ እነርሱ መጡ።
2እነርሱም፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ሕዝቡን ያስተምሩና ከሙታን መነሣቱንም ያውጁ ስለ ነበረ፣ እጅግ ተበሳጩ።
3ያዟቸውና በዚያ ጊዜ ምሽት ስለ ነበረ እስከሚቀጥለው ጧት ድረስ በወኅኒ አቈዩአቸው።
4ነገር ግን መልእክቱን ከሰሙት ብዙ ሰዎች አመኑ፤ ያመኑት ሰዎች ቍጥርም ዐምስት ሺሕ ያህል ነበረ።
5በሚቀጥለው ቀን እንደዚህ ሆነ፤ አለቆቻቸው፣ ሽማግሌዎቻቸውና የሕግ መምህራናቸው በኢየሩሳሌም ውስጥ በአንድነት ተሰበሰቡ።
6ሊቀ ካህናቱ ሐና እዚያ ነበረ፤ ቀያፋም፣ ዮሐንስም፣ እስክንድሮስና የሊቀ ካህናቱ ዘመዶች ሁሉ ነበሩ።
7ጴጥሮስንና ዮሐንስን በመካከላቸው አቁመውም፣ "በማን ሥልጣን ወይም በማንስ ስም ይህን አደረጋችሁ?" ብለው ጠየቋቸው።
8ከዚያም ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የሕዝቡ አለቆች፣ ሽማግሌዎችም፣
9ለታመመ ሰው የተደረገ መልካም ነገርን በሚመለከት በዚህ ቀን እየተጠየቅን ከሆንን፣ ይህ ሰው በምን ዳነ?
10ይህ ለእናንተ ለሁላችሁ፣ ለእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ የታወቀ ይሁን፤ ይህ ሰው በፊታችሁ እዚህ በጤንነት የቆመው እናንተ በሰቀላችሁት፣ እግዚአብሔር ከሞት ባስነሣው በናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው።
11ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ ነገር ግን የማእዘን ራስ የሆነ ድንጋይ ነው።
12በሌላ በማንም ድነት የለም፤ ልንድንበት የሚገባ በሰዎች መካከል የተሰጠ ሌላ ስም ከሰማይ በታች የለምና።”
13የጴጥሮስንና የዮሐንስን ድፍረት ሲያዩ፣ ያልተማሩና ተራ ሰዎች እንደ ሆኑ ሲያውቁም፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩ በማወቅ ተደነቁ።
14የተፈወሰው ሰውዬ ዐብሯቸው ቆሞ ስላዩት፣ የአይሁድ መሪዎች በእነርሱ ላይ ምንም መናገር አልቻሉም።
15ሐዋርያቱ ከሸንጎው ወጥተው እንዲሄዱ ካዘዙ በኋላ፣ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።
16እንደዚህም አሉ፤ “በእነዚህ ሰዎች ላይ ምን እናድርግ? በእነርሱ አማካይነት የታወቀ ተአምር የመፈጸሙ እውነታ በኢየሩሳሌም ለሚኖር ሁሉ ታውቆአልና፤ ልንክደው አንችልም።
17ሆኖም ይህ በሕዝቡ መካከል የበለጠ እንዳይሠራጭ፣ በዚህ ስም ከእንግዲህ ለማንም እንዳይናገሩ እናስጠንቅቃቸው።”
18ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ ውስጥ ጠርተው በኢየሱስ ስም ፈጽሞ እንዳይናገሩም፣ እንዳያስተምሩም አዘዟቸው።
19ነገር ግን ጴጥሮስና ዮሐንስ መልሰው እንዲህ አሏቸው፤ “ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ይልቅ እናንተን መታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል እንደ ሆነ እናንተ ፍረዱ።
20እኛ ስላየናቸውና ስለ ሰማናቸው ነገሮች ለመናገር ዝም ማለት አንችልም።”
21እንደ ገናም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ካስጠነቀቋቸው በኋላ፣ ለቀቋቸው። እነርሱን ለመቅጣት ምንም ምክንያት ለማግኘት አልቻሉም፤ ምክንያቱም ሰዎቹ ሁሉ ለተደረገው እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።
22ይህ በተአምር የተፈወሰው ሰውዬ ከዐርባ ዓመት በላይ ዕድሜ ነበረው።
23ከተለቀቁ በኋላ፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ራሳቸው ሰዎች መጡና የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሏቸውን ሁሉ ነገሯቸው።
24ሰዎቹ የነገሯቸውን ሲሰሙም፣ ድምፃቸውን በአንድነት ወደ እግዚአብሔር ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ሰማያትን፣ ምድርንና ባሕርን፣ በውስጣቸው የሚገኘውንም ሁሉ የፈጠርህ ነህ፤
25በመንፈስ ቅዱስም በአገልጋይህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለሃል፦ ‘አሕዛብ ለምን አጕረመረሙ፣ ሕዝቡስ ከንቱ ነገርን ለምን ዐሰቡ?
26በጌታ፣ በእርሱ መሲሕም ላይ የምድር ነገሥታት ተነሡ፣ አለቆችም በአንድነት ተሰበሰቡ።’
27በእውነት ሄሮድስና ጴንጤናዊው ጲላጦስ፣ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በቀባኸው በቅዱሱ አገልጋይህ በኢየሱስ ላይ በዚህ ከተማ ውስጥ በአንድነት ተሰብስበዋል።
28የተሰበሰቡትም እጅህና ዐሳብህ አስቀድመው የወሰኑት እንዲፈጸም ነው።
29ጌታ ሆይ፣ አሁን ወደ ዛቻዎቻቸው ተመልከት፤ ለባሪያዎችህም ቃልህን በሙሉ ድፍረት እንዲናገሩ ስጥ።
30ለመፈወስ እጅህን ስትዘረጋው፣ ምልክቶችና ድንቆች በቅዱሱ አገልጋይህ በኢየሱስ ስም ይደረጋሉ።"
31ጸሎት ሲጨርሱ፣ ተሰብስበውበት የነበረው ስፍራ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃልም በድፍረት ተናገሩ።
32ካመኑት እጅግ ብዙዎች አንድ ልብና አንድ ነፍስ ነበራቸው፤ ከእነርሱ አንድም ሰው፣ ያለው ማንኛውም ነገር የራሱ እንደ ሆነ አልተናገረም፤ ይልቁን ሁሉም ነገሮች የጋራ ነበሩ።
33ሐዋርያቱም በታላቅ ኀይል ስለ ጌታ ኢየሱስ ትንሣኤ ምስክርነታቸውን ያውጁ ነበር፤ በሁሉም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበረባቸው።
34በመካከላቸው ችግረኛ ሰው አልነበረም፤ መሬት ወይም ቤት ያላቸው ሁሉ ሸጠው የሽያጩን ገንዘብ ያመጡትና፣
35በሐዋርያት እግር አጠገብ ያስቀምጡት ነበርና። አከፋፈሉም ይደረግ የነበረው እያንዳንዱ አማኝ በሚያስፈልገው መሠረት ነው።
36ሌዋዊ የሆነው፣ ቆጵሮሳዊው ዮሴፍ ሐዋርያት በርናባስ የሚባል ስም ያወጡለት ሰው ነበር (ትርጕሙ የመጽናናት ልጅ ማለት ነው)።
37እርሱ የነበረውን መሬት ሸጠው፤ ገንዘቡንም አምጥቶ በሐዋርያት እግር አጠገብ አስቀመጠው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።