1ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸሎት ጊዜ፣ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር።
2ወደ ቤተ መቅደሱ ከሚገቡ ሰዎች ምጽዋት መለመን እንዲችል፣ ውብ ተብሎ በሚጠራው በቤተ መቅደሱ በር ላይ ሰዎች በየቀኑ በሸክም አምጥተው የሚያስቀምጡት፣ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ዐንካሳ የሆነ አንድ ሰው ነበረ።
3ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ ቤተ መቅደሱ ሊገቡ ሲሉ ባያቸው ጊዜ፣ ምጽዋት ለመነ።
4ጴጥሮስ ዐይኖቹን ምጽዋት በሚለምነው ሰውዬ ላይ በማድረግ፣ ከዮሐንስ ጋር “ወደ እኛ ተመልከት” አለው።
5ዐንካሳውም፣ ከእነርሱ አንድ ነገር ለመቀበል በመጠበቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ።
6ጴጥሮስ ግን፣ “ብርና ወርቅ የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ። በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተራመድ” አለው።
7ጴጥሮስ ቀኝ እጁን ያዘውና ወደ ላይ አነሣው፤ ወዲያውም እግሮቹና የቍርጭምጭሚቱ ዐጥንቶች ጥንካሬ አገኙ።
8ዐንካሳው ሰውዬ ወደ ላይ ዘልሎ ቆመ፤ መራመድም ጀመረ፤ ከጴጥሮስና ከዮሐንስ ጋርም እየተራመደ፣ እየዘለለና እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ።
9ሰዎች ሁሉ ዐንካሳው እየተራመደ ሲሄድና እግዚአብሔርን ሲያመሰግን አዩት።
10ምጽዋት ለመቀበል ውብ በሚባለው የቤተ መቅደሱ በር ላይ ይቀመጥ የነበረው ሰውዬ እንደ ሆነም ዐወቁ፤ በእርሱ ላይ ከሆነው የተነሣም በመደነቅና በመገረም ተሞሉ።
11ሰውየው የጴጥሮስንና የዮሐንስን እጅ ይዞ ሳለ፣ የሰሎሞን መመላለሻ በሚባለው ደጅ ሰዎች ሁሉ በኀይል እየተደነቁ በአንድነት ወደ እነርሱ ሮጡ።
12ጴጥሮስ ይህን ሲያይ ለሕዝቡ፣ “እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ለምን ትደነቃላችሁ? ይህን ሰው በገዛ ኀይላችን ወይም በመንፈሳዊነታችን እኛ እንዲራመድ እንዳደረግን ሁሉ፣ ለምን ዐይናችሁን አፍጥጣችሁ ትመለከታላችሁ? በማለት መልስ ሰጠ።
13የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ፣ የአባቶቻችን አምላክ አገልጋዩን ኢየሱስን አክብሮታል። እርሱ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትና ጲላጦስ ሊፈታው ወስኖ ሳለ፣ በፊቱ የካዳችሁት ነው።
14ቅዱሱንና ጻድቁን ካዳችሁት፤ በእርሱም ፈንታ ነፍሰ ገዳይ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ።
15እግዚአብሔር ከሙታን ያስነሣውን፣ የሕይወትን ጌታ ገደላችሁት፤ እኛም የዚህ ምስክሮች ነን።
16በእርሱ ስም ማመን አሁን የምታዩትንና የምታውቁትን ይህን ሰው ብርቱ አድርጎታል። አዎ፣ በኢየሱስ ያለው እምነቱ በሁላችሁ ፊት ይህን ፍጹም ጤንነት ሰጠው።
17አሁን ወንድሞች ሆይ፣ አለቆቻችሁም እንዳደረጉት ባለማወቅ ያደረጋችሁት እንደ ሆነ ዐውቃለሁ።
18ነገር ግን እግዚአብሔር በነቢያቱ ሁሉ አፍ የእርሱ ክርስቶስ መከራ መቀበል እንዳለበት አስቀድሞ የተናገረውን አሁን ፈጸመው።
19እንግዲህ ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ፣ ከጌታ ዘንድም የመታደስ ዘመን እንዲመጣ ንስሓ ግቡ፤ ተመለሱም፤
20ይኸውም ለእናንተ የመረጠውን ክርስቶስ የሆነውን ኢየሱስን እንዲልከው ነው።
21እርሱ ሰማያት ሊቀበሉትና ነገሮች ሁሉ እስከሚታደሱበት ዘመን ድረስ ጠብቀው ሊያቈዩት የሚገባ፣ ከጥንት ጀምሮ በነበሩ ቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተነገረለት ነው።
22ሙሴ በእርግጥ፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣል። የሚነግራችሁንም ሁሉ ስሙ’ አለ።
23ያን ነቢይ የማይሰማ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል።
24አዎ፣ ከሳሙኤል ጀምሮና ከእርሱም በኋላ የተናገሩ ነቢያት ሁሉ ስለ እነዚህ ቀኖች ተናግረዋል።
25እናንተ የነቢያትና ‘በዘርህ የምድር ሕዝቦች ሁሉ ይባረካሉ’ ብሎ ለአብርሃም እንደ ተናገረው፣ ከአባቶቻችሁ ጋር እግዚአብሔር ያደረገው ኪዳን ልጆች ናችሁ።
26እግዚአብሔር አገልጋዩን ካስነሣ በኋላ በመጀመሪያ ወደ እናንተ ላከው፤ ይኸውም እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ መልሶ ሊባርካችሁ ነው።