መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 2

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በበዓለ ኀምሳ ቀን ሁሉም በአንድነት አንድ ስፍራ ላይ ነበሩ።
2ድንገት እንደ ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ ተቀምጠውበት የነበረውን ቤትም ሞላው።
3እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳናት ታዩአቸው፤ በእያንዳንዳቸው ላይም ተቀመጡባቸው።
4ሁሉም መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፤ መንፈስ ቅዱስ እንዲናገሩ እንደ ሰጣቸውም በሌሎች ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ።
5በዚያን ጊዜ ከሰማይ በታች ካለው ሕዝብ ሁሉ የመጡ፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች፣ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ አይሁድ ነበሩ።
6ይህ ድምፅ ሲሰማ፣ ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰበ፣ እያንዳንዱ ሰውም በገዛ ራሱ ቋንቋ ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ።
7ሕዝቡ ተደነቁ፤ ተገረሙም፤ “እነዚህ የሚናገሩ ሰዎች ሁሉ በእውነት የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? ብለውም ተናገሩ።
8እያንዳንዳቸው በተወለድንበት ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማቸው ለምንድን ነው?
9የጳርቴና፣ የሜድና የኢላሜጥ ሰዎች፣ በመስጴጦምያም፣ በይሁዳም፣ በቀጰዶቅያም፣ በጳንጦስም፣ በእስያም፣
10በፍርግያም፣ በጵንፍልያም፣ በግብፅም፣ በቀሬና በኩል በሚገኙት የሊቢያ ክፍሎች የምንኖርም፣ ከሮም የመጣን፣
11አይሁድና ወደ ይሁዲነት የገባን ቀርጤሳውያንና ዐረባውያን የሆንን እኛም፣ እነዚህ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ታላላቅ ሥራዎች በራሳችን ቋንቋዎች ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።"
12ሁሉም ተደነቁ፣ ግራ ተጋቡም፤ እርስ በርሳቸውም፣ “ይህ ነገር ምን ይሆን?” ተባባሉ።
13ሌሎች ግን፣ “ዐዲስ ወይን ጠጅ ጠጥተው ጠግበው ነው” ብለውም በማፌዝ ተናገሩ።
14ነገር ግን ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆሞ፣ ድምፁን ከፍ በማድረግ እንደዚህ አላቸው፤ “የይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁሉ፣ ይህ ለእናንተ የታወቀ ይሁን፤ የምናገረውንም አድምጡ።
15እነዚህ ሰዎች እናንተ እንደምታስቡት አልሰከሩም፤ ምክንያቱም ገና ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነው።
16ነገር ግን በነቢዩ በኢዩኤል ይህ ተነግሯል፦
17‘በመጨረሻዎቹ ቀናት ይህ ይሆናል፣’ እግዚአብሔር እንደዚህ ይላል፤ ‘መንፈሴን ሥጋ በለበሱ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፣ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ። ወጣቶቻችሁ ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ።
18በአገልጋዮቼና በሴት አገልጋዮቼ ላይም በእነዚያ ቀናት መንፈሴን አፈስሳለሁ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ።
19በላይ በሰማይ ድንቆችን፣ ምልክቶችንም በታች በምድር ላይ፣ ደምን፣ እሳትንና የጢስ ደመናን አሳያለሁ።
20ታላቁና ገናናው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ፀሓይ ወደ ጨለማነት፣ ጨረቃም ወደ ደምነት ይለወጣሉ።
21የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።'
22የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ እነዚህን ቃሎች ስሙ፦ ራሳችሁ እንደምታውቁት የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ በመካከላችሁ እግዚአብሔር በእርሱ በኩል ባደረጋቸው ታላላቅ ተግባራት፣ በተኣምራትና በምልክቶች፣ ከእግዚአብሔር ለእናንተ መገለጡ የተረጋገጠ ሰው ነው።
23አስቀድሞ በተወሰነው የእግዚአብሔር ዕቅድና በቀዳሚ ዕውቀቱ መሠረት፣ ዐልፎ ተሰጥቶአል፤ እናንተም በዐመፀኞች እጅ ሰቀላችሁት፤ ገደላችሁትም፤
24እግዚአብሔርም የሞትን ጣር ከእርሱ አጥፍቶ አስነሣው፤ ምክንያቱም ሞት እርሱን ይይዘው ዘንድ አልቻለም።
25ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ብሎ ይናገራልና፦ ‘ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፤ በቀኜ ነውና አልናወጥም።
26ስለዚህ ልቤ ተደሰተ፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ። ሥጋዬም በተስፋ ያድራል።
27ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም፤ ቅዱስህም መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም።
28የሕይወትን መንገድ ገለጥህልኝ፤ በፊትህም ደስታን ታጠግበኛለህ።’
29ወንድሞች ሆይ፣ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት በግልጽ ልነግራችሁ እችላለሁ፤ እርሱ ሞቶአል፤ ተቀብሮአልም፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ ዘንድ ነው።
30ስለዚህ ዳዊት ነቢይ ነበረና ከዘሩ በዙፋኑ ላይ አንድን ሰው እንደሚያስቀምጥ እግዚአብሔር በመሐላ ለእርሱ ቃል ገብቶለት ነበር።
31ዳዊት ይህን አስቀድሞ አየ፤ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤም ተናገረ፦ ክርስቶስ በሲኦል አልቀረም፤ ሥጋውም መበስበስን አላየም።
32ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው፤ ለዚህም እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን።
33ስለዚህ ከሙታን በመነሣትና በእግዚአብሔር ቀኝ በመቀመጥ፣ ከአብ ቃል የተገባውን መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ፣ እናንተ የምታዩትንና የምትሰሙትን ይህን አፈሰሰው።
34-35ዳዊት ወደ ሰማይ አልወጣም፤ ነገር ግን እንዲህ ይላል፦ “ጌታ ለጌታዬ፣ ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርጋቸው ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።”
36ስለዚህ፣ እናንተ የሰቀላችሁትን ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።"
37ሕዝቡ ይህን ሲሰሙ ልባቸው ተነካና ለጴጥሮስና ለቀሩት ሐዋርያት፣ “ወንድሞች ሆይ፣ ምን እናድርግ?” አሉ።
38ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ እያንዳንዳችሁም ለኀጢአታችሁ ይቅርታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ መንፈስ ቅዱስንም በስጦታነት ትቀበላላችሁ።
39የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ፣ ጌታ አምላካችን ለሚጠራቸው ሩቅ ላሉት ሁሉም ነውና።”
40ጴጥሮስ በሌሎች ብዙ ቃላት መሰከረ፤ “ከዚህ ክፉ ትውልድ ራሳችሁን አድኑ” በማለትም አስጠነቀቃቸው።
41ከዚያም ሕዝቡ ቃሉን ተቀብለው ተጠመቁ፤ በዚያም ቀን ሦስት ሺሕ ያህል ሰዎች ተጨመሩ።
42እነርሱም ሐዋርያት በሚያስተምሩት ትምህርትና በኅብረት፣ እንጀራውን በመቊረስና በጸሎትም ይተጉ ነበር።
43በሰው ሁሉ ላይ ፍርሀት መጣ፤ ብዙ ድንቆችና ምልክቶችም በሐዋርያት እጅ ተደረጉ።
44ያመኑት ሁሉ በአንድነት ነበሩ፤ ሁሉም ነገር የጋራ ነበር፤
45መሬታቸውንና ንብረታቸውን እየሸጡም ለሁሉም እንደሚያስፈልገው አካፈሉ።
46በየቀኑም በአንድ ዐላማ በመቅደስ እየተጉ፣ በቤት ውስጥ እንጀራ እየቈረሱም ምግብን ልባዊ በሆነ ደስታና ትሕትና ዐብረው ይመገቡ ነበር፤
47እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ በሕዝቡም ሁሉ ዘንድ ከበሬታ ነበራቸው። ጌታም የሚድኑትን በየቀኑ በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።