መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 27

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ወደ ኢጣሊያ በመርከብ እንድንሄድ በተወሰነ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሌሎችን እስረኞች የአውግስጦስ ክፍለ ጦር አባል ለሆነ ዩልዮስ ለተባለ የመቶ አለቃ አስረከቡአቸው።
2እኛም ከአድራሚጥዮን ተነሥተን በእስያ ጠረፍ ሊሄድ በተዘጋጀ መርከብ ላይ ተሳፍረን ወደ ባሕር ተጓዝን። በመቄዶንያ ካለችው ተሰሎንቄ የሆነው አርስጥሮኮስም ከእኛ ጋር ሄደ።
3በማግስቱ ወደ ሲዶን ከተማ ደርሰን፣ ከመርከብ ወረድን፤ እዚያም ዩልዮስ ለጳውሎስ ቸርነት አደረገለት፤ ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድና እንክብካቤ እንዲያደርጉለትም ፈቀደለት።
4ከዚያም ተነሥተን ወደ ባሕር ሄድን፤ ነፋስ ይነፍስብን ስለ ነበር፣ በመርከብ ሆነን ነፋሱ በማያገኛት በቆጵሮስ ደሴት ዙሪያ ተጓዝን።
5በኪልቅያና በጵንፍልያ አጠገብ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላም፣ የሉቅያ ከተማ ወደ ሆነው ወደ ሙራ ደረስን።
6በዚያም፣ የመቶ አለቃው ከእስክንድርያ ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ መርከብ አግኝቶ አሳፈረን።
7ብዙ ቀንም በዝግታ ተጓዝንና በመጨረሻ በችግር ወደ ቀኒዶስ ደረስን፤ ነፋሱም በዚያ መንገድ እንዳንሄድ ስለከለከለን፣ በሰልሙና አንጻር ያለችውን ቀርጤስን ተገን አድርገን ተጓዝን።
8በላሲያ ከተማ አጠገብ ወዳለው መልካም ወደብ ወደ ተባለው ስፍራ እስከምንደርስ ድረስ በችግር በጠረፉ በኩል ተጓዝን።
9ብዙ ጊዜም አሳለፍን፤ የአይሁድ የጾም ወራት ደግሞ ዐልፎ ነበር፤ ጕዞውን መቀጠልም አደጋ የሚያስከትል ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ አስጠነቀቃቸው፤
10እንዲህም አለ፤ “እናንተ ሰዎች፣ አሁን የምናደርገው ጕዞ አደጋና ብዙ ጉዳት እንደሚኖርበት ይታየኛል፤ አደጋውም በመርከቡና በጭነቱ ብቻ ሳይሆን፣ በእኛም ሕይወት ላይ የሚደርስ ነው።”
11የመቶ አለቃው የሰማው ግን ጳውሎስ የተናገረውን ሳይሆን፣ በይበልጥ የመርከቡ አዛዥና ባለቤት ያሉትን ነው።
12ክረምቱን ለማሳለፍ ወደቡ ተስማሚ ስላልነበረ፣ አብዛኛዎቹ ተጓዦች የሚቻል ከሆነ ከዚያ ተነሥተን ፊንቄ ወደ ተባለችው ከተማ እንድንሄድና ክረምቱን እዚያ እንድናሳልፍ ምክር ሰጡን። ፊንቄ በሰሜን ምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ አንጻር የምትገኝ የቀርጤስ ወደብ ነች።
13የደቡቡ ነፋስ በቀስታ መንፈስ በጀመረ ጊዜ፣ መርከበኞቹ የፈለጉት እንደተከናወነላቸው ዐሰቡ። ስለዚህ ሸራውን አውርደው በባሕሩ ዳርቻ አቅራቢያ፣ በቀርጤስ በኩል አለፉ።
14ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን፣ የሰሜን ምሥራቅ ዐውሎ ነፋስ የተባለ ኃይለኛ ነፋስ ደሴቲቱን አቋርጦ በመምጣት ይነፍስብን ጀመረ፤
15መርከቡም ወደ ፊት በተገፋና ነፋሱን መቋቋም ባልቻለ ጊዜ፣ ዝም ብለነው በነፋሱ እየተነዳን ሄድን።
16ቄዳ የተባለችውን ትንሽ ደሴት ተተግነን ተጓዝን፤ በትልቅ ችግርም ሕይወት አድን ጀልባው ላይ መውጣት ቻልን።
17መርከበኞቹ ጀልባውን ወደ መርከቡ ጎትተው አወጡት፤ ገመዱንም የመርከቡን ዙሪያ ለማሰር ተጠቀሙበት። ስርቲስ በምትባል አሸዋማ ስፍራ እንዳንወድቅ ፈርተው ነበር፤ ስለዚህ የባሕር ሸራውን አውርደው እየተነዱ ሄዱ።
18ዐውሎ ነፋሱ በጣም ስላየለብን፣ በማግስቱ መርከበኞቹ የመርከቡን ጭነት ወደ ባሕር መጣል ጀመሩ።
19በሦስተኛው ቀን መርከበኞቹ በመርከቡ የሚያገለግሉ ዕቃዎችን እያነሡ ጣሉ።
20ለብዙ ቀንም ፀሐይና ከዋክብት ብርሃናቸውን ባልሰጡንና ትልቁ ማዕበልም በወረደብን ጊዜ፣ አንድንም ብለን ተስፋ ቈረጥን።
21ተጓዦቹ ምግብ ሳይበሉ ብዙ ቀን ቈይተው ነበር፤ በዚያን ጊዜ ጳውሎስ በተጓዦቹ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፤ “እናንተ ሰዎች፣ ይህ አደጋና ጉዳት እንዳይደርስባችሁ፣ ከቀርጤስ አትነሡ ብዬ የነገርኋችሁን መስማት ነበረባችሁ፤
22አሁንም መርከቡ ብቻ ይጎዳል እንጂ ከመካከላችሁ የሚሞት አይኖርምና አይዞአችሁ ብዬ እመክራችኋለሁ።
23ምክንያቱም ባለፈው ሌሊት የእርሱ የሆንሁትና ደግሞም የማመልከው የእግዚአብሔር መልአክ በአጠገቤ ቆሞ እንዲህ ብሏል፤
24“ጳውሎስ ሆይ፣ አትፍራ። በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ ተመልከት፤ እግዚአብሔር በቸርነቱ ዐብረውህ የሚጓዙትን ሁሉ ሰጥቶሃል።
25ስለዚህ እናንተ ሰዎች፣ አይዞአችሁ፤ ልክ እንደ ተናገረኝ እንደሚሆን እግዚአብሔርን አምነዋለሁ።
26ነገር ግን ወደ አንዲት ደሴት ደርሰን ልናርፍ ይገባል።”
27በዐሥራ አራተኛውም ሌሊት፣ በአድርያቲክ ባሕር ወዲያና ወዲህ እየተንገላታን እያለን፣ እኩለ ሌሊት ገደማ፣ መርከበኞቹ ወደ መሬት የቀረቡ መሰላቸው።
28የባሕር ጥልቀት መለኪያ ገመድ ጣሉና ጥልቀቱን አርባ ሜትር ሆኖ አገኙት፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ መለኪያውን ሲጥሉም ሠላሳ ሜትር ሆኖ አገኙት።
29ከዐለቶቹ ጋር እንጋጫለን ብለውም ፈሩ፤ ስለዚህ ከኋላ አራት መልሕቆችን አውርደው ቶሎ እንዲነጋ ጸለዩ።
30መርከበኞቹ መርከቡን ትተው ለመሄድ መንገድ ይፈልጉና ሕይወት አድን ጀልባውን ወደ ባሕሩ ውስጥ ያወርዱ ነበር፤ መልሕቆቹንም ከቀስቱ የሚወረውሩ መሰሉ።
31ጳውሎስ ግን መቶ አለቃውንና ወታደሮቹን፣ “እነዚህ ሰዎች በመርከቡ ካልቆዩ በቀር፣ እናንተ መዳን አትችሉም” አላቸው።
32ከዚያም ወታደሮቹ የጀልባውን ገመዶች ቈረጡት፤ እንዲንሳፈፍም አደረጉት።
33ቀኑ ሊነጋ ሲልም፣ ምግብ እንዲበሉ ጳውሎስ ሁሉንም መከራቸው። እንዲህም አላቸው፤ “ምንም ሳትበሉ ከቈያችሁ ይህ ዐሥራ አራተኛ ቀናችሁ ነው።
34ስለዚህ በሕይወት እንድትኖሩ፣ ጥቂት ምግብ እንድትበሉ እለምናችኋለሁ፤ ከራሳችሁ ላይ አንዲቱም ጠጕር አትጠፋም።”
35ይህን ተናግሮ፣ እንጀራ አነሣና በሁሉም ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ። ከዚያም እንጀራውን ቈርሶ መብላት ጀመረ።
36በዚያን ጊዜ ሁሉም ተጽናንተው ምግብ በሉ።
37በመርከቡ ውስጥ 276 ሰዎች ነበርን።
38በልተው በጠገቡ ጊዜም፣ ስንዴውን ወደ ባሕሩ በመጣል የመርከቡን ጭነት አቃለሉ።
39በነጋታውም፣ የነበሩበትን ምድር አላወቁትም፤ ነገር ግን በዳርቻ ያለውን የባሕር ሰርጥ አዩ፤ መርከቡን ወደ ሰርጡ መግፋት ይችሉ እንደሆነም ተነጋገሩ።
40ስለዚህ መልሕቆቹን ቈርጠው ባሕሩ ላይ ተዉአቸው። በዚሁ ጊዜም የመቅዘፊያዎቹን ገመዶች ፈትተው ሸራውን ወደ ነፋሱ ከፍ አደረጉና ወደ ባሕሩ ዳርቻ ለመውጣት ሄዱ።
41ነገር ግን ሁለት ማዕበሎች ወደ ተገናኙበት ስፍራ መጡ፤ መርከቡም ወደ መሬት ገባ፤ የመርከቡ ቅስትም በዚያ ተተከለና የማይነቃነቅ ሆነ፤ የኋላ ክፍሉ ግን ከማዕበሉ ነውጥ የተነሣ ይሰባበር ጀመር።
42የወታደሮቹ ዕቅድ ከመካከላቸው ማንም ዋኝቶ እንዳያመልጥ እስረኞቹን ለመግደል ነበር።
43የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ለማዳን ፈለገ፤ ስለዚህ ዕቅዳቸውን አልተቀበለም፤ መዋኘት የሚችሉትም በመጀመሪያ ከመርከቡ ላይ እየዘለሉ ወደ የብስ እንዲወጡ አዘዘ።
44ከዚያም የቀሩት ሰዎች በሳንቃዎችና ከመርከቡ በተገኙ ስብርባሪዎች ላይ ሆነው ተከትለው እንዲወጡ አደረገ። በዚህ ዐይነት ሁላችንም በደኅና ወደ የብስ ወጣን።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።