1አግሪጳም ጳውሎስን፣ «አንተ ለራስህ ተናገር» አለው። ከዚያም በኋላ፣ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ መከላከያውን አቀረበ።
2«ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ ዛሬ በፊትህ አይሁድ ስለ ከፈቱብኝ ክስ ሁሉ መከላከያዬን ሳቀርብ ራሴን ደስተኛ አድርጌ እቈጥረዋለሁ፤
3ምክንያቱም በተለይ አንተ የአይሁድን ልማድና ጥያቄ ሁሉ ጠንቅቀህ ታውቃለህ። ስለዚህ በትግዕሥት እንድታደምጠኝ እለምንሃለሁ።
4በእውነት ከልጅነቴ ጀምሮ በሕዝቤ መካከልና በኢየሩሳሌም እንዴት እንደ ኖርሁ አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ።
5ከመጀመሪያው አንሥቶ እኔን ያውቁኛል፤ የሃይማኖታችን በጣም ወግ አጥባቂ ክፍል ፈሪሳዊ ሆኜ እንደ ኖርሁም ሊያምኑ ይገባል።
6አሁን እዚህ ለፍርድ የቆምሁት እግዚአብሔር ለአባቶቻችን የሰጠውን ተስፋ የምፈልግ በመሆኔ ነው።
7በዚህ ምክንያት ዐሥራ ሁለቱ ነገዶቻችን ቀንና ሌሊት በቅንነት እግዚአብሔርን ያገለግላሉ፤ እኛም ወደ እርሱ ለመድረስ ተስፋ እናደርጋለን። ንጉሥ ሆይ፣ አይሁድ እኔን የሚከሱኝ ስለዚህ ተስፋ ነው!
8እግዚአብሔር ሙታንን እንደሚያስነሣ አይታመንም ብላችሁ ለምን ታስባላችሁ?
9አንድ ጊዜ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስን ስም በመቃወም ብዙ ነገር ማድረግ አለብኝ ብዬ ዐሰብሁ።
10በኢየሩሳሌምም ይህንኑ አደረግሁ፤ ከምእመናን ብዙዎችን ወኅኒ እንዲገቡ አደረግሁ፤ ለዚህም ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብዬ ነበር፤ በሚገደሉበት ጊዜም፣ ተስማምቻለው።
11ብዙ ጊዜም በምኵራቦች ሁሉ እንዲቀጡ አድርጌአለሁ፤ የስድብ ቃል እንዲናገሩም ጥረት አድርጌአለሁ። ምእመናኑን እጅግ እቈጣቸውና ሌሎች ከተሞች እንኳ አሳድዳቸው ነበር።
12ይህን እያደረግሁ፣ ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ሄድሁ፤
13ወደዚያ በመጓዝ ላይ እያለሁም ንጉሥ ሆይ፣ እኩለ ቀን ላይ ከፀሐይ ይልቅ የሚያበራ ብርሃን ከሰማይ አየሁ፤ በእኔና አብረውኝ ይጓዙ በነበሩት ሰዎች ዙሪያም አበራ።
14ሁላችንም በመሬት ላይ በወደቅን ጊዜ፣ በዕብራይስጥ ቋንቋ፣ «ሳውል፣ ሳውል፣ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የመውጊያውን ብረት ብትረግጥ ለአንተ ይከፋብሃል» የሚል ድምፅ ሲናገረኝ ሰማሁ።
15እኔም፣ 'ጌታ ሆይ፣ አንተ ማን ነህ?' አልሁ። ጌታም እንዲህ ብሎ መለሰልኝ፤ 'አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ።
16ተነሣና በእግርህ ቁም፤ እኔ የተገለጥሁልህ አሁን ስለ እኔ ስለምታውቃቸውና ኋላ ላይ ስለማሳይህ ነገሮች አገልጋዬና ምስክር እንድትሆን ልሾምህ ነው፤
17ወደ እነርሱ ከምልክህ ሕዝብና ከአሕዛብም አድንሃለሁ ፤
18ዐይናቸውን እንድትከፍትላቸውና ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሰይጣን ኃይልም ወደ እግዚአብሔር እንድትመልሳቸው አደርግሃለሁ፤ ይኸውም በእኔ በማመናቸው ለራሴ የለየኋቸው እነርሱ፣ ከእግዚአብሔር የኃጢአትን ይቅርታና ርስትን እንዲቀበሉ ነው።'
19ስለዚህ፣ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ ለሰማያዊው ራእይ አልታዘዝም አላልሁም፤
20ነገር ግን መጀመሪያ በደማስቆ ላሉት፣ ከዚያም በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳ፣ ደግሞም ለአሕዛብ ንስሓ እንዲገቡ፣ ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉና ለንስሓ የሚገባ ሥራ እንዲሠሩ ሰበክሁ።
21በዚህ ምክንያት አይሁድ በቤተ መቅደስ ያዙኝና ሊገድሉኝ ሞከሩ።
22እስካሁን ድረስ እግዚአብሔር ረድቶኛል፤ ስለዚህ ለታናናሾችና ለታላላቆች ለመመስከር እዚህ ቆሜአለሁ፤ ምስክርነቴም ሙሴና ነቢያት ይሆናል ብለው ከተናገሩት የሚያልፍ አይደለም፤
23ይኸውም ክርስቶስ መከራ ይቀበላል፤ ከሙታን ለመነሣትና ለአይሁድ ሕዝብ፣ ለአሕዛብም ብርሃንን ለመስበክ የመጀመሪያው ይሆናል የሚል ነው።
24ጳውሎስም መከላከያውን እንደ ጨረሰ ፊስጦስ፣ «ጳውሎስ፣ አንተ ዕብድ ነህ፤ ብዙ መማርህ አሳብዶሃል» ሲል ጮኾ ተናገረ።
25ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ፤ «እጅግ የተከበርህ ፊስጦስ ሆይ፣ እኔ ዕብድ አይደለሁም፤ ነገር ግን እውነተኛውንና ትክክለኛውን ቃል በድፍረት እናገራለሁ።
26ንጉሡ ስለ እነዚህ ነገሮች ያውቃልና እንደ ልብ እነግረዋለሁ፤ በመሆኑም ከእነዚህ ነገሮች አንዱም ከእርሱ የተሰወረ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ።
27ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ በነቢያት ታምናለህን? እንደምታምን ዐውቃለሁ።»
28አግሪጳም ጳውሎስን፣ «በአጭር ጊዜ ልታሳምነኝና ክርስቲያን ልታደርገኝ ትፈልጋለህን?» አለው።
29ጳውሎስም፣ «በአጭር ይሁን ወይም በረዥም ጊዜ፣ አንተ ብቻ ሳትሆን፣ ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ፣ ከእነዚህ የወኅኒ ሰንሰለቶች በቀር እንደ እኔ እንድትሆኑ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ» አለ።
30ከዚያም ንጉሡ፣ ገዥውም፣ በርኒቄም ደግሞ፣ ከእነርሱ ጋር ተቀምጠው የነበሩትም ተነሡ፤
31ከአዳራሹም በወጡ ጊዜ፣ እርስ በርስ ተነጋግረው ፣«ይህ ሰው ለሞት ወይም ለእስራት የሚያበቃ ምንም አላደረገም» አሉ።
32አግሪጳ ፊስጦስን፣ «ይህ ሰው ወደ ቄሣር ይግባኝ ባይል ኖሮ በነጻ ሊለቀቅ ይችል ነበር» አለው።