1ወደ መሬት በደኅና በደረስን ጊዜም፣ ደሴቲቱ ማልታ የምትባል መሆንዋን ዐወቅን።
2የዚያች ደሴት ሰዎችም የተለመደውን ደግነት እንኳ አላሳዩንም፤ ሆኖም፣ በማያቋርጠው ዝናብና ብርድ ምክንያት እሳት አንድደው ሁላችንንም ተቀበሉን።
3ነገር ግን ጳውሎስ ጭራሮ ሰብስቦ እሳቱ ላይ በጨመረው ጊዜ፣ ከሙቀቱ የተነሣ አንድ እፉኝት ወጣና በእጁ ላይ ተጣበቀ።
4የደሴቲቱ ሰዎችም እፉኝቱ ከእጁ ላይ ተንጠልጥሎ ባዩ ጊዜ፣ እርስ በርሳቸው፣ “ይህ ሰው በእርግጥ ከባሕር ያመለጠ ነፍሰ ገዳይ ስለ ሆነ፣ ፍትሕ በሕይወት እንዲኖር አልፈቀደለትም” ተባባሉ።
5ጳውሎስ ግን እፉኝቱን በእሳቱ ላይ አራገፈው፤ አልተጐዳምም።
6ሰዎቹም ሰውነቱ በትኵሳት ያብጣል ወይም በድንገት ይሞታል ብለው ይጠባበቁ ነበር። ነገር ግን ረዘም ላለ ጊዜ ተጠባብቀውት ምንም እንዳልደረሰበት ካዩ በኋላ፣ ዐሳባቸውን ለውጠው አምላክ ነው አሉ።
7በአቅራቢያው ባለ አንድ ስፍራም ፑብልዮስ የተባለ የደሴቲቱ ገዢ መሬት ነበር፤ እርሱም ተቀብሎን ሦስት ቀን በደግነት አስተናገደን።
8የፑብልዮስ አባት ትኵሳትና ተቅማጥ ይዞት ታሞ ነበር። ጳውሎስ ወደ እርሱ ሄዶ ጸለየ፤ እጆቹን ጫነበት፤ ፈወሰውም።
9ይህ ከሆነ በኋላ፣ በደሴቲቱ የሚኖሩ ታመው የነበሩ ሌሎች ደግሞ መጡና ተፈወሱ።
10ሰዎቹም እጅግ አከበሩን። ለመሄድ በምንዘጋጅበት ጊዜም፣ የሚያስፈልገንን ሰጡን።
11ከሦስት ወር በኋላ፣ አፍንጫው ላይ የመንታ ወንድማማች ዓርማ በነበረበት፣ ክረምቱን በደሴቲቱ ባሳለፈ የእስክንድርያ መርከብ ላይ ተሳፍረን ጕዞ ጀመርን።
12ወደ ሲራኩስ ከተማ ከደረስን በኋላም፣ እዚያ ሦስት ቀን ቈየን።
13ከዚያም ተጕዘን ወደ ሬጊዩም ከተማ ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላ የደቡብ ነፋስ ተነሣ፤ በሁለት ቀንም ወደ ፑቲዮሉስ ከተማ መጣን።
14እዚያም አንዳንድ ወንድሞችን አገኘንና ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን እንድንቈይ ተጋበዝን። በዚህ ዐይነት ወደ ሮም መጣን።
15ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ከሰሙ በኋላ፣ ሊቀበሉን አፍዩስ ገበያና ሦስቱ ማደሪያዎች ድረስ መጡ። ጳውሎስ ወንድሞችን ባየ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ተጽናናም።
16ወደ ሮም በገባን ጊዜ፣ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ብቻውን እንዲኖር ተፈቀደለት።
17ቀን በኋላ፣ ጳውሎስ በአይሁድ መካከል መሪዎች የነበሩትን ሰዎች አንድ ላይ ጠራ። በተሰበሰቡ ጊዜም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፣ በሕዝቡ ወይም በአባቶች ሥርዓት ላይ የፈጸምሁት ስሕተት ባይኖርም እንኳ፣ ከኢየሩሳሌም በእስረኝነት ለሮማውያን እጅ ተላልፌ ተሰጠሁ።
18እነርሱ ከመረመሩኝ በኋላ ለሞት የሚያበቃኝ ምክንያት ስላልነበረብኝ፣ በነጻ ሊለቁኝ ፈልገው ነበር።
19ነገር ግን አይሁድ የሮማውያንን ፍላጎት ተቃውመው በተናገሩ ጊዜ፣ በሕዝቤ ላይ የማቀርበው ክስ ባይኖረኝም እንኳ፣ ወደ ቄሣር ይግባኝ ለማለት ተገደድሁ።
20በዚህ ምክንያት፣ ላያችሁና ላነጋግራችሁ ልመና አቅርቤአለሁ፤ ምክንያቱም እኔ በዚህ ሰንሰለት የታሰርሁት ለእስራኤል ስለ ተሰጠው እምነት ነው።”
21ከዚያም እነርሱ እንዲህ አሉት፤ “ከይሁዳ ስለ አንተ ደብዳቤ አልደረሰንም፤ ከወንድሞች መካከልም ስለ አንተ ያወራ ወይም ክፉ የተናገረ የለም።
22ነገር ግን በሁሉም ስፍራ ተቃውሞ እየተወራበት መሆኑን እኛ ስለምናውቅ፣ ስለዚህ የሃይማኖት ወገን ምን እንደምታስብ ከአንተ መስማት እንፈልጋለን።”
23ለጳውሎስ ቀን በቀጠሩለት ጊዜም፣ ብዙ ሰዎች ወደ መኖሪያ ቤቱ መጡ። እርሱም ጉዳዩን ገለጠላቸው፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም መሰከረላቸው። ከጠዋት እስከ ማታም ከሙሴ ሕግና ከነቢያት እየጠቀሰ፣ ስለ ኢየሱስ ሊያሳምናቸው ጥረት አደረገ።
24አንዳንዶች የተናገረውን ቃል ሲያምኑ፣ ሌሎች ግን አላመኑም።
25እርስ በርሳቸው ሳይስማሙ ሲቀሩ፣ ጳውሎስ ይህን አንድ ቃል ከተናገረ በኋላ ሄዱ፤ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካይነት ለአባቶቻችሁ በትክክል ተናገረ።
26እንዲህም አለ፤ ‘ወደዚህ ሕዝብ ሂድና እንደዚህ በላቸው፤ ‘መስማትስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትስ ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አታደርጉም።
27በዐይናቸው እንዳያዩ፣ በጆሮአቸው እንዳይሰሙ፣ በልባቸው እንዳያስተውሉ፣ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፣ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፤ ዐይናቸውም ተጨፍኖአል።’
28-29ስለዚህ፣ ይህ የእግዚአብሔር ድነት ወደ አሕዛብ እንደ ተላከ፣ እነርሱም እንደሚቀበሉት ዕወቁ።
30ጳውሎስ በተከራየው በራሱ ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ኖረ፤ ወደ እርሱ የሚመጡትንም ሁሉ ይቀበል ነበር።
31የእግዚአብሔርን መንግሥት ይሰብክ፣ ያስተምርም ነበር። ይህንም ሲያደርግ ማንም አልከለከለውም።