1ፊስጦስም ወደ ክፍለ ሀገሩ ገባ፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ከቂሣርያ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።
2የካህናት አለቃውና ታዋቂ የሆኑት አይሁድ ጳውሎስን ፊስጦስ ላይ ከሰሱት፤ ለፊስጦስም በኀይል ተናገሩ።
3በመንገድም ላይ ሊገድሉት ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያስጠራው ፊስጦስን ለመኑት።
4ፊስጦስ ግን መልሶ ጳውሎስ በቂሣርያ እስረኛ እንደ ሆነ፣ እርሱ ራሱም ወደዚያ እንደሚመለስ ተናገረ።
5“ስለዚህ፣ የሚችሉ ከእኛ ጋር ወደዚያ መሄድ አለባቸው። ሰውየው ያጠፋው ነገር ካለ፣ ክሰሱት” አለ።
6ፊስጦስም ስምንት ወይም ዐሥር ቀን ከቆየ በኋላ፣ ወደ ቂሣርያ ወረደ። በማግስቱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ጳውሎስን ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ።
7ጳውሎስም በደረሰ ጊዜ፣ ከኢየሩሳሌም የመጡት አይሁድ በአጠገቡ ቆሙ፤ በማስረጃ ማረጋገጥ ያልቻሉትን ብዙ ከባድ ክስም አቀረቡ።
8ጳውሎስ፣ “በአይሁድ ስምም ላይ፣ በቤተ መቅደሱም ላይ፣ በቄሣርም ላይ በደል አልፈጸምሁም” ብሎ ራሱን ተከላከለ።
9ፊስጦስ ግን አይሁድን ለማስደሰት ፈለገ፤ ስለሆነም፣ “እስከ ኢየሩሳሌም መውጣትና ስለ እነዚህ ነገሮች በዚያ ፍርድ እንድሰጥህ ትፈልጋለህን?” ብሎ ጳውሎስን ጠየቀው።
10ጳውሎስም እንዲህ አለ፤ “ፍርድ ሊሰጠኝ በሚገባኝ በቄሣር የፍርድ ወንበር ፊት እቆማለሁ። አንተም ደግሞ በሚገባ እንደምታውቀው፣ አንድንም አይሁዳዊ አልበደልሁም።
11ብበድልና ሞት የሚገባውን ነገር አድርጌ ቢሆን እንኳ፣ አልሞትም አልልም። እነርሱ በእኔ ላይ የሚያቀርቡት ክስ ከንቱ ከሆነ ግን፣ ማንም ለእነርሱ አሳልፎ ሊሰጠኝ አይችልም። ለቄሣር ይግባኝ ብያለሁ።”
12ከዚያም ፊስጦስ ከሸንጎው ጋር ተነጋግሮ፣ “ለቄሣር ይግባኝ ብለሃልና ወደ ቄሣር ትሄዳለህ” ብሎ መለሰ።
13ከጥቂት ቀናትም በኋላ ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ፊስጦስን ለመጐብኘት ቂሣርያ ደረሱ።
14ንጉሥ አግሪጳ በዚያ ብዙ ቀን ከተቀመጠ በኋላ፣ ፊስጦስ የጳውሎስን ጉዳይ ለንጉሡ አቀረበ፤ እንዲህም አለ፤ “ፊልክ አስሮ የተወው አንድ ሰው በዚህ አለ።
15እኔ በኢየሩሳሌም በነበርሁ ጊዜ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች ክስ መሥርተውበት ለእኔ አመለከቱ፤ እንድፈርድበትም ለመኑኝ።
16ለዚህም፣ የተከሰሰው ሰው በከሳሾቹ ፊት ቀርቦ ለተከሰሰበት ነገር እንዲከላከል ዕድል ሳይሰጠው አንድን ሰው አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ልማድ አይደለም ብዬ መልስ ሰጠሁ።”
17ስለዚህ፣ እነርሱ በአንድ ላይ ወደዚህ በመጡ ጊዜ፣ አልዘገየሁም፤ ነገር ግን በማግስቱ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ ሰውዬውን እንዲያመጡት አዘዝሁ።
18ከሳሾቹ ቆመው በከሰሱት ጊዜ፣ ካቀረቡበት ክሶች ማንኛቸውም ከባድ አይደሉም ብዬ ዐሰብሁ።
19ይልቁንም ስለ ገዛ ራሳቸው ሃይማኖትና ጳውሎስ ሕያው ነው ስለሚለው ሞቶ ስለ ነበረው ኢየሱስ ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ነበር።
20ይህን ጉዳይ እንዴት እንደምመረምር ግራ ገብቶኝ ነበር፤ ስለ እነዚህ ነገሮችም በዚያ ለመፋረድ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ እንደ ሆነ ጳውሎስን ጠየቅሁት።
21ጳውሎስ ግን የንጉሠ ነገሥቱን ውሳኔ እስኪያገኝ፣ በዘብ እንዲጠበቅ ይግባኝ ባለ ጊዜ፣ ወደ ቄሣር እስክሰደው ድረስ በጥበቃ ሥር እንዲሆን አዘዝሁት።”
22አግሪጳ፣ “እኔ ደግሞ ይህን ሰው ልሰማው እፈልጋለሁ” ብሎ ፊስጦስን አነጋገረው። ፊስጦስም፣ “ነገ ትሰማዋለህ” አለው።
23ስለ ሆነም፣ በማግስቱ፣ አግሪጳና በርኒቄ በታላቅ ሥነ ሥርዓት ከወታደራዊ መኮንኖችና ከከተማዋ ታዋቂ ሰዎች ጋር ወደ አዳራሹ ገቡ። በፊስጦስ ትእዛዝም ጊዜ ጳውሎስን ወደ እነርሱ አመጡት።
24ፊስጦስም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ እዚህ ከእኛ ጋር ያላችሁትም ሰዎች ሁሉ፣ ይህን ሰው ተመልከቱት፤ በኢየሩሳሌምና እዚህም ያሉት የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ ከእኔ ጋር ተማከሩ፤ ይህ ሰው ከእንግዲህ ወዲያ በሕይወት መኖር የለበትም ብለውም ጮኹብኝ።
25እኔ ግን ለሞት የሚያበቃው ምንም በደል አለመፍጸሙን ዐወቅሁ፤ ነገር ግን ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ይግባኝ በማለቱ ልሰደው ወሰንሁ።
26ሆኖም ለንጉሠ ነገሥቱ ለመጻፍ አሳማኝ ነገር የለኝም። በዚህ ምክንያት ስለ ጉዳዩ የምጽፈው ነገር እንዲኖረኝ፣ በተለይ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ።
27አንድን እስረኛ መስደድና የቀረበበትን ክስም አለመግለጽ ለእኔ ምክንያታዊ ያልሆነ ይመስለኛልና።”