መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 24

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዐምስት ቀናት በኋላ፣ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ፣ አንዳንድ ሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ የተባለ አንድ የሕግ ባለ ሙያ ወደዚያ ሄዱ። እነዚህ ሰዎች ለገዡ አመልክተው ጳውሎስን ከሰሱት።
2ጳውሎስ በገዡ ፊት በቆመ ጊዜ፣ ጠርጠሉስ ይከሰው ጀመር፤ ገዡንም እንዲህ አለው፤ «ክቡር ፊልክስ ሆይ፣ በአንተ ምክንያት ብዙ ሰላም አግኝተናል፤ የአንተ ማስተዋልም ለሕዝባችን ጥሩ መሻሻልን ያመጣለታል፤
3ስለ ሆነም አንተ የምታደርገውን ሁሉ በፍጹም ምስጋና እንቀበለዋለን።
4ብዙ እንዳላቈይህ፣ በቸርነትህ በዐጭሩ እንድትሰማኝ እለምንሃለሁ።
5ይህ ሰው ቅንቅን ሆነና በመላው ዓለም ላይ ያሉትን አይሁዶች ሲያሳምፅ አግኝተነዋልና። የናዝራውያን ወገን መሪ ነው።
6ቤተ መቅደሱንም እንኳ ሊያረክስ ሞክሯል፤ ስለዚህ ያዝነው።
7ነገር ግን ወታደራዊው መኰንን ሉስዮስ መጥቶ፣ ጳውሎስን በኀይል ከእጃችን ወሰደው።
8አንተም ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ጳውሎስን በምትጠይቀው ጊዜ ለምን እንደምንከሰው ልታውቅ ትችላለህ።»
9አይሁድም አንድ ላይ ሆነው ጳውሎስን ከሰሱት፤ ነገሮቹም ሁሉ እውነት መሆናቸውን ተናገሩ።
10ገዡ ግን እንዲናገር ሲጠይቀው፣ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ መልስ ሰጠ፤ «አንተ ለብዙ ዓመታት ለዚህ ሕዝብ ፈራጅ መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለ ሆነም ደስ እያለኝ ስለ ራሴ እገልጽልሃለሁ።
11ለማምለክ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከዐሥራ ሁለት ቀን እንደማይበልጥ አንተ መርምረህ ልትደርስበት ትችላለህ፤
12እነርሱ በቤተ መቅደስ ባገኙኝ ጊዜም፣ ከማንም ጋር አልተከራከርሁም፤ በምኵራቦችም ሆነ በከተማው ሕዝብን አልቀሰቀስሁም፤
13አሁን በእኔ ላይ የሚያቀርቡት ክስ እውነተኛ ለመሆኑ ማስረጃ የላቸውም።
14ነገር ግን ለአንተ ይህን እነግርሃለሁ፤ እነርሱ የእምነት ክፍል ብለው እንደሚጠሩት እኔም በዚያ ተመሳሳይ መንገድ የአባቶቻችንን አምላክ አገለግላለሁ። በሕግና በነቢያት ለተጻፈው ሁሉ የታመንሁ ነኝ።
15ልክ እነዚህ ሰዎች ደግሞ እንደሚጠብቁት፣ ስለሚመጣው የሙታን ማለትም የጻድቃንና የኀጥአን ትንሣኤ በእግዚአብሔር ላይ እምነት አለኝ።
16በዚህም በሁሉም ነገር በእግዚአብሕርና በሰዎች ፊት ነቀፋ የሌለበት ኅሊና እንዲኖረኝ እሠራለሁ።
17ከብዙ ዓመታትም በኋላ ለሕዝቤ ርዳታና የገንዘብ ስጦታ ለመስጠት መጣሁ።
18ይህንም ባደረግሁ ጊዜ ከእስያ የሆኑ አንዳንድ አይሁድ፣ ሕዝብም ጩኸትም ሳይኖር በቤተ መቅደስ የመንጻት ሥርዓት ላይ አገኙኝ።
19እነዚህ ሰዎች በእኔ ላይ አንዳች ነገር ካላቸው፣ በፊትህ መጥተው ክሱን ሊያቀርቡብኝ ይገባቸዋል።
20አለበለዚያም፣ እነዚሁ ሰዎች በአይሁድ ሸንጎ ፊት በቆምሁ ጊዜ፣ ምን እንዳጠፋሁ መናገር ነበረባቸው፤
21«ዛሬ አንተ የምትፈርድብኝ ስለ ሙታን ትንሣኤ ነው» ብዬ በመካከላቸው ቆሜ ድምፄን ከፍ በማድረግ ከተናገርሁት ከዚህ አንድ ነገር በቀር፣ ምንም የተናገርሁት የለም።
22ፊልክስ ግን ስለ መንገዱ በሚገባ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሆነም፣ «አዛዡ ሉስዮስ ከኢየሩሳሌም በሚወርድበት ጊዜ ለክሳችሁ ውሳኔ እሰጣለሁ» ብሎ አይሁድን እንዲጠብቁ አደረጋቸው።
23ከዚያም ጳውሎስን እንዲጠብቀው፣ ነገር ግን እንዲያደላለት፣ እርሱንም ከመርዳት ወይም ከመጎብኘት ማንም ወዳጆቹን እንዳይከለክል የመቶ አለቃውን አዘዘው።
24ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ፊልክስ ድሩሲላ ከምትባል አይሁዳዊት ሚስቱ ጋር ተመልሶ መጣ፤ ጳውሎስንም በማስጠራት በክርስቶስ ኢየሱስ ስላለው እምነት ከእርሱ ሰማ።
25ነገር ግን ጳውሎስ ስለ ጽድቅ፣ ራስን ስለ መግዛት፣ ስለሚመጣውም ፍርድ ከእርሱ ጋር በተነጋገረ ጊዜ፣ ፊልክስ ፈራ፤ «ለአሁኑ ሂድ፤ እንደ ገና ጊዜ ሲኖረኝ ግን፣ አስጠራሃለሁ» አለው።
26በዚሁ ጊዜ፣ ጳውሎስ ገንዘብ ይሰጠኛል ብሎ ፊልክስ ተስፋ ያደርግ ነበር፤ ስለዚህ ብዙ ጊዜ እያስጠራ ያነጋግረው ነበር።
27ከሁለት ዓመት በኋላ ግን፣ ከፊልክስ ቀጥሎ ጶርቅዮስ ፊስጦስ ገዢ ሆነ፤ ፊልክስ ግን አይሁድን ለማስደሰት ፈልጎ ጳውሎስን በጥበቃ ሥር እንዲቆይ አደረገ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።