1ጳውሎስም ትኵር አድርጎ ወደ ሸንጎው በመመልከት፣ “ወንድሞች ሆይ፣ እኔ እስካሁን ድረስ፣ በእግዚአብሔር ፊት በንጹሕ ኅሊና ሁሉ ኖሬአለሁ” አለ።
2ሊቀ ካህናቱ ሐናንያም ጳውሎስ አጠገብ የነበሩትን ሰዎች አፉን እንዲመቱት አዘዛቸው።
3በዚህ ጊዜ ጳውሎስ፣ “አንተ ነጭ ቀለም የተቀባህ ግድግዳ፣ እግዚአብሔር ይመታሃል። በሕጉ መሠረት ልትፈርድብኝ የተቀመጥህ፣ ሕጉን ጥሰህ እኔ እንድመታ ታዛለህን?” አለው።
4በአጠገቡ ቆመው የነበሩትም፣ “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት እንዴት ትሰድባለህ?” አሉ።
5ጳውሎስም፣ “ወንድሞች ሆይ፣ ሊቀ ካህናት መሆኑን አላወቅሁም፤ ምክንያቱም፣ በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል ከአፍህ አይውጣ ተብሎ ተጽፎአል።”
6ጳውሎስም ከሸንጎው አባላት ከፊሉ ሰዱቃውያን፣ ሌሎቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን ሲያይ፣ በሸንጎ መካከል ሆኖ በከፍተኛ ድምፅ፣ “ወንድሞች ሆይ፣ እኔ የፈሪሳዊ ልጅ የሆንሁ፣ ፈሪሳዊ ነኝ። ፍርድ ፊት የቀረብሁትም የሙታን ትንሣኤ እንዳለ ስለማምን ነው” አላቸው።
7ይህን በተናገረ ጊዜ፣ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ክርክር ተነሣ፤ ጉባኤውም ተከፋፈለ።
8ምክንያቱም ሰዱቃውያን ትንሣኤ ሙታን የለም፤ መላእክትም የሉም፤ መናፍስትም የሉም ስለሚሉና፣ ፈሪሳውያን ግን እነዚህ ሁሉ አሉ ስለሚሉ ነው።
9በዚህ ጊዜ፣ ታላቅ ውካታ ሆነ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ ጸሐፍትም ተነሥተው፣ “በዚህ ሰው ላይ አንድም ጥፋት አላገኘንም፤ መንፈስ ወይም መልአክ ተናግሮት እንደ ሆነስ ማን ያውቃል?” በማለት ተከራከሩ።
10ክርክሩም እየጋለ ሲሄድ፣ ጳውሎስን ይዘው እንዳይቦጫጭቁት ሻለቃው ፈራ፤ ስለዚህ ወታደሮቹ ወርደው ጳውሎስን በኀይል ይዘው ከሸንጎ አባላት መካከል እንዲወስዱትና ወደ ምሽጉ አምጥተው እንዲያስገቡት አዘዘ።
11በሚቀጥለውም ሌሊት ጌታ በጳውሎስ አጠገብ ቆሞ፣ “አትፍራ፤ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርኸው፣ በሮማም ደግሞ ልትመሰክር ይገባሃል” አለው።
12በነጋም ጊዜ፣ አንዳንድ አይሁድ ጳውሎስን ሳንገድል እኽል ውሃ አንቀምስም በማለት በመሐላ ተስማሙ።
13ይህን የዶለቱትም ሰዎች ቍጥር ከአርባ በላይ ነበር።
14ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎችም ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ጳውሎስን እስከምንገድል ድረስ፣ እኽል እንዳንቀምስ በታላቅ ርግማን ተማምለናል።
15ስለዚህ አሁን ሻለቃው ጳውሎስን ወደ እናንተ እንዲያወርደውና እናንተ የእርሱን ጉዳይ ይበልጥ በትክክል እንደምታዩለት አስመስላችሁ፣ ሸንጎው ለሻለቃው ያመልክት። በእኛ በኩል ግን እዚህ ከመምጣቱ በፊትም ቢሆን ልንገድለው ዝግጁ ነን።”
16የጳውሎስ እኅት ወንድ ልጅም ጳውሎስን አድፍጠው እንደሚጠብቁት ዐወቀ፤ ሄዶም ወደ ምሽጉ ገብቶ ለጳውሎስ ነገረው።
17ጳውሎስም አንዱን መቶ አለቃ ጠራና፣ “ይህን ወጣት ወደ ሻለቃው ውሰደው፤ የሚናገረው ነገር አለውና” አለ።
18መቶ አለቃውም ወጣቱን ይዞ ወደ ሻለቃው አመጣውና እንዲህ አለ፤ “ጳውሎስ የተባለው እስረኛ ወደ ራሱ ጠርቶኝ፣ ይህን ወጣት ወደ አንተ እንዳቀርበው ለመነኝ፤ ወጣቱ ለአንተ የሚነግርህ ነገር አለው።”
19ሻለቃውም እጁን ይዞ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ ወስዶት፣ “ልትነግረኝ የፈለግኸው ነገር ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀው።
20ወጣቱም እንዲህ አለ፤ “አይሁድ ስለ ጉዳዩ ትክክለኛነት ይበልጥ ለመረዳት የፈለጉ አስመስለው፣ ነገ ጳውሎስን ወደ ሸንጎው እንድታወርደው አንተን ለመለመን ተስማምተዋል።
21ነገር ግን እሺ አትበላቸው፤ ምክንያቱም ከአርባ በላይ የሚሆኑ ሰዎች አድፍጠው እየጠበቁት ነው። ጳውሎስን ካልገደሉም እኽል ውሃ እንደማይቀምሱ ተማምለዋል። አሁንም እንኳ የአንተን መስማማት እየጠበቁ ነው እንጂ ዝግጁ ናቸው።”
22ስለዚህ ሻለቃው ወጣቱን ልጅ፣ “ስለ እነዚህ ነገሮች ለእኔ መግለጥህን ለማንም እንዳትናገር” ብሎ ካስጠነቀቀው በኋላ፣ አሰናበተው።
23ከመቶ አለቆቹም ሁለቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ “እስከ ቄሣርያ ለመሄድ የሚችሉ ሁለት መቶ ወታደሮችን፣ ሰባ ፈረሰኞችንና ሁለት መቶ ባለ ጦሮችን አዘጋጁ፤ ከሌሊቱም በሦስተኛው ሰዓት ትንቀሳቀሳላችሁ” አላቸው።
24ጳውሎስ ወደ ሀገረ ገዡ፣ ወደ ፊልክስ የሚሄድበትንም ከብት እንዲያዘጋጁና በሰላም እንዲያደርሱት አዘዛቸው።
25ከዚያም እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፈ፤
26“ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ፣ ወደ ተከበረው ሀገረ ገዢ ፊልክስ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን።
27ይህን ሰው አይሁድ ይዘው ሊገድሉት ሲሉ፣ ከወታደሮች ጋር ደርሼባቸው አዳንሁት፤ ይህን ያደረግሁትም ሮማዊ ዜጋ መሆኑን ስለ ተረዳሁ ነው።
28ለምን እንደ ከሰሱት ለማወቅ ስለ ፈለግሁም፣ ወደ ሸንጎአቸው ይዤው ወረድሁ።
29የገዛ ራሳቸውን ሕግ በሚመለከት በተነሣ ጥያቄ ምክንያት ተከሶ እንጂ፣ ሞት ወይም እስራት የሚገባው ክስ እንደሌለበት ዐውቄአለሁ።
30በዚህ ሰው ላይ ሤራ እንደ ተካሄደበትም ደርሼበታለሁ፤ ስለዚህም ፈጥኜ ወደ አንተ ላክሁት፤ ከሳሾቹም በእርሱ ላይ ያላቸውን ክስ አንተ ባለህበት እንዲያቀርቡ መመሪያ ሰጥቻቸዋለሁ። በደኅና ሰንብት።”
31ስለዚህ ወታደሮቹ በታዘዙት መሠረት፣ ጳውሎስን ይዘው በሌሊት ወደ አንቲጳጥሪስ ወሰዱት።
32በሚቀጥለውም ቀን፣ አብዛኞቹ ወታደሮች ፈረሰኞቹን ከእርሱ ጋር እንዲሄዱ ትተው፣ ወደ ምሽግ ተመለሱ።
33ፈረሰኞቹም ቂሣርያ በደረሱና ደብዳቤውን ለሀገር ገዡ ሲሰጡ፣ ጳውሎስንም ለእርሱ አስረከቡት።
34ሀገረ ገዡም ደብዳቤውን ካነበበ በኋላ፣ ጳውሎስ ከየትኛው አውራጃ እንደ መጣ ጠየቀ፤ ከኪልቅያ እንደ መጣ ባወቀ ጊዜም፣
35“ከሳሾችህ ወደዚህ ሲመጡ፣ በሚገባ እሰማሃለሁ” አለው። ከዚያም በኋላ፣ በሄሮድስ ቅጥር ግቢ እንዲጠብቁት አዘዘ።