መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 22

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1“ወንድሞችና አባቶች ሆይ፣ አሁን ስለ ራሴ ለእናንተ የማቀርበውን መከላከያ አድምጡኝ።”
2ሕዝቡም ጳውሎስ በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲያናግራቸው በሰሙ ጊዜ፣ ጸጥ አሉ። ጳውሎስም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤
3“እኔ በኪልቅያዋ ጠርሴስ የተወለድሁ አይሁዳዊ ነኝ፤ የተማርሁትም በዚሁ ከተማ በገማልያል እግር ሥር ተቀምጬ ነው። የአባቶቻችንንም ጥብቅ የሕግ መንገድ በሚገባ ተምሬአለሁ። ዛሬ እናንተ ሁላችሁ እንደ ሆናችሁት፣ እኔም ለእግዚአብሔር ቀናተኛ ነኝ።
4ይህን መንገድ እስከ ሞት አሳድጄዋለሁ፤ ሴቶችንና ወንዶችን አስሬ ለወኅኒ አሳልፌ ሰጠኋቸው።
5ደግሞም ከእነርሱ ደብዳቤ ተቀብዬ፣ በደማስቆ ስለሚገኙ ወንድሞች ወደዚያ ለመጓዝ እንደ ተነሣሁ፣ ሊቀ ካህናቱና ሽማግሌዎች ሁሉ መመስከር ይችላሉ። ከዚያ መንገድ የሆኑትን አስሬ ወደ ኢየሩሳሌም ለመምጣትና ለማስቀጣት ስንቀሳቀስም ነበር።
6እየተጓዝሁ ወደ ደማስቆ ስቃረብ፣ ቀትር ላይ ድንገት ታላቅ ብርሃን ከሰማይ በዙሪያዬ በራ፤
7እኔም መሬት ላይ ወደቅሁ፤ ከዚያም፣ 'ሳውል፣ ሳውል፣ ለምን ታሳድደኛለህ?' የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ።
8እኔም፣ 'ጌታ ሆይ፣ አንተ ማን ነህ?' ብዬ መለስሁለት። እርሱም፣ 'አንተ የምታሳድደኝ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ' አለኝ።
9ከእኔ ጋር የነበሩትም ብርሃኑን አዩ፤ ነገር ግን የተናገረኝን ድምፅ አልሰሙም።
10እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፣ ምን ላድረግ?’ አልሁ። ጌታም፣ ‘ተነሥና ወደ ደማስቆ ሂድ፤ ማድረግ የሚገባህን ሁሉ እዚያ ይነግሩሃል’ አለኝ።
11ከዚያ ብርሃን ድምቀት የተነሣም አንዳች ማየት አልቻልሁም፤ ስለዚህ ከእኔ ጋር በነበሩት ሰዎች እጅ እየተመራሁ ወደ ደማስቆ ገባሁ።
12ለሕጉ በትጋት የሚታዘዝና በዚያ የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ መልካምነቱን የመሰከሩለት፣ ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው አገኘሁ።
13እርሱም ወደ እኔ መጥቶ አጠገቤ በመቆም፣ ‘ወንድሜ ሳውል፣ ዐይንህን ገልጠህ እይ’ አለኝ። እኔም በዚያው ቅጽበት አየሁት።
14እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘ቅዱሱን እንድታይና ከገዛ አፉ የሚወጣውን ድምፅ እንድትሰማ፣ የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን እንድታውቅ መርጦሃል፤
15ምክንያቱም ስለ አየኸውና ስለ ሰማኸው ነገር ለሰዎች ሁሉ ምስክር ትሆንለታለህ።
16ስለዚህ አሁን ለምን ታመነታለህ? ተነሥ፤ ስሙን እየጠራህ ተጠመቅና ከኃጢአትህ ታጠብ።’
17ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለስሁ በኋላም፣ በቤተ መቅደስ እየጸለይሁ ሳለሁ፣ ሸለብ አድርጎኝ ሰመመን ውስጥ ገባሁ።
18እርሱም፣ ‘ከኢየሩሳሌም ቶሎ ብለህ ውጣ፤ ምክንያቱም ስለ እኔ የምትናገረውን ምስክርነትህን አይቀበሉህም’ ሲለኝ አየሁ።
19እኔም እንዲህ አልሁ፤ ‘ጌታ ሆይ፣ በምኵራብ ሁሉ በአንተ ያመኑትን ሳስርና ስደበድብ እንደ ነበርሁ እነርሱ ራሳቸው ያውቃሉ።
20የሰማዕትህን የእስጢፋኖስንም ደም በሚያፈሱበት ጊዜ፣ በመስማማት እዚያው ቆሜ ነበር፤ የገዳዮቹንም ልብሶች እጠብቅ ነበር።’
21እርሱ ግን፣ ‘ተነሥተህ ሂድ፤ ምክንያቱም ወደ አሕዛብ እልክሃለሁ’ አለኝ።”
22ሕዝቡም እስከዚህ ድረስ እንዲናገር ፈቀዱለት፤ ከዚህ በኋላ ግን፣ “እንደዚህ ያለ ሰው ከምድር ይወገድ፤ በሕይወትም ይኖር ዘንድ አይገባውም” እያሉ ይጮኹ ጀመር።
23እየጮኹም ሳለ፣ ልብሳቸውን እያወለቁና አቧራም ወደ ላይ ይበትኑ ነበር፤
24ሻለቃውም ጳውሎስን ወደ ወታደራዊው ምሽግ እንዲወስዱት አዘዘ። እርሱ ራሱ ሕዝቡ ለምን እንደዚያ እንደ ጮኹበት ለማወቅ ስለ ፈለገ፣ እየገረፉ ጳውሎስን እንዲመረምሩት ትእዛዝ ሰጠ።
25ሰዎቹ በጠፍር ወጥረው ባሰሩት ጊዜ፣ ጳውሎስ በአጠገቡ የቆመውን መቶ አለቃ፣ “ሮማዊ የሆነን ሰው፣ ገና ሳይፈረድበት እንዲህ መግረፍህ ሕጋዊ ነው ወይ?” አለው።
26መቶ አለቃውም ይህን ሲሰማ፣ ወደ ሻለቃው ሄዶ፣ “ምን ማድረግህ ነው? ሰውየውኮ የሮማ ዜጋ ነው” በማለት ነገረው።
27ሻለቃውም መጥቶ፣ “አንተ የሮማ ዜጋ ነህን? እስቲ ንገረኝ” አለው። ጳውሎስም፣ “አዎ፣ ነኝ” አለ።
28ሻለቃውም፣ “እኔኮ ይህን ዜግነት ያገኘሁት በብዙ ገንዘብ ነው” ብሎ መለሰለት። ጳውሎስም፣ “እኔ ግን ከመወለዴ ጀምሮ ሮማዊ ነኝ” አለ።
29ሊመረምሩት የመጡ ሰዎችም ወዲያው ትተውት ሄዱ። ሻለቃውም ጳውሎስ የሮም ዜጋ መሆኑን ባወቀ ጊዜ ፈራ፤ ምክንያቱም ጳውሎስን አሳስሮት ነበር።
30በማግስቱም ሻለቃው፣ አይሁድ ጳውሎስን የከሰሱበትን ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅ ፈለገ። ስለዚህ ጳውሎስን ከእስራት አስፈታውና የካህናት አለቆችና ሸንጎው በሙሉ እንዲሰበሰቡ አዘዘ። ከዚያም ጳውሎስን አስመጥቶ በመካከላቸው አቆመው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።