1ከእነርሱም ተለይተን የባሕር ላይ ጕዞአችንን በቀጠልን ጊዜ፣ ቀጥታ ወደ ቆስ ከተማ አመራን፤ በማግስቱም ወደ ሩድ ከተማ፣ ከዚያም ወደ ጳጥራ ከተማ ሄድን።
2ወደ ፊንቄ የሚሻገር መርከብ ባገኘን ጊዜም ተሳፍረን መጓዝ ጀመርን።
3የቆጵሮስን ደሴት ከሩቅ ባየን ጊዜ፣ ወደ ግራ ትተናት በባሕር ወደ ሶርያ ተጓዝን፤ መርከብዋ ጭነቷን የምታራግፈው በዚያ ስለ ነበር፣ ጢሮስ ወደብ ላይ ደረስን።
4ደቀ መዛሙርቱን ካገኘን በኋላም፣ በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን። እነዚህም ደቀ መዛሙርት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይገባ በመንፈስ ቅዱስ ተናገሩት።
5የምንቈይበት ጊዜ ሲገባደድ፣ ተነሥተን ጕዞአችንን ቀጠልን። ሁሉም፣ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ከከተማ እስክንወጣ ድረስ በመንገዳችን ሸኙን። ከዚያም እወደቡ ላይ ተንበርክከን ጸለይን፤ እርስ በርስም ተሰነባበትን።
6እኛ በመርከቡ ተሳፈርን፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመልሰው ሄዱ።
7ከጢሮስ የተነሣንበትን ጕዞ በጨረስን ጊዜ፣ አካ ደረስን። በዚያም ወንድሞችን አገኘንና አንድ ቀን ከእነርሱ ጋር ቈየን።
8በሚቀጥለው ቀን ከዚያ ተነሥተን ወደ ቂሣርያ ሄድን። ከዚያም ከሰባቱ አንዱ ወደ ሆነው፣ ወደ ወንጌል ሰባኪው ወደ ፊልጶስ ቤት ገብተን ከእርሱ ጋር ሰነበትን።
9ይህም ሰው ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት።
10የተወሰኑ ቀናት እንደ ተቀመጥንም፣ አጋቦስ የሚሉት ነቢይ ከይሁዳ ወደ ነበርንበት ወረደ።
11ወደ እኛም መጥቶ፣ የጳውሎስን መታጠቂያ ወሰደ፤ የገዛ ራሱን እጆችና እግሮችም አስሮ፣ “መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ ‘በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁድ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት እንደዚህ አድርገው ያስሩታል፤ አሳልፈውም ለአሕዛብ እጅ ይሰጡታል’” አለ።
12እነዚህን ነገሮች በሰማን ጊዜ፣ እኛና በዚያ ስፍራ የሚኖሩ ሰዎችም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው።
13ጳውሎስም፣ “እያለቀሳችሁ ልቤን የምትሰብሩት ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔኮ መታሰር ብቻ ሳይሆን፣ ለጌታችን ለኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት ዝግጁ ነኝ” ብሎ መለሰ።
14ጳውሎስ ምክር ለመቀበል እንዳልፈለገ በተረዳን ጊዜ፣ “የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን መለመኑን አቆምን።
15ከእነዚህ ቀናት በኋላ፣ እኛም የጕዞ ዕቃዎቻችንን ይዘን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን።
16ደግሞም ከቂሣርያ የነበሩ አንዳንድ ደቀ መዛሙርት ከእኛ ጋራ መጡ። ምናሶን የሚባለውንም ሰው ይዘውት መጡ፤ እርሱም የቆጵሮስ ሰው፣ ወደ ፊት ከእርሱ ጋር እንድንቀመጥ የታሰበ የቀድሞ ደቀ መዝሙር ነበረ።
17ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ፣ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን።
18በማግስቱም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ሄደ፤ ሽማግሌዎችም ሁሉ በዚያ ነበሩ።
19ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ፣ እግዚአብሔር በእርሱ አገልግሎት አማካይነት በአሕዛብ መካከል የሠራቸውን ነገሮች አንድ በአንድ ዘርዝሮ ነገራቸው።
20እነርሱም ስለ ሰሙት ነገር እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ እንዲህም አሉት፤ “ወንድም ሆይ፣ ከአይሁድ ያመኑት ስንትና ስንት ሺህ እንደ ሆኑ ታያለህ። ሁላቸውም ሕግን ለመጠበቅ የወሰኑ ናቸው።
21በአሕዛብ መካከል የሚኖሩት አይሁድ ሁሉ ሙሴን እንዲተዉ እንደምታስተምራቸው፣ ልጆቻቸውንም እንዳይገርዙ እንደምትነግራቸውና በቀድሞው ልማድ እንዳይሄዱ እንደምታደርግ፣ ስለ አንተ ተነግሮአቸዋል።
22እንግዲህ ምን እናድርግ? መምጣትህን እንደሚሰሙ ርግጠኞች ነን።
23ስለዚህ አሁን እኛ የምንልህን አድርግ፤ ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች እዚህ አሉን።
24እነዚህን ሰዎች ይዘህ ከእነርሱ ጋር ራስህን አንጻ፤ ጠጕራቸውን ለመላጨት የሚያስፈልጋቸውንም ገንዘብ ክፈልላቸው። በዚህም ስለ አንተ የተነገራቸው ሁሉ ውሸት እንደ ሆነ ያውቃሉ፤ አንተም ልማዱን ጠብቀህ እንደምትኖር ይረዳሉ።
25ስላመኑ አሕዛብ ግን ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደም፣ ከታነቀ፣ እንዲሁም ከዝሙት ራሳቸውን እንዲጠብቁ ጽፈን ትእዛዝ ሰጥተናል።”
26ጳውሎስም ሰዎቹን ይዞ በሚቀጥለው ቀን ራሱን ከእነርሱ ጋር እያነጻ ወደ መቅደሱ ገባ፤ ይኸውም መሥዋዕቱ ስለ እያንዳንዳቸው እስከሚቀርብ ድረስ መንጻቱ የሚወስደውን ጊዜ በመንገር ነው።
27ሰባቱ ቀናት ወደ መገባደዱ ሲቃረቡ፣ ከእስያ የመጡ አንዳንድ አይሁድ ጳውሎስን በቤተ መቅደስ ውስጥ አዩት፤ ሕዝቡንም ሁሉ በእርሱ ላይ አነሣሡ፤ ያዙትም።
28እንዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ርዱን። ሰዎችን ሁሉ ከሕዝቡ፣ ከሕጉና ከዚህ ስፍራ ጋር የማይስማሙ ነገሮችን የሚያስተምር ይህ ሰው ነው። ከዚህም በላይ የግሪክን ሰዎች ወደ ቤተ መቅደሱ በማስገባት፣ ይህን ቅዱስ ስፍራ የሚያረክሰውም እርሱ ነው።”
29ምክንያቱም ቀደም ሲል የኤፌሶኑን ሰው ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ ስላዩት፣ ጳውሎስ ወደ ቤተ መቅደስ ያስገባው መሰላቸው።
30ከተማውም ሁሉ ታወከ፤ ሕዝቡም በአንድነት ተሰባስበው ጳውሎስን ያዙት፤ ጐትተውም ከቤተ መቅደስ አስወጡት፤ በሮቹም ወዲያው ተዘጉ።
31ሊገድሉት ሲሞክሩም፣ መላዋ ኢየሩሳሌም እጅግ ታውካለች የሚል ወሬ ወደ ጭፍሮቹ አለቃ ደረሰ።
32እርሱም ወዲያው ወታደሮችንና የመቶ አለቆችን ይዞ ሕዝቡ ወዳሉበት በሩጫ ወረደ። ሰዎቹም ሻለቃውንና ወታደሮችን ሲያዩ፣ ጳውሎስን መደብደብ አቆሙ።
33ከዚያም ሻለቃው ወደ ጳውሎስ ሄዶ ያዘው፤ በሁለት ሰንሰለቶች እንዲታሰርም አዘዘ። ስለ ማንነቱና ስለ ፈጸመው ድርጊትም ጠየቀው።
34ከሕዝቡም ግማሾቹ ስለ አንድ ነገር ሲጮኹ፣ የቀሩት ደግሞ ስለ ሌላ ነገር ይንጫጩ ነበር። ሻለቃውም ከጫጫታው ሁሉ የተነሣ፣ ስለ ምን እንደሚጮኹ እንኳ መለየት አልቻለም፤ ስለዚህ ጳውሎስን ወደ ወታደሮች ምሽግ እንዲያገቡት አዘዘ።
35ጳውሎስ ወደ መወጣጫው ደረጃ በደረሰ ጊዜ፣ ከሕዝቡ ረብሻ የተነሣ፣ ወታደሮቹ ተሸክመውት ሄዱ።
36ሕዝቡ “አስወግደው!” እያሉና እየጮኹ ከኋላ ይከተሉ ነበር።
37ጳውሎስም ወደ ምሽጉ ሊገባ ጥቂት ሲቀረው፣ ሻለቃውን፣ “አንድ ነገር እንድናገርህ ትፈቅድልኛለህ?” አለው። ሻለቃውም፣ “የግሪክ ቋንቋ መናገር ትችላለህ ወይ?
38አንተ ከዚህ በፊት ዐመፅ አስነሥተህ፣ አራት ሺህ ሰዎችን በማስሸፈት፣ ወደ ምድረ በዳ የገባህ ግብፃዊ አይደለህምን?” አለው።
39ጳውሎስም፣ “እኔስ በኪልቅያ ከምትገኘው ከጠርሴስ ከተማ የመጣሁ አይሁዳዊ ነኝ፤ የታዋቂዋ ከተማ ዜጋ ነኝ። አንድ ነገር እለምንሃለሁ፤ ለሰዎቹ እንድናገር ፍቀድልኝ” አለው።
40ሻለቃው በፈቀደለት ጊዜም፣ ጳውሎስ መወጣጫ ደረጃው ላይ ቆሞ፣ በእጁ ወደ ሕዝቡ አመለከተ። ሕዝቡ ጸጥ እረጭ ሲልም፣ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦