መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 20

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ሁከቱ ካበቃ በኋላ፣ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስጠርቶ አበረታታቸው። ከዚያም ተሰናበታቸውና ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ተነሣ።
2በእነዚያም አካባቢዎች እያለፈ ያመኑትን እጅግ ካበረታታ በኋላ፣ ወደ ግሪክ ገባ።
3በዚያም ሦስት ወር ከቈየ በኋላ፣ ወደ ሶርያ በመርከብ ለመሄድ እያሰበ ሳለ፣ አይሁድ አሤሩበት፤ ስለዚህ በመቄዶንያ አድርጎ ለመመለስ ወሰነ።
4እስከ እስያ የሸኙትም የቤርያው ሱሲጳጥሮስ፣ ከተሰሎንቄ የመጡት አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ፣ የደርቤኑ ጋይዮስ፣ ጢሞቴዎስ፣ እንዲሁም ከእስያ የመጡት ቲኪቆስና ጥሮፊሞስ ነበሩ።
5እነዚህ ሰዎች ግን ቀድመውን በጢሮአዳ ጠበቁን።
6እኛም ከቂጣ በዓል ቀን በኋላ፣ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሥተን በዐምስት ቀን ውስጥ ጢሮአዳ ደረስንባቸው፤ እዚያም ሰባት ቀን ተቀመጥን።
7በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቊረስ በተሰበሰብን ጊዜ፣ ጳውሎስ ለምእመናኑ ንግግር አደረገ። በሚቀጥሉት ቀናት ለመሄድ ዐቅዶ ስለ ነበረ፣ እስከ እኩለ ሌሊት መናገሩን ቀጠለ።
8በተሰበሰብንበትም ሰገነት ላይ ብዙ መብራቶች ነበሩ።
9አውጤኪስ የሚባል ወጣትም በመስኮት ተቀምጦ ሳለ፣ እንቅልፍ ጭልጥ አድርጎ ወሰደው። ጳውሎስ ንግግሩን ባስረዘመ ጊዜ፣ ይህ ወጣት ገና ተኝቶ እንዳለ ከሦስተኛው ፎቅ ወደቀ፤ ሲያነሡትም ሞቶ ነበር።
10ጳውሎስ ግን ወርዶ በላዩ ተዘረጋበት፣ ዐቀፈውም። ከዚያም፣ “በሕይወት ስላለ ከዚህ በኋላ አትታወኩ” አለ።
11እንደ ገናም በደረጃ ወደ ላይ ወጣ፤ እንጀራ ቈርሶም በላ። እስኪነጋ ድረስም ለረዥም ጊዜ ከእነርሱ ጋር ከተነጋገረ በኋላ፣ ተለይቶአቸው ሄደ።
12ወጣቱንም በሕይወት እያለ አመጡት፤ በዚህም እጅግ ተጽናኑ።
13እኛም ራሳችን ጳውሎስን በመርከብ ለማሳፈር ወዳሰብንበት ወደ አሶን ቀድመን በመርከብ ሄድን። እርሱም ያሰበው ይህንኑ ነበር፤ በመርከብ ለመሄድ ዐቅዶ ነበርና።
14በአሶን ሲያገኘንም፣ ወዳለንበት መርከብ አስገብተነው ወደ ሚሊጢን ጕዞአችንን ቀጠልን።
15ከዚያም በመርከብ ተነሣንና በማግስቱ ኪዩ በምትባለዋ ደሴት ትይዩ ደረስን። በሚቀጥለውም ቀን ወደ ሳሞን ደሴት ጎራ ብለን፣ በማግስቱ ወደ ሚሊጢን ከተማ ገባን፤
16ጳውሎስም በእስያ ውስጥ ጊዜ ሳያባክን፣ ኤፌሶንን ዐልፎ በመርከብ ለመሄድ ወስኖ ነበርና፤ ምክንያቱም በተቻለው መጠን ሁሉ ለበዓለ ኀምሳ በኢየሩሳሌም ለመገኘት ቸኵሎ ነበር።
17ሰዎችንም ከሚሊጢን ወደ ኤፌሶን ልኮ፣ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ወደ ራሱ አስጠራቸው።
18ወደ እርሱ በመጡም ጊዜ፣ እንዲህ አላቸው፤ “ወደ እስያ ከገባሁበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ፣ ዘወትር እንዴት ከእናንተ ጋር እንደ ኖርሁ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።
19ራሴን እጅግ ዝቅ በማድረግና በእንባ፣ ከአይሁድ ሤራ የተነሣ በገጠመኝ መከራም ውስጥ ጌታን ማገልገል አላቋረጥሁም።
20ጠቃሚ የሆነውን ነገር ሁሉ ለእናንተ ከመግለጽና በአደባባይም ሆነ ቤት ለቤት በመዞር እናንተን ከማስተማር ወደ ኋላ እንዳላልሁ ታውቃላችሁ።
21በንስሓ ወደ እግዚአብሔር ስለ መመለስና በጌታችን በኢየሱስ ስለ ማመን አይሁድንና ግሪኮችን እንዴት ሳስጠነቅቃቸው እንደ ነበር ታውቃላችሁ።
22እንግዲህ ተመልከቱ፤ እዚያ ምን እንደሚጠብቀኝ ሳላውቅ፣ በመንፈስ ቅዱስ ታስሬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፤
23ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ እስራትና መከራ እንደሚቆየኝ በየከተማው ይመሰክርልኛል።
24ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ኢየሱስ የተቀበልሁትን የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎት እስከምጨርስ ድረስ፣ እንደ ውድ ነገር በመቍጠር፣ ለሕይወቴ አልሳሳላትም።
25እንግዲህ ተመልከቱ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበክሁ በመካከላችሁ የዞርሁትን የእኔን ፊት ሁላችሁ ዳግመኛ እንደማታዩ ዐውቃለሁ።
26ስለዚህ ከማንም ሰው ደም ንጹሕ እንደ ሆንሁ ዛሬ እመሰክርላችኋለሁ፤
27ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሁሉ ለእናንተ ከመግለጽ ወደ ኋላ ብዬ አላውቅም።
28ስለዚህ በገዛ ራሱ ደም የገዛትን የጌታን ጉባኤ ትጠብቁ ዘንድ፣ ስለ ራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ጠባቂ አድርጎ እናንተን ለሾመበት፣ ለመንጋው ሁሉ ተጠንቀቁ።
29እኔ ከሄድሁ በኋላ፣ ለመንጋው ርኅራኄ የሌላቸው አጥፊ ተኵላዎች በመካከላችሁ እንደሚገቡ ዐውቃለሁ።
30ከእናንተ መካከልም እንኳ ደቀ መዛሙርትን የራሳቸው ተከታዮች ለማድረግ አንዳንድ ሰዎች መጥተው ጠማማ ነገሮችን እንደሚናገሩ ዐውቃለሁ።
31ስለዚህ ተጠንቀቁ። ሳላቋርጥ ቀንና ሌሊት፣ ሁላችሁንም ሦስት ዓመት በእንባ እንዳገለገልኋችሁም አስታውሱ።
32አሁንም ለእግዚአብሔርና ሊያንጻችሁ፣ እንዲሁም በቅዱሳን ሁሉ መካከል ርስትን ሊሰጣችሁ ለሚችለው ለጸጋው ቃል ዐደራ እሰጣችኋለሁ።
33የማንንም ብር፣ ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም።
34እነዚህ እጆቼ የእኔንም፣ ከእኔ ጋር የነበሩትንም ሰዎች ፍላጎት ሲያሟሉ እንደ ነበር እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።
35ደካሞችን በሥራ እንዴት እንደምትረዱ፣ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ የተባረከ ነው” የሚለውንም የጌታ ኢየሱስን ቃል እንዴት እንደምታስታውሱ በሁሉም ረገድ አርኣያ ሆንኋችሁ።
36ጳውሎስ ይህን ሁሉ ካለ በኋላ፣ ተንበርክኮ ከሁሉም ጋር ጸለየ።
37ሁሉም እጅግ በማልቀስ ዐንገቱ ላይ ተጠምጥመው ሳሙት።
38ፊቱን ዳግመኛ እንደማያዩ መናገሩም ከሁሉ በላይ አሳዘናቸው። ከዚያም እስከ መርከቡ ድረስ ሸኙት።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።