መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 19

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አጵሎስ በቆሮንቶስ በነበረ ጊዜ፣ ጳውሎስ በላይኛው አገር አድርጎ ወደ ኤፌሶን ከተማ መጣ፤ በዚያም አንዳንድ ደቀ መዛሙርትን አገኘ።
2ጳውሎስም፣ “ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀብላችኋል?” አላቸው። እነርሱም፣ “አልተቀበልንም፤ እንዲያውም መንፈስ ቅዱስ መኖሩን አልሰማንም” አሉት።
3ጳውሎስም፣ “ታዲያ፣ በምን ተጠመቃችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “የተጠመቅነው በዮሐንስ ጥምቀት ነው” አሉት።
4ጳውሎስም መልሶ፣ “ዮሐንስ ያጠመቀው በንስሓ ጥምቀት ነው። ሰዎች ከእርሱ በኋላ በሚመጣው፣ በኢየሱስ ማመን እንደሚገባቸውም ነገራቸው” አለ።
5ሕዝቡ ይህን ሲሰሙ፣ በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠመቁ።
6ጳውሎስም እጆቹን በሰዎቹ ላይ በጫነ ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ እነርሱም በልዩ ቋንቋ መናገርና መተንበይ ጀመሩ።
7ቍጥራቸውም ዐሥራ ሁለት ያህል ነበረ።
8ጳውሎስ ከዚህ በኋላ ወደ ምኵራብ እየገባ ሦስት ወር ያህል በድፍረት ይናገር ነበር፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየገለጠ ሰዎችን ያስረዳ ነበር።
9አንዳንድ አይሁድ ግን ልባቸውን አደንድነው በመቃወም፣ በሕዝቡ ፊት የክርስቶስን መንገድ ተሳደቡ፤ ስለዚህ ጳውሎስ ትቶአቸው ሄደ፤ ያመኑትንም ከእነርሱ አራቀ። ጢራኖስ በሚባል የትምህርት አዳራሽም በየዕለቱ ንግግር ያደርግ ጀመር።
10ይህም፣ በእስያ የሚኖሩ አይሁድና ግሪኮችም ሁሉ የጌታን ቃል እስኪሰሙ ድረስ፣ ሁለት ዓመት ቀጠለ።
11እግዚአብሔር በጳውሎስ እጅ ታላላቅ ተአምራትን ያደርግ ነበር፤
12ስለዚህ የጳውሎስ አካል የነካው ጨርቅ ወይም መሐረብ ሲወሰድ፣ የታመሙት ይፈወሱ፣ አጋንንትም ከሰዎች ይወጡ ነበር።
13አጋንንት እናስወጣለን እያሉ ከቦታ ቦታ የሚዞሩ አይሁድ ነበሩ፤ እነርሱም የኢየሱስን ስም ለገዛ ጥቅማቸው ለማዋል፣ በክፉ መናፍስት ላይ እየጠሩ፣ “እንድትወጡ ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናዛችኋለን” ይሉ ነበር።
14ይህን ያደረጉትም የአይሁድ የካህናት አለቃ የነበረው የአስቄዋ ሰባት ወንድ ልጆች ነበሩ።
15ክፉው መንፈስም፣ “ኢየሱስን ዐውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም ዐውቃለሁ፤ ለመሆኑ እናንተ እነማን ናችሁ?” ብለው መለሱላቸው።
16ክፉ መንፈስ ያለበትም ሰው ዘሎ ያዛቸው፤ አሸንፏቸውም ደበደባቸው። ከዚያም ቤት ቈስለው ዕራቁታቸውን ሸሹ።
17ይህም በኤፌሶን ይኖሩ በነበሩ አይሁድና ግሪኮችም ዘንድ ሁሉ ታወቀ። እነርሱም ሁሉ በፍርሀት ተዋጡ፤ የጌታ ኢየሱስም ስም ተከበረ።
18ደግሞም ካመኑት ብዙዎቹ መጥተው ቀደም ሲል ያደረጉትን ክፉ ነገር ሳይሸሽጉ ይናዘዙ ነበር።
19አስማተኞችም የጥንቈላ መጻሕፍታቸውን ሰብስበው እያመጡ በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉ፤ ዋጋቸውም ሲተመን ሃምሳ ሺህ ብር ሆነ።
20በዚህም መሠረት የጌታ ቃል በስፋትና በኀይል ተሠራጨ።
21ጳውሎስ በኤፌሶን የነበረውን አገልግሎቱን ከፈጸመ በኋላ፣ በመቄዶንያና በአካይያ አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በመንፈስ ቅዱስ ሆኖ ወሰነ፤ ደግሞም፣ “እዚያ ከደረስሁ በኋላም፣ ሮሜን ማየት ይገባኛል” አለ።
22ሲረዱት ከነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን፣ ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን ወደ መቄዶንያ ላካቸው። እርሱ ራሱ ግን ጥቂት ጊዜ በእስያ ቆየ።
23በዚህ ጊዜ የጌታን መንገድ በተመለከተ በኤፌሶን ትልቅ ሁከት ተነሣ።
24ድሜጥሮስ የሚባል አንድ ብር ሠሪም የዲያናን ምስል ከብር እያበጀ ለአንጥረኞች ትልቅ ገቢ ያስገኝላቸው ነበር።
25ስለዚህ በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩትን ብዙ ሠራተኞች አንድ ላይ ሰብስቦ፣ “ሰዎች ሆይ፤ በዚህ ሙያችን ብዙ ገንዘብ እንደምናገኝ ታውቃላችሁ።
26ይህ ጳውሎስ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን፣ ከብዙ በጥቂቱ በእስያ ሁሉ አብዛኛውን ሕዝብ በቃላት እያባበለ ከእኛ ማራቁን እያያችሁና እየሰማችሁ ነው። በእጅ የሚሠሩ አማልክት የሉም እያላቸው ነው።
27የእኛ ሞያዊ ጥበብ አላስፈላጊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የታላቅዋ አምላክ የዲያና ቤተ መቅደስም እንደ ከንቱ ነገር የመቍጠር አደጋ ያሠጋል፤ እስያ ሁሉና ዓለሙ የሚያመልካት ይህች አምላክም ዝናዋን ታጣለች።”
28ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ በቍጣ ተሞልተው፣ “የኤፌሶንዋ ዲያና ታላቅ ናት” እያሉ ጮኹ።
29ከተማው ሁሉ ድብልቅልቁ ወጣ፤ ሕዝቡም በአንድ ላይ ገንፍለው ወደ ቲያትር ማሳያው ቦታ ገቡ። ከመቄዶንያ የመጡትንም የጳውሎስን የጕዞ ባልደረቦች፣ ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ያዙአቸው።
30ጳውሎስ ወደ ሕዝቡ ሊደባለቅ ፈልጎ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ከለከሉት።
31ደግሞም፣ የጳውሎስ ወዳጆች የነበሩ አንዳንድ የአካባቢ ሹሞች ጳውሎስ ወደ ቲያትር ማሳያ ቦታ እንዳይገባ መልእክት ላኩበት።
32ሕዝቡ ሁሉ ግራ ተጋብቶ ነበርና፣ አንዳንዶቹ ስለ አንድ ነገር ሲጮኹ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ስለ ሌላ ነገር ይጮኹ ነበር። አብዛኛዎቹ ደግሞ ለምን ተሰብስበው እንደ ወጡ እንኳ አያውቁም ነበር።
33አይሁድም እስክንድሮስን ገፋፍተው ወደ ሕዝቡ ፊት አወጡት። እስክንድሮስ ለሕዝቡ በእጅ ምልክት እያሳየ ሊያስረዳቸው ሞከረ።
34ሕዝቡም አይሁዳዊ መሆኑን በተረዱ ጊዜ ሁሉም በአንድ ድምፅ፣ “የኤፌሶንዋ ዲያና ታላቅ ናት” እያሉ ለሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ።
35የከተማዋ ጸሓፊ ሕዝቡን ዝም ካሰኘ በኋላ፣ እንዲህ አለ፤ “እናንተ የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፣ የኤፌሶን ከተማ የታላቅዋ ዲያና ቤት መቅደስና ከሰማይ የወረደው ምስል ጠባቂ መሆንዋን የማያውቅ የትኛው ሰው ነው?
36እንግዲህ ይህ የማይካድ ነገር መሆኑ ከታያችሁ፣ ጸጥ ልትሉ፣ አንዳች ነገርም በችኰላ ልታደርጉ አይገባም፤
37ምክንያቱም አብያተ መቅደስን ያልሰረቁ፣ አማልክታችንንም ያልሰደቡ እነዚህን ሰዎች ወደዚህ ፍርድ ቤት አምጥታችኋል።
38ስለዚህ ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉ አንጥረኞች የሚከሱት ሰው ካለ፣ ፍርድ ቤቱ ክፍት ነው፤ ዳኞችም አሉ፤ እዚያ እርስ በርስ ይካሰሱ።
39ስለ ሌላ ጉዳይ የምትፈልጉት ነገር ካለ ግን፣ ችግሩ በመደበኛው ጉባኤ ይፈታል፤
40ምክንያቱም በዛሬው ቀን የነበረው ዐመፅ ሳያስጠይቀን አይቀርም። የነበረው ግርግር መንሥኢ የለውም፤ እንዲህ ነው ብለን ልንገልጸውም አንችልም።”
41ጸሓፊው ይህን ተናግሮ ጉባኤውን አሰናበተው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።