1ቴዎፍሎስ ሆይ፣ ኢየሱስ እስካረገበት ቀን ድረስ ለማድረግና ለማስተማር የጀመረውን ሁሉ የሚናገረውን የመጀመሪያውን መጽሐፍ ጻፍሁ፤
2ይህም የሆነው ጌታ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እርሱ የመረጣቸውን ሐዋርያትን ካዘዛቸው በኋላ ነበር፤
3ለምርጦቹ ከመከራው በኋላ ሕያው ሆኖ ተገልጦላቸዋል። አርባ ቀን እየታያቸው፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየተናገረ ቆየ።
4ከእነርሱም ጋር ዐብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፤ ነገር ግን "ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን ተስፋ ጠብቁ፤
5በእርግጥ ዮሐንስ በውሃ አጥምቆ ነበር፤ እናንተ ግን በጥቂት ቀናት ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ" አለ።
6ሐዋርያት በአንድነት ተሰብስበው ሳለ፣ “ጌታ ሆይ፣ ይህ የእስራኤልን መንግሥት የምትመልስበት ጊዜ ነውን?” ብለው ጠየቁት።
7እርሱም እንደዚህ አላቸው፤ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ጊዜ ወይም ወቅት ማወቅ እናንተን አይመለከትም።
8ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ ሲመጣ፣ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፣ በሰማርያና እስከ ምድር ዳርቻ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።”
9ጌታ ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ከተናገረ በኋላ፣ ሐዋርያቱ እያዩት ወደ ላይ ዐረገ፤ ደመናም ከዐይናቸው ሰወረው።
10ትኵር አድርገው ወደ ሰማይ እየተመለከቱ ሳለ፣ ድንገት ነጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ።
11እነርሱም፣ “እናንተ የገሊላ ሰዎች፣ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ለምን እዚህ ትቆማላችሁ? ወደ ሰማይ የወጣው ይህ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ ባያችሁበት ሁኔታ ተመልሶ ይመጣል” አሏቸው።
12ከዚያም በኋላ፣ የሰንበት ቀን ጕዞ ያህል ከሚያስሄደው፣ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ካለው ከደብረ ዘይት ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ።
13ሐዋርያት እዚያ ሲደርሱ፣ ወደሚቈዩበት፣ ወደ ላይኛው ሰገነት ወጡ። እነርሱም ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ ያዕቆብ፣ እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ ቶማስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ቀናተኛው ስምዖንና የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ ነበሩ።
14ሁሉም በአንድነት ሆነው፣ ሴቶቹ፣ የኢየሱስ እናት ማርያምና ወንድሞቹም ጭምር በጸሎት ይተጉ ነበር።
15በዚያ ጊዜ ጴጥሮስ 120 ያህል በሚሆኑት ወንድሞች መካከል ቆመ፤ እንደዚህም አለ፤
16“ወንድሞች ሆይ፣ ኢየሱስን የያዙትንና መርቶ ያመጣውን ይሁዳን በሚመለከት መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ አስፈላጊ ነበር።
17ይሁዳ ከእኛ እንደ አንዱ ተቈጥሮና የዚህን አገልግሎት ድርሻም ተቀብሎ ነበርና።
18“ይሁዳም ለክፉ ሥራው በተከፈለው ዋጋ መሬት ገዛ። ከዚያም በግንባሩ ተደፋ፤ አካሉ ተሰነጠቀ፤ አንጀቱም ተዘረገፈ።
19በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ መሬቱ በቋንቋቸው አኬልዳማ [የደም መሬት] ተብሎ እንደሚጠራ ታወቀ።
20በመዝሙር መጽሐፍ፦ መኖሪያው ወና ይሁን፤ የሚኖርበት አንድ ሰውም እንኳ አይገኝ፤ ሹመቱንም ሌላ ሰው ይውሰደው፤ ተብሎ ተጽፎአልና።
21ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በመካከላችን በገባበትና በወጣበት ጊዜ ሁሉ ዐብረውን ከቈዩ ሰዎች፣
22ይኸውም ዮሐንስ ካጠመቀው ጥምቀት ጀምሮ ኢየሱስ ከእኛ እስካረገበት ቀን ድረስ፣ ከነበሩት ከእነዚህ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር ሊሆን ይገባል።”
23ኢዮስጦስም የሚባለውን፣ በርስያን ተብሎ የሚጠራውን ዮሴፍንና ማትያስን፣ ሁለት ሰዎችን እንዲቀርቡ አደረጉ።
24እንደዚህ ብለውም ጸለዩ፤ “ጌታ ሆይ፣ የሰዎችን ሁሉ ልብ አንተ ታውቃለህ፤ ስለዚህ ከእነዚህ ከሁለቱ የትኛውን እንደ መረጥኸው ግለጥ፤
25ይኸውም ይሁዳ ወደገዛ ስፍራው ትቶት በሄደው በዚህ አገልግሎትና ሐዋርያነት ውስጥ ስፍራ እንዲያገኝ ነው።”
26ሐዋርያት ዕጣዎችን ለእነርሱ ጣሉ፤ ዕጣውም ለማትያስ ወደቀ፤ እርሱም ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር አንድ ሆኖ ተቈጠረ።