መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 18

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚህ በኋላ፣ ጳውሎስ ከአቴና ወደ ቆሮንቶስ ሄደ።
2እዚያም ከጳንጦስ ወገን የሆነ አቂላ የሚባል አይሁዳዊ አገኘ። እርሱም አይሁድ ሁሉ ከሮም እንዲወጡ ቀላውዴዎብ ባዘዘው መሠረት፣ ከሚስቱ ከጵርቅላ ጋር በቅርብ ከኢጣሊያ የመጣ ሰው ነበር። ጳውሎስም ከእነርሱ ጋር ተቀራረበ።
3ሥራቸው አንድ ዓይነት ስለ ሆነም፣ በእነርሱ ዘንድ እየኖረ ዐብሮአቸው ይሠራ ነበር። ሥራቸውም ድንኳን መስፋት ነበር።
4በየሰንበቱም በምኵራብ ውስጥ በመገኘት እየተከራከረ፣ አይሁድንም ግሪኮችንም ያሳምን ነበር።
5ሲላስና ጢሞቴዎስ ከመቄዶንያ እርሱ ወዳለበት በወረዱ ጊዜ ግን፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለአይሁድ እንዲመሰክር መንፈስ ቅዱስ ጳውሎስን ገፋፋው።
6አይሁድ በተቃወሙትና በተሳደቡ ጊዜ፣ ጳውሎስ ልብሱን እያራገፈባቸው፣ «ደማችሁ በራሳችሁ ላይ ይሁን፤ እኔ ንጹሕ ነኝ፤ ከአሁን ጀምሮ ወደ አሕዛብ እሄዳለሁ» አላቸው።
7ከዚያም ወጥቶ ቲቶ ኢዮስጦስ ወደሚባል፣ እግዚአብሔርን ወደሚያመልክ ሰው ቤት ሄደ። ቤቱም በምኵራብ አጠገብ ነበር።
8ቀርስጶስ የተባለም የምኵራብ አለቃ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር በጌታ አመነ። ጳውሎስ ሲናገር ከሰሙት ከቆሮንቶስ ሰዎች መካከልም ብዙዎቹ አምነው ተጠመቁ።
9ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን እንዲህ አለው፤ "አትፍራ ተናገር፣ ዝምም አትበል።
10ምክንያቱም እኔ ከአንተ ጋር አለሁ፤ ሊጎዳህ የሚነሣብህ ማንም የለም፤ እንዲያውም በዚህ ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝ።"
11ጳውሎስም በመካከላቸው የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረ አንድ ዓመት ከስድስት ወር እዚያ ተቀመጠ።
12ነገር ግን ጋልዮስ የአካይያ አገረ ገዢ በሆነ ጊዜ፣ አይሁድ በጳውሎስ ላይ በአንድነት ተነሡ፤ ይዘውም ፍርድ ፊት አቀረቡት።
13ከዚያም፣ “ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዲያመልክ ይህ ሰው ከሕግ ውጪ እየቀሰቀሰ ነው” አሉ።
14ጳውሎስ ሊናገር ሲልም፣ ጋልዮስ አይሁድን፣ “አይሁድ ሆይ፣ ጉዳዩ በርግጥ የበደል ወይም የወንጀል ቢሆን ኖሮ፣ ልታገሣችሁ በተገባኝ ነበር።
15ነገር ግን ክርክሩ ስለ ቃላትና ስለ ስሞች፣ ደግሞም ስለ ገዛ ሕጋችሁ ስለ ሆነ፣ እናንተው ራሳችሁ ተነጋገሩበት። እኔ ስለ እንደዚህ ዐይነት ጉዳይ ፈራጅ መሆን አልፈልግም” አለ።
16ከዚያም ጋልዮስም ከችሎቱ አስወጣቸው።
17እነርሱ ሁሉ ግን የምኵራቡን አለቃ ሶስቴንስን በጉልበት ይዘው በፍርድ ወንበሩ ፊት ደበደቡት። ይሁን እንጂ፣ ይህ ድርጊታቸው ለጋልዮስ ደንታም አልሰጠውም።
18ጳውሎስም ብዙ ቀናት ከተቀመጠ በኋላ፣ ወንድሞችን ተሰናብቶ ከጵርስቅላና ከአቂላ ጋር በመርከብ ወደ ሶርያ ሄደ። ስእለት ስለ ነበረበትም፣ ከወደቡ ከክንክራኦስ ከመነሣቱ በፊት ራሱን ተላጨ።
19ኤፌሶን በደረሱ ጊዜ፣ ጳውሎስ ጵርስቅላንና አቂላን ትቶአቸው ወደ ምኵራብ ሄዶ ከአይሁድ ጋር ይነጋገር ነበር።
20እነርሱም ረዘም ላለ ጊዜ ዐብሮአቸው እንዲቆይ ሲለምኑት፣ ጳውሎስ እንቢ አለ።
21ከዚያም፣ “እግዚአብሔር ቢፈቅድ እንደ ገና ተመልሼ እመጣለሁ” ብሎ ተሰናበታቸው። ከኤፌሶንም ተነሥቶ በመርከብ ሄደ።
22ጳውሎስ ቂሣርያ በደረሰ ጊዜ፣ በኢየሩሳሌም ወደ ነበረችው ቤተ ክርስቲያን ወጥቶ ሰላምታ አቀረበላቸውና ወደ አንጾኪያ ወረደ።
23በዚያም ጥቂት ጊዜ ከተቀመጠ በኋላ፣ ጳውሎስ ተለያቸው፤ በገላትያና በፍርግያ አካባቢ በማለፍም ደቀ መዛሙርቱን ሁሉ አበረታታ።
24ትውልዱ እስክንድርያዊ የሆነ፣ አጵሎስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ እርሱም የንግግር ችሎታና በቂ የቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት ያለው ሰው ነበር።
25አጵሎስ የጌታን ትምህርት በሚገባ የተማረ በመሆኑ፣ በመንፈሱ ተነቃቅቶ ስለ ኢየሱስ በትክክል ይናገርና ያስተምር ነበር፤ የሚያውቀው ግን ስለ ዮሐንስ ጥምቀት ብቻ ነበር።
26አጵሎስ ምኵራብ ውስጥ በድፍረት መናገር ጀመረ። ነገር ግን ጵርስቅላና አቂላ በሰሙት ጊዜ፣ ወደ እርሱ ቀርበው የእግዚአብሔር መንገድ ይበልጥ በትክክል አብራሩለት።
27እርሱም ወደ አካይያ ማለፍ በፈለገ ጊዜ፣ ወንድሞች አበረታቱት፤ በአካይያ የነበሩ ደቀ መዛሙርት እንዲቀበሉትም ጻፉላቸው። እዚያ በደረሰ ጊዜም፣ በጸጋ ያመኑትን እጅግ ረዳቸው።
28አጵሎስ ከቅዱሳት መጻሕፍት እያስደገፈ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ በማሳየት በኀይሉና በችሎታው አይሁድን ተከራክሮ ረታቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።