መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 17

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አንፊጶልና አጶሎንያ በተባሉ ከተሞች በኩል ካለፉ በኋላም፣ ተሰሎንቄ ወደ ተባለች ከተማ መጡ፤ በዚያም ከተማ የአይሁድ ምኵራብ ነበረ።
2ጳውሎስም እንደ ልማዱ፣ ወደ አይሁድ ሄዶ፣ ለሦስት ሰንበታት ያህል ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር።
3ቅዱሳት መጻሕፍትንም እየገለጠ፣ ክርስቶስ መከራን መቀበልና ከሙታን መነሣት እንደ ነበረበት እያስረዳም፣ «ይህ እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው» ይላቸው ነበር።
4ከአይሁድም አንዳንዶቹ መልእክቱን ተቀብለው ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ፤ በተጨማሪም ለእግዚአብሔር ያደሩ ግሪኮች፣ የከበሩ ብዙ ሴቶችና ከፍተኛ ቍጥር ያላቸው ሰዎች ከእነርሱ ጋር ሆኑ።
5ሌሎች ያላመኑ አይሁድ ግን፣ በቅንዓት በመነሣሣትና ክፉ ሰዎችን ከጎዳና ላይ በማሰባሰብ ሕዝብን አከማችተው ከተማዋን አወኩአት። የኢያሶንን ቤት በዐመፅ በመክበብም፣ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ለሕዝቡ ለማስረከብ ፈለጉ።
6ሊያገኙአቸው ባልቻሉ ጊዜም፣ ኢያሶንንና ሌሎች ወንድሞችን ይዘው መሬት ለመሬት እየጎተቱ ወደ ከተማዋ ባለ ሥልጣናት ፊት አወጡአቸው፤ እንዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ «እነዚህ ዓለምን የገለባበጡ ሰዎች ወደዚህ ደግሞ መጥተዋል፤
7ኢያሶን በቤቱ የተቀበላቸው እነዚህ ሰዎች የቄሣርን ሕግ የሚቃወሙ ናቸው፤ ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ እያሉ ነው።»
8ሕዝቡና የከተማው ሹሞች እነዚህን ነገሮች ሲሰሙ፣ ታወኩ።
9ከኢያሶንና ከሌሎቹም የዋስትና ገንዘብ ተቀብለው ለቀቁአቸው።
10ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በዚያው ሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው። እነርሱም እዚያ በደረሱ ጊዜ፣ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ።
11እዚህ የሚኖሩ ሰዎች በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ሰፊ አስተሳሰብ ስለ ነበራቸው፣ ነገሩ እንዲህ ይሆንን በማለት ቅዱሳት መጻሕፍትን በየዕለቱ እየመረመሩ፣ ልባቸው ቃሉን ለመቀበል ዝግጁ ነበር።
12ስለዚህ ከእነርሱ ብዙዎች አመኑ፤ በተጨማሪ አንዳንድ ተደማጭነት ያላቸው የግሪክ ሴቶችና ሌሎች ወንዶችም አመኑ።
13በተሰሎንቄ የነበሩ አይሁድም ጳውሎስ በቤርያም ደግሞ ቃሉን እንደ ሰበከ ባወቁ ጊዜ፣ ወደዚያ ሄደው ሕዝቡን በማነሣሣት አወኩ።
14ወንድሞችም ወዲያው ጳውሎስን ወደ ባሕሩ አካባቢ እንዲሄድ አደረጉ ፤ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው ቆዩ።
15ጳውሎስን ይሸኙ የነበሩት ሰዎችም እስከ አቴና ድረስ ወሰዱት። ከዚያም ሲነሡ፣ ሲላስና ጢሞቴዎስ በተቻለው ፍጥነት ወደ እነሱ እንዲመጡ የሚል መልእክት ከጳውሎስ ተቀብለው ሄዱ።
16ጳውሎስ አቴና ተቀምጦ እየጠበቃቸው ሳለ፣ ከተማዋ በጣዖት የተሞላች መሆንዋን ሲያይ፣ መንፈሱ በውስጡ ተበሳጨበት።
17ስለዚህም ነገር በምኵራብ ከሚያገኛቸው አይሁድ፣ እግዚዘብሔርንም ከሚያመልኩ ሌሎች ሰዎችና ዘወትር በገበያ ቦታ ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይነጋገር ነበር።
18ከኤፌቆስና ከኢስጦኢኮች ወገን የሆኑ አንዳንድ ፈላስፎችም ደግሞ ጳውሎስን አገኙት። ከእነርሱም አንዳንዶች፣ «ይህ ለፍላፊ ምን እያለ ነው?» አሉ። ሌሎቹም፣ ስለ ኢየሱስና ስለ ትንሣኤው ሲሰብክ ስለ ሰሙት፣ «ስለ እንግዳ አማልክት የሚሰብክ ይመስላል» አሉ።
19ከዚያም፣ «አንተ የምትናገረውን ይህን ዐዲስ ትምህርት ማወቅ እንችላለን ወይ?
20ምክንያቱም እየሰማናቸው ያሉ ነገሮች እንግዳ ናቸው። ስለዚህ፣ የእነዚህን ነገሮች ትርጕም ማወቅ እንሻለን» አሉት።
21አቴናውያንና ሌሎች በዚያ የሚኖሩ እንግዶች ሁሉ ጊዜአቸውን የሚያሳልፉት በሌላ ጉዳይ ሳይሆን፣ ስለ ዐዳዲስ ነገሮች በማውራት ወይም በመስማት ነበር።
22ስለዚህ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፤ «እናንተ የአቴና ሰዎች ሆይ፣ በየትኛውም መልክ እጅግ ሃይማኖተኞች እንደ ሆናችሁ እመለከታለሁ።
23ምክንያቱም ወዲያ ወዲህ እየተመላለስሁ የምታመልኳቸውን ስመለከት፣ ላልታወቀ አምላክ የሚል ጽሑፍ የተጻፈበት አንድ መሠዊያ አይቻለሁ። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን አምላክ እኔ እነግራችኋለሁ።
24ዓለምንና በውስጧ የሚገኙትን ሁሉ የፈጠረ አምላክ፣ የሰማይና የምድር ጌታ በመሆኑ፣ በእጅ በተሠራ መቅደስ ውስጥ አይኖርም።
25ለሰዎች ሕይወት፣ እስትንፋስንና ሁሉንም ነገር የሚሰጠው እርሱ ራሱ ስለ ሆነ፣ እግዚአብሔር አንዳች እንደሚያስፈልገው በሰው እጅ አይገለገልም።
26በምድር ገጽ ላይ የሚኖሩትንም ሕዝቦች ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ የሚኖሩባቸውንም ስፍራዎች ወሰን፣ ወቅቶችንም የወሰነላቸው እርሱ ነው።
27ስለዚህ እግዚአብሔርን ቢፈልጉ ሊያገኙት ይችላሉ፤ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ እርሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።
28ምክንያቱም የምንኖረው፣ የምንንቀሳቀሰውና በሕይወት የቆምነው በእርሱ ነው፤ ከእናንተ ባለ ቅኔዎች አንዱ እንዳለውም፣ 'እኛ ልጆቹ ነን።'
29እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን፣ መለኮትን በሰው ጥበብና እንደ ተቀረጸ ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ አድርገን ማሰብ የለብንም።
30ስለዚህ እግዚአብሔር የአለማወቅ ጊዜያትን አሳልፎ፣ አሁን ግን በየትኛውም ስፍራ ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ ያዛል።
31ምክንያቱም በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ላይ የሚፈርድበትን ቀን አዘጋጅቶአል። እግዚአብሔር ይህን ሰው ከሙታን በማስነሣቱ ለሁሉ ሰው ማረጋገጫ ሰጥቶአል።"
32የአቴና ሰዎች ስለ ሙታን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ፣ አንዳንዶቹ በጳውሎስ ላይ አፌዙ፤ሌሎች ግን፣ «ስለዚህ ጉዳይ ዳግመኛ እንሰማሃለን» አሉት።
33ከዚህ በኋላ፣ ጳውሎስ ተለይቶአቸው ሄደ፤
34አንዳንድ ወንዶች ግን ከእርሱ ጋር ተባብረው አመኑ፤ በእነዚህም ውስጥ የአርዮስፋጎስ አመራር አባል ዲዮናስዮስ፣ ደማሪስ የተባለች ሴትና ሌሎችም ይገኛሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።