1ጳውሎስ ወደ ደርቤና ወደ ልስጥራ መጣ፤ እነሆም፣ እናቱ አይሁዳዊት አማኝ የሆነች፣ አባቱ ግን ግሪክ የሆነ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር አገኘ።
2በልስጥራና በኢቆንዮን የነበሩ ወንድሞችም ስለ እርሱ ጥሩ ምስክርነት ነበራቸው።
3ጳውሎስም እርሱን ይዞ መጓዝ ፈለገ፤ በዚያ አካባቢ ስለ ነበሩ አይሁድ ሲልም ጢሞቴዎስን ገረዘው፤ አባቱ የግሪክ ሰው እንደ ሆነ ሁሉም ያውቁ ነበርና።
4በየከተሞቹ በሚዞሩበት ጊዜ፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲጠብቁት በኢየሩሳሌም የነበሩ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የጻፉትን መመሪያ ሰጡአቸው።
5ስለዚህ አብያተ ክርስቲያናቱ በእምነት እየበረቱ፣ ቍጥራቸውም በየዕለቱ እየጨመረ ነበር።
6በእስያ አውራጃ ቃሉን እንዳይሰብኩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው፣ ጳውሎስና ባልደረቦቹ በፍርግያና በገላትያ አውራጃዎች አድርገው ዐለፉ።
7ወደ ሚስያ አካባቢ በደረሱ ጊዜ፣ ቢታንያ ለመግባት ሞከሩ፤ የኢየሱስ መንፈስ ግን ከለከላቸው።
8ስለዚህ ሚስያን ዐልፈው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ።
9ጳውሎስም አንድ የመቄዶንያ ሰው ቆሞ፣ “ወደ መቄዶንያ ተሻግረህ ርዳን” እያለ ሲለምነው ሌሊት በራእይ ታየው።
10ራእዩንም ካየ በኋላ፣ ወዲያው ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ተነሣን፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ወንጌልን ለእነርሱ እንድንሰብክ እንደ ጠራን ዐሰብን።
11ከጢሮአዳ ተነሥተንም ቀጥታ በመርከብ ወደ ሳሞትራቄ ሄድን፤ በማግስቱም ናጱሌ ደረስን፤
12ከዚያም የመቄዶንያ ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ፊልጵስዩስ ሄድን፤ ከተማዋ የወረዳው ዋና ከተማና የሮም ቅኝ ግዛት ነበረች፤ በዚችም ከተማ ብዙ ቀን ተቀመጥን።
13በሰንበት ቀንም፣ በወንዝ አጠገብ በነበረው በር በኩል ወደ ውጭ ወጣን፤ ይህም ስፍራ የጸሎት ቦታ እንደ ሆነ ዐሰብን። በዚያም ተቀምጠን ተሰብስበው ለነበሩ ሴቶች ተናገርን።
14ከትያጥሮን ከተማ የመጣችና የሐምራዊ ሐር ሻጭ የነበረች፣ ልድያ የምትባል፣ እግዚአብሔርን የምታመልክ አንድ ሴት ትሰማን ነበር። ጳውሎስ እየተናገረ የነበረውን በሚገባ እንድታደምጥ፣ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።
15ከቤተ ሰብዋ ጋር በተጠመቀች ጊዜም፣ “በጌታ ማመኔን ከተረዳችሁልኝ ወደ ቤቴ ግቡና ተቀመጡ” ብላ ለመነችን፤ አስገደደችንም።
16አንድ ቀን ጸሎት ቦታ ስንሄድ የጥንቈላ መንፈስ ያደረባት አንዲት ወጣት አገኘችን፤ በዚህ የጥንቈላ ሥራዋም ለአሳዳሪዎችዋ ከፍተኛ ገቢ ታስገኝ ነበር።
17ይህችው ሴት ጳውሎስንና እኛን ከኋላ እየተከተለች፣ “እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው፤ የመዳንን መንገድ ይነግሯችኋል” እያለች ትጮኽ ነበር።
18ይህንም ብዙ ቀን ደጋገመች። ጳውሎስ ግን በዚህ እጅግ ተበሳጨ፤ ዘወር ብሎም መንፈሱን፣ “ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ” አለው፤ በዚያው ቅጽበትም መንፈሱ ወጣ።
19አሳዳሪዎችዋም ተስፋ የሚያደርጉበት የገቢያቸው ምንጭ እንደ ጠፋ ባዩ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው በምድር ላይ እየጎተቱ በገበያ ስፍራ ባለ ሥልጣኖቹ ፊት አቀረቡአቸው።
20ወደ ገዢዎችም አምጥተዋቸው፣ “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ሳሉ በከተማችን ውስጥ ከፍተኛ ሁከት እየፈጠሩ ነው።
21እኛ ሮማውያን ለመቀበል ያልተፈቀዱልንን ነገሮች ያስተምራሉ” አሉ።
22በዚህ ጊዜ ሕዝቡ በጳውሎስና በሲላስ ላይ በአንድነት ተነሡ፤ ገዦቹም ልብሳቸውን አስወልቀው በዱላ እንዲደበድቡአቸው አዘዙ።
23ብዙ ድብደባ ካደረሱባቸው በኋላ፣ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፤ የወኅኒ ጠባቂውም በጥንቃቄ እንዲጠብቃቸው አዘዙት።
24የወኅኒ ጠባቂውም ይህን ትእዛዝ ተቀብሎ፣ ወደ ውስጠኛው እስር ቤት ጣላቸው፤ እግራቸውንም ከግንድ ጋር አጣብቆ አሰራቸው።
25እኩለ ሌሊት አካባቢም፣ ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ በዝማሬ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፤ ሌሎች እስረኞችም አደመጡአቸው።
26ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስከሚናጋ ድረስ ታላቅ የምድር መናወጥ ተከሠተ፤ ወዲያውም የወኅኒው በሮች ሁሉ ተከፈቱ፤ የታሳሪዎችም ሁሉ ሰንሰለቶች ተፈቱ።
27የወኅኒ ጠባቂውም ከእንቅልፉ ነቅቶ በሮቹ እንደ ተከፈቱ አየ፤ እስረኞቹ ያመለጡ ስለ መሰለውም፣ ሰይፉን መዞ ራሱን ሊገድል ቃጣ።
28ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ፣ “ራስህን አትጉዳ! እኛ ሁላችን እዚሁ አለን” ብሎ ጮኸ።
29የወኅኒ ጠባቂውም መብራት ለምኖ ሮጦ ወደ ውስጥ ገባ፤ በፍርሀት እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ ፊት ተደፋ፤
30ወደ ውጭም አስወጥቶአቸው፣ “ጌቶች ሆይ፣ ለመዳን ምን ማድረግ አለብኝ?” አላቸው።
31እነርሱም፣ “በጌታ ኢየሱስ እመን፤ አንተም ቤተ ሰዎችህም ትድናላችሁ” አሉት።
32ጳውሎስና ሲላስ ለእርሱና አብረውት በቤት ለነበሩ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ተናገሩ።
33የወኅኒ ጠባቂውም ሌሊት፣ በዚያው ሰዓት ወስዶአቸው ቍስላቸውን አጠበላቸው። እርሱና ቤተ ሰዎቹም ሁሉ ወዲያው ተጠመቁ።
34ጳውሎስንና ሲላስንም ወደ ቤቱ ይዞአቸው ወጣ፤ ምግብም አቀረበላቸው። ሁሉም በእግዚአብሔርም በማመናችው ከቤተ ሰዎቹ ጋር እጅግ ደስ አለው።
35ሲነጋም ገዦቹ፣ “እነዚያን ሰዎች ልቀቋቸው” የሚል ትእዛዝ ለጠባቂዎቹ ላኩ።
36የወኅኒ ጠባቂውም፣ “ገዦቹ እንድትፈቱ ትእዛዝ ለእኔ ልከዋል፤ ስለዚህ ውጡና በሰላም ሂዱ” ብሎ ለጳውሎስ ነገረው።
37ጳውሎስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ሮማውያን የሆንነውን እኛን ያለ ፍርድ በሕዝብ ፊት ደብድበውናል፤ ወደ ወኅኒም አስገብተውናል፤ ታዲያ፣ አሁን በድብቅ ያስወጡናል? በፍጹም አይሆንም፤ እነርሱ ራሳቸው መጥተው ያስወጡን።”
38ጠባቂዎቹም ይህንኑ አባባል ለገዦቹ ነገሯቸው፤ ገዦቹም ጳውሎስና ሲላስ ሮማውያን እንደ ሆኑ በሰሙ ጊዜ ፈሩ።
39መጥተውም ተማጸኑአቸው፤ ከወኅኒም ካስወጡአቸው በኋላ፣ ከከተማው እንዲወጡ ጳውሎስንና ሲላስን ለመኑአቸው።
40ጳውሎስና ሲላስም ከወኅኒው ወጥተው ወደ ልድያ ቤት ገቡ። ወንድሞችንም ባዩአቸው ጊዜ፣ አበረታቱአቸው፤ ከዚያም ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ።