መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

የሐዋርያት ሥራ 15

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አንዳንድ ሰዎች ከአይሁድ ወደ አንጾኪያ ወርደው፣ «በሙሴ ሥርዓት መሠረት ካልተገረዛችሁ መዳን አትችሉም» በማለት ወንድሞችን አስተማሯቸው።
2ጳውሎስና በርናባስም ከእነርሱ ጋር ጥልና ክርክር በገጠሙ ጊዜ፣ ጳውሎስና በርናባስ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ስለዚህ ጉዳይ በኢየሩሳሌም ወደ ነበሩ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እንዲወጡ ወንድሞች ወሰኑ።
3ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን ተልከው፣ በፊንቄና በሰማርያ በኩል አድርገው ሲሄዱ፣ የአሕዛብን መለወጥ እያወጁ ዐለፉ፤ ይህም ወንድሞችን ሁሉ እጅግ ደስ አሰኛቸው።
4ወደ ኢየሩሳሌም በመጡ ጊዜም፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በደስታ ተቀበሏቸው፤ እነ ጳውሎስም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ሆኖ የሠራውን ሁሉ ነገሯቸው።
5ከፈሪሳውያን ወገን ያመኑ አንዳንድ ሰዎች ግን ተነሥተው፣ «እነርሱን መግረዝና የሙሴንም ሕግ እንዲጠብቁ ማዘዝ ያስፈልጋል» አሉ።
6ስለዚህ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ይህን ጉዳይ ለማየት ተሰበሰቡ።
7ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ ቆመና እንዲህ አለ፦ «ወንድሞች ሆይ፣ አሕዛብ የወንጌልን ቃል ከአፌ እንዲሰሙና እንዲያምኑ፣ እግዚአብሔር ከጥቂት ጊዜያት በፊት ከእናንተ መካከል እኔን እንደ መረጠኝ ታውቃላችሁ።»
8ልብን የሚያውቅ አምላክ፣ ለእኛ እንዳደረገው ሁሉ፣ ለእነርሱም መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፤
9በእኛና በእነርሱ መካከልም ልባቸውን በእምነት በማንጻት ልዩነት አላደረገም።
10እንግዲህ አባቶቻችንና እኛ መሽከም ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን ለምን እግዚአብሔርን ትፈታተናላችሁ?
11ነገር ግን እኛም በጌታ በኢየሱስ ጸጋ እንደ እነርሱ እንደምንድን እናምናለን።»
12በርናባስና ጳውሎስ እግዚአብሔር በእነርሱ አማካይነት በአሕዛብ መካከል ስለ ሠራው ምልክትና ድንቅ ሲናገሩ፣ ሕዝቡ ሁሉ በጸጥታ አደመጡ።
13ንግግራቸውንም በጨረሱ ጊዜ፣ ያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰ፤ «ወንድሞች ሆይ፣ አድምጡኝ።
14እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ሕዝብ ከእነርሱ መካከል ይወስዱ ዘንድ፣ አሕዛብን በመጀመሪያ በጸጋ እንደ ረዳ ስምዖን ተናግሮአል።
15የነቢያት ቃል ከዚህ ጋር ይስማማል እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤
16ከእነዚህ ነገሮች በኋላ እመለሳለሁ፤ ፍርስራሹንም መልሼ እተክላለሁ፤ እንደገናም ዐድሳለሁ፤
17ይኸውም የተረፉት ሰዎችና በስሜ የተጠሩ አሕዛብ፣ እግዚአብሔርን እንዲፈልጉ ነው።
18እነዚህ ጥንታዊ ነገሮች እንዲታወቁ የሚያደርግ ጌታ የሚለው ይህን ነው።
19ስለዚህ የእኔ ዐሳብ ከአሕዛብ ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን እንዳናስጨንቃቸው ነው፤
20ነገር ግን በጣዖታት ከመርከስ፣ ከዝሙት፣ ከታነቀና ከደም እንዲርቁ እንጻፍላቸው።
21ሙሴስ ከጥንት ዘመናት ጀምሮ በከተሞች ሁሉ በየሰንበታቱ በምኵራብ የሚሰብኩና የሚያነቡ ሰዎች አሉትና።»
22ስለዚህ በርስያን የተባለው ይሁዳንና ሲላስን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አድርገው እንዲመርጡና፣ ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ እንዲልኳቸው ለሐዋርያትና ለሽማግሌዎች፣ ከቤተ ክርስቲያን ሁሉ ጋር መልካም መስሎ ታያቸው።
23እንዲህም ብለው ጻፉ፤ «ለሐዋርያት፣ ለሽማግሌዎችና ወንድሞች፣ እንዲሁም በአንጾኪያ፣ በሶርያና በኪልቅያ ለሚገኙ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ወንድሞች፣ ሰላም ለእናንተ ይሁን።
24እኛ ያላዘዝናቸው አንዳንድ ሰዎች ከእኛ ዘንድ መጥተው ነፍሳችሁን በሚያስጨንቅ ትምህርት እንዳስቸገሩአችሁ ሰምተናል።
25ስለዚህ በአንድ ልብ ሆነን ሰዎችን መርጠን ከወዳጆቻችን ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር ወደ እናንተ መላክ ለሁላችንም መልካም መስሎ ታየን፤
26እነዚህ ሰዎች ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሲሉ ለሕይወታቸው እንኳ ያልሣሡ ናቸው።
27ይህንኑ እንዲነግሯችሁ ይሁዳንና ሲላስን ወደ እናንተ ልከናል፤
28ከእነዚህ አስፈላጊ ነገሮች በላይ ከባድ ሸክም እንዳንጭንባችሁ፣ ለመንፈስ ቅዱስና ለእኛ መልካም መስሎ ታይቶናልና፤
29ይኸውም ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደም፣ ከታነቀ፣ ከዝሙትም እንድትርቁ ነው። ራሳችሁን ከእነዚህ ብትጠብቁ መልካም ይሆንላችኋል፤ ደኅና ሁኑ።»
30ከዚያም ተሰናብተው ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ ሕዝቡንም ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጡአቸው።
31ደብዳቤውንም አንብበው ስለ ተጽናኑ በጣም ደስ አላቸው።
32ደግሞም ይሁዳና ሲላስ ነቢያት ስለ ነበሩ፣ወንድሞችን በብዙ ቃል በመምከር አበረታቱአቸው።
33በዚያም ጥቂት ጊዜ ከተቀመጡ በኋላ፣ከወንድሞች በሰላም ተሰናብተው ወደ ላኳቸው ሄዱ።
34ሲላስ ግን እዚያው መቆየት መልካም መስሎ ታየው።
35ጳውሎስና በርናባስ ግን የጌታን ቃል ባስተማሩበትና በሰበኩበት በአንጾኪያ ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ተቀመጡ።
36ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ጳውሎስ በርናባስን፣ «ተመልሰን የጌታን ቃል በሰበክንበት ከተማ ሁሉ ያሉትን ወንድሞች እንጐብኝ፤ በምን ሁኔታ እንዳሉም እንወቅ» አለ።
37በርናባስም ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ደግሞ ከእነሱ ጋር ይዞ ለመሄድ ፈለገ።
38ጳውሎስ ግን ማርቆስን ይዞ መሄድ አልፈለገም፤ ምክንያቱም ማርቆስ ከዚህ ቀደም ከእነርሱ ጋር ለሥራ በመሄድ ፈንታ፣ በጵንፍልያ ተለይቶአቸው ቀርቶ ነበር።
39በመካከላቸው ከፍተኛ አለምስማማት ስለ ተፈጠረም፣ ተለያዩ፤ በርናባስም ማርቆስን ይዞ ወደ ቆጵሮስ በመርከብ ሄደ።
40ጳውሎስ ግን ሲላስን መረጠ፤ ወንድሞች ለጌታ ጸጋ አደራ ከሰጡት በኋላ፣ ተለይቶአቸው ሄደ።
41ከዚያም አብያተ ክርስቲያናትን እያበረታታ በሶርያና በኪልቅያ ይዞር ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።